ፈልግ

በሊቢያ ውስጥ ስደተኞች ያለ ምንም ክፍያ የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ ይገደዳሉ፣ በሊቢያ ውስጥ ስደተኞች ያለ ምንም ክፍያ የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ ይገደዳሉ፣  

በሊቢያ ውስጥ የስደተኞች ሁኔታ እየከፋ መምጣቱ ተነገረ።

ከትውልድ አገራቸው ተነስተው ሊቢያን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመድረስ በጉዞ ላይ የሚገኙ በርካታ ስደተኞች መኖራቸው ታውቋል። ባሁኑ ጊዜ በሊቢያ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ በርካታ የልዩ ልዩ አገሮች ስደተኞች የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል። በሊቢያ ውስጥ ከሚገኙ ስደተኞች መካከል ከአሥሩ ውስጥ አንዱ በስደተኞች ማጎሪያ ውስጥ፣ የተቀሩት አነሰተኛ ክፍያ እየተደረገላቸው አልያም ያለ ምንም ክፍያ የጉልበት ሥራ እየሰሩ መኖራቸ ታውቋል። ከዚህም ሌላ በታጣቂዎች እጅ የገቡ እንደሆነ እንዲያበረክቱ በሚገደዱበት ማንኛውም ዓይነት አገልግሎት የሚሰማሩ መሆናቸውን በጣሊያን የ“ኮሪዬረ ዴላ ሴራ” ዕለታዊ ጋዜጣ ክፍል ልዑክ፣ ፍራንችስኮ ባቲስቲኒ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለሥራ ጉዳይ ወደ ሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ ደርሰው የተመለሱት አቶ ፍራንችስኮ ባቲስቲኒ እንዳታወቁት የጉዞ መስመር  ተዘግቶባቸው ሊቢያ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ስደተኞች በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸው፣ እስካሁን በሊቢያ ውስጥ እንደ ስደተኛ ተመዝግበው የሚገኙ በቁጥር ወደ 7000 የሚጠጉ መኖራቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ መካከል በሊቢያ መንግሥት እና በሚሊሺያ በሚመሩ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ወደ 6000 የሚሆኑ ስደተኞች መኖራቸውን ያስታወቁት አቶ ፍራንችስኮ ባቲስቲኒን የተቀሩት ደግሞ በሊቢያ ከተሞች ውስጥ በመዘዋወር፣ ከባድ እና ክፍያቸው በጣም አነስተኛ በሆኑ የጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መሆናቸውን አስረድተው አንዳንድ ጊዜ ምንም የማይከፈላቸው መሆኑንም ገልጸዋል። ከስደተኞቹ መካከል አንዳንዶቹ ለሥራ በተሰማሩበት ነጻ ማደሪያ እና ቀለብ ተሰጥቶአቸው ነገር ግን ምንም የገንዘብ ክፍያ የማይድረግላቸው እንደሆነ መናገራቸውን አቶ ፍራንችስኮ ባቲስቲኒ ገልጸው በሊቢያ ውስጥ ከሚገኘው ስደተኛ ዜጋ መካከል ከፍተኛ ቁጥር የያዘው ከሰሃራ በታች ካሉት አገሮች የመጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ሃቁ ሲዳሰስ፣

በጣሊያን የ“ኮሪዬረ ዴላ ሴራ” ዕለታዊ ጋዜጣ ክፍል ልዑክ፣ ፍራንችስኮ ባቲስቲኒ በሊቢያ ውስጥ በመንግሥት ወታደሮች እና በአማጺው ታጣቂ ቡድን መካከል የሚደረግ ጦርነት የቀጠለ መሆኑን ገልጸው፣ የተኩስ አቁም ስምምነቶች መጣሳቸውን፣ በጀኔራል ሃፍታር ታማኝ ወታደሮች በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሕጻናት እና አዋቂዎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን፣ በትሪፖሊ ደቡባዊ ክፍለ ከተማ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን ተናግረዋል። “ሊቢያ ኦብዘርቨር” ጋዜጣን ዋቢ በማድረግ የተናገሩት አቶ ፍራንችስኮ ባቲስቲኒ፣ የጀኔራል ሃፍታር ወታደራዊ ኃይል ንብረት የሆነ አንድ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን በመንግሥት ወታደሮች በኩል በተሰነዘረው ጥቃት ተመትቶ መውደቁን ገልጸዋል።

ከቤርሊኑ ጉባኤ ማግሥት፣

ሊቢያን ያጋጠማትን የፖለቲካ ቀውስ አስመልክተው የሁለቱ አገራት መሪዎች፣ የሰሜን አሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቱርኩ አቻቸው፣ ታይፕ ኤርዶጋ በስልክ ሃሳባቸውን መለዋወጣቸው ታውቋል። ከ“ዋይት ሃውስ” የወጣው ዘገባ እንዳመለከተው ሁለቱም መሪዎች በሊቢያ በሚታይ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የውጭ መንግሥታት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም፣ በሊቢያ መንግሥት እና በአማጺ ወገን መካከል የሚደረስ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ዘላቂ እንዲሆኑ በሚሉ ሃሳቦች ላይ ወደ ስምምነት መድረሳቸው ታውቋል። በሌላ ወገን ሩሲያ በበኩሏ አስፈላጊ መስሎ ከታያት ለሊቢያ ወታደራዊ ኃይል እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን መግለጿ ሲነገር፣ ከሁለቱ ወገኖች ማለትም ከሊቢያ ብሔራዊ ጦር አባላት እና ትሪፖሊን ከሚቆጣጠር የሃፍታር ወታደራዊ ኃይል የተወጣጡ፣ ከእያንዳንዱ ወገን አምስት አባላትን የያዘ ቡድን በመጭው የካቲት ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በጄኔቭ የሚገናኙ መሆናቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
30 January 2020, 16:53