ፈልግ

የሰላም ስምምነቱን የተፈራረሙት የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና የተቃዋሚ ቡድኖች ተወካዮች፣ የሰላም ስምምነቱን የተፈራረሙት የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና የተቃዋሚ ቡድኖች ተወካዮች፣ 

የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ለማስቆም የሚያስችል የሰላም ስምምነት ተፈረመ።

የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና የፖለቲካ ተቃዋሚ እንቅስቃሴዎች በአገራቸው የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን ለማስቆም በሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል። እሑድ ጥር 3/2012 ዓ. ም. ያጸደቁትን የስምምነት ሰነድ በፊርማቸው ያረጋገጡት ጥር 4/2012 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት መሆኑ ታውቋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት፣ የፖለቲካ ተቃዋሚ እንቅስቃሴዎች እና ስምምነቱ በተደረገበት ቦታ እና ቀን ሊገኙ ያልቻሉ ሌሎች የመንግሥት ተቀናቃኞችን ጨምሮ በጋራ የደረሱበትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ያሚያደርጉት ከረቡዕ ጥር 6/2012 ዓ. ም. ጀምሮ መሆኑን በስምምነት ሰነዳቸው ላይ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የደቡብ ሱዳን የሐይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት በጋራ ከሚያዚያ 2-3/2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን የሁለት ቀን ሱባኤ ማድረጋቸው ያታወሳል። በዚህ ሱባኤ ማጠቃለያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባሰሙት የመዝጊያ ንግግር እንደገለጹት “ሰላም፣ ብርሃን እና ተስፋ ደቡብ ሱዳን ውስጥ እውን ሊሆኑ ይችላሉ” በማለት አስተንትኖዋቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በወቅቱ በዚያው የተገኙ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በአገሪቷ ሰላም እንዲፈጠር ቁርጠኛ ሆነው መሥራት እንደሚገባቸው ለመማጸን በማሰብ በእያንዳንዳቸው እግር ሥር ወድቀው ጫማዎቻቸውን መሳማቸው ይታወሳል።

ሁለት ዓመት የወሰደ የሰላም ጥረት ነው፣

በሮም የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር ዋና ጸሐፊ፣ ክቡር አቶ ፓውሎ ኢምፓሊያዞ፣ በጋዜጣዊ መግለቻቸው እንዳታወቁት፣ በሱዳን መንግሥት እና በተቀናቃኝ እንቅስቃሴ መሪዎች መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሰነድ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን አስረድተው፣ ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደባቸው መሆኑን አስረድተው፣ ሁለቱ ወገኖች ወደ ስምምነት እንዲደርሱ መንገድ የከፈተላቸውን የጋራ ውይይቶች በማዘጋጀት እና በማደራደር ረገድ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አስረድተዋል። ዋና ጸሐፊው በማከልም የሱዳን መንግሥት እና ተቀናቃኞቻቸው ወደ ሰላም ስምምነት መድረሳቸው አገሪቱ እንደገና መወለዷን ያበስራል ብለው፣ በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሳይፈሩ በነጻነት ለጋራ ውይይት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀርቡ የሚያደርጋቸው ነው ካሉ በኋላ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን ሰላም እና እርቅ እንዲወርድ በማለት የሚያደርጉት የዘወትር ጥረት በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ መሪዎች ልብ የማረከ መሆኑን አስረድተዋል።

በደቡብ ሱዳን ውስጥ የሰላም ጉዞ ተጀምሯል፣

እሑድ ጥር 3/2012 ዓ. ም. የሰላም ስምምነት ሰነድ በፊርማቸው ያረጋገጡት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተወካዮች እና ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች እንዳስታወቁት፣ ስምምነታቸው በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት የደረሰውን ከፍተኛ ስቃይ፣ ድህነት እና እንዲሁም በአሰቃቂ የጎርፍ አደጋ ችግር ውስጥ ለሚገኝ የደቡብ ሱዳን ህዝብ፣ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች እርዳታቸውን ሳያቋርጡ የሚያዳርሱበትን መስመር ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥትን በመወከል በስምምነቱ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ክቡር አቶ ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚን እንዳስታወቁት፣ ወደ ሰላም ስምምነቱ እንድረስ እንጂ አሁንም መጓዝ ያለብን ረጅም መንገድ አለ ብለው፣ ይህን መንገድ ስንጓዝ ብቻችን ሳትተውን ከጎናችን በመሆን ትብብራችሁን አሳዩን በማለት ቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበርን ተማጽነው ማሕበሩ ላበርከተላቸው የእስካሁን በጎ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በሮም የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ኢምፓሊያዞ በበኩላቸው፣ በደቡብ ሱዳን እርቅን እና ሰላምን ለማውረድ ማሕበራቸው የሚችለውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፣ በአካባቢው የተኩስ አቁም ስምምነትን ተግባራዊ የሚያደርግ፣ እውነተኛ መሠረት ያላቸውን የፖለቲካ ውይይቶች ለመጀመር የሚያስችሉ የጋራ ጉባኤ በቅርቡ የሚካሄድ መሆኑ ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 January 2020, 16:08