ፈልግ

የአፍሪካ ሴቶች በግብርና ሥራ ተሰማርተው፣ የአፍሪካ ሴቶች በግብርና ሥራ ተሰማርተው፣ 

“ኦክስፋም”፣ ሴቶች ከሥራቸው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ የማያገኙ መሆኑን አስታወቀ።

ኦክስፋም የተሰኘ በጎ አድራጊ ድርጅት፣ በጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት 2020 ዓ. ም. ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት፣ በዓለማችን ውስጥ 42 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች፣ በሥራ ገበታቸው ተገቢ እንክብካቤ እና ክፍያ  የማይደረግላቸው መሆኑን አስታውቋል። በስዊዘርላንድ፣ ዳቮስ ከተማ ከጥር 12 - 15/2012 ዓ. ም. ድረስ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ፎሬም ባቀረበው ዓመታዊ ሪፖርቱ ፣ በዓለማችን ውስጥ በሕዝቦች መካከል ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ አለመመጣጠን መኖሩን በሪፖርቱ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ኦክስፋም የተሰኘ በጎ አድራጊ ድርጅት “እንክብካቤ ሊደረግ ይገባል” በሚል ርዕስ ስር ባሰፈረው ሪፖርቱ እንደገለጸው፣ በዓለማችን ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ቢሆን ስብዓዊ ክብራቸውን ባስጠበቀ መልኩ እየኖሩ አለመሆኑን አስታውቋል። ከጎርጎሮሳዊያኑ ሰኔ ወር 2018 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 2019 ዓ. ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በዓለማችን የኤኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡን አስረድቶ፣ የኤኮኖሚ እድገቱን ክፍፍል በምናይበት ጊዜ፣ ኤኮኒሚው አንድ ከመቶ በሚሆኑ ሃብታም ሰዎች እጅ መገኘቱን ገልጾ ይህም በ6.9 ቢሊዮን ሰዎች እጅ የተያዘ የተጣራ ሀብት እጥፍ መሆኑን አስረድቷል።

በገቢ አለመመጣጠን የሚከሰት ችግር፣

በዓለማችን አሉ የሚባሉ፣ በቁጥር 2,153 በሚሆኑ ሃብታሞች ኪስ ውስጥ የሚገኝ የሃብት መጠን፣ 4.6 ቢሊዮን ሰዎች ወይም ወደ 60 ከመቶ የሚጠጉ የዓለማን ሕዝቦች ካላቸው የሃብት መጠን በልጦ መገኘቱን ኦክስፋም የተሰኘ በጎ አድራጊ ድርጅት በዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል። በጎ አድራጊ ድርጅቱ በሌላ መመዘኛው፣ በዓለማችን ውስጥ አሉ የሚባሉ 22 በሃብት የበለጸጉ ሰዎች የያዙት የሃብት መጠን፣ በአፍሪካ አህጉር ያሉት ሴቶች ካላቸው የሃብት መጠን በልጦ መገኘቱን አስታውቆ፣ በዓለማችን ውስጥ 46 ከመቶ የሚሆን ሕዝብ የቀን ገቢው ከ5.5 ዶላር በታች መሆኑን አስታውቋል። ድርጅቱ በማከልም በዓለማችን ውስጥ በገቢ መጠን ላይ ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን ጠቅሶ ይህም በሥራ ገበታ ላይ በሚገኙት ሰዎች መካከል እጅግ ጎልቶ የሚታይ መሆኑ አስታውቋል።  

በዓለም ዙሪያ 42 ከመቶ ለሚሆኑ የጤና ባለሞያ ሴቶች ተገቢ ክፍያ አለመደረጉ ችግር ውስጥ ጥሏቸዋል፣

ኦክስፋም በተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ወ/ሮ ሚሻ ማስለንኮቭ እንዳስረዱት፣ የድርጅቱ ዓመታዊ ሪፖርት በጤና አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ለሚገኙ የጤና ባለሞያ ሴቶች ከሚያበረክቱት አገልግሎት ጋር የሚመጣጠን ወርሃዊ ክፍያ የማይከፈላቸው መሆኑን ገልጿል ብለው፣ በትርፍ ጊዜያቸው ተጨማሪ ሥራ እንዳይሰሩ እድል የማይሰጥ፣ የሙሉ ጊዜ ሥራ መሆኑን ሪፖርቱ ያብራራል ብለዋል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የፖሊሲ አማካሪ ወ/ሮ ሚሻ ማስለንኮቭ እንዳስረዱት፣ ዓለም አቀፉ የሴት ሠራተኛ ሃይል ሠንጠርዥ እንደሚያመለክተው በዓለም ዙሪያ 42 ከመቶ ለሚሆኑ የጤና ባለሞያ ሴቶች ከሥራቸው ጋር የሚመጣጠን ክፍያ የማይደረግላቸው መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ ወጣት ሴት ተማሪዎች የትምህርት ቤት ክፍያ ለማጠናቀቅ የሚቸገሩ መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል። የችግሩ ተጠቂ የሚሆኑት በጣም ዝቅተኛ የገቢ መጠን ያላቸው የአፍርካ አህጉር ሴቶች፣ በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ሴቶች መሆናቸውን የፖሊሲ አማካሪዋ ወ/ሮ ሚሻ ማስለንኮቭ አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 January 2020, 15:18