ፈልግ

የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አንቶኒዮ ጉቴረዝ በጀኔቭ በተካሄደው በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ጉባኤ ላይ፣ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አንቶኒዮ ጉቴረዝ በጀኔቭ በተካሄደው በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ጉባኤ ላይ፣ 

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰላም ግንባታ የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ መሆኑ ተነገረ።

የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አንቶኒዮ ጉቴረዝ “ላ ስታምፓ” ከተሰኘ የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰላም ግንባታ የሚያድረጉት ጥረት ከፍተኛ መሆኑን አስታወቁ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊው አክለውም ቅዱስነታቸው በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት፣ በአገሮች መካከል የሚደረገው ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ግንኙነት ማጠናከርን በተመለከተ፣ ይህን ዕቅድ ፍሬያማ ለማድረግ በአገሮች መካከል የልዩነት ግርግዳን በመገንባት ሳይሆን የአንድነት እና የመገናኛ ድልድይ በመገንባት መሆኑን በየጊዜው ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እስካሁን ላበረከቱት እና በማበርከት ላይ ለሚገኙት መልካም ተግባራት አድናቆትን በመስጠት ማመስገን እንደሚፈልጉ የገለጹት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ ቅዱስነታቸው ካተኮሩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድህነት ቅነሳን፣ ሁለ ገብ ማሕበራዊ ሕይወት፣ ስደት እና የጦር መሣሪያ ቅነሳን የሚሉ ቅድሚያ የሰጡባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መወያየት ከሚፈልጓቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ሌላው የሃይማኖት ነጻነትን የተመለከተ ሲሆን በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚታየው ውጥረት፣ የሚከተሉትን እምነት በመጻረር በሰዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እጅግ ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል። በተለያዩ አገሮች ውስጥ በሚገኙ የአምልኮ ሥፍራዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን ያስታወሱት የተባበሩት  መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክብር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ የሰው ሕይወት የጠፋበት የኒውዚላንድ መስጊድ ጥቃት፣ በሰሜን አሜሪካ በሚገኝ የአይሁድ ምኩራብ ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ በስሪላንካ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ላይ የተፈጸመ ጥቃት አስታውሰዋል። የሐይማኖት ነጻነቶች እንዲከበሩ በማለት በቅርቡ ማሳሰባቸውን የተናገሩት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ በሕይማኖት ተቋማት መካከል የሚታየውን የጥላቻ መንፈስ ማርገብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል። የእምነት ሥፍራዎች ሰላማዊ እና ጸጥታቸውም የተከበር መሆን እንዳለበት የገልጹት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማትን በማስተባበር በመካከላቸው መቻቻል እና ሕብረት እንዲኖር ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ከጥር 26/28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተሰበሰቡበት ጉባኤ ላይ ታሪካዊ ነው የተባለለት የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ተሰጋጅቶ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም በሆኑት በዶክተር አህመድ ሞሐመድ አህመድ ኤል ጣይብ መካከል ተፈርሞ መጽደቁ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የሐይማኖት ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት መግባባት እና መቻቻል ያለበት እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል። ዋና ጸሐፊው ከዚህ ጋር በማያያዝ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚታየውን የጥላቻ መንፈስ ለማስወገድ ማስተማር እና ግንዛቤን ማስጨበጥ የድርጅታቸው አቋም መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓለማችን ውስጥ እያደገ የመጣውን የስደት ቀውስ ያስታወሱት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ ባሁኑ ጊዜ ከ70 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በስደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው ይህም ከሃያ ዓመት በፊት ከተመዘገበው የስደተኛ ቁጥር 2.3 ሚሊዮን በልጦ መገኘቱን ገልጸዋል። ለዚህ ቀውስ ተጠቃሽ ምክንያት በአገሮች ውስጥ የሚቀሰቀሱ አመጾች እና ጦርነቶች መሆናቸውን ጠቅሰው በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች መሳፋፋት እና የምግብ አቅርቦት ማነስ ለሕዝቦች መሰደድ አስተዋጽዖ ማድረጉን አስረድተዋል። ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለማገዝ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የገባውን ቃል ኪዳን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረው በንጹሐን ዜጎች ሕይወት መጥፋት በርካታ ወንጀለኞች ሃብት የሚሰበስቡ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ለስደት የሚዳርጉ ማሕበራዊ ችግሮችን ለይቶ በማወቅ በስደተኞች ላይ የሚደርስ የሞት አደጋን ማስወገድ የሚቻለው በሕዝቦች መካከል የሚቀሰቀሱትን አመጾች በመቀነስ እና ማሕበራዊ እድገትን ሊያመጡ የሚችሉ ውጥኖችን ተግባራዊ በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

በቅርቡ በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ የተካሄደውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ያስታወሱት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በተለይም በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች የካርቦን ልቀትን እስከ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2050 ዓ. ም. ድረስ ለመቀነስ መስማማታቸውን አስታውሰዋል።

በአንድ ወገን በዓለማችን ውስጥ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች መካከል መጠቃቀም እና መረዳዳት መኖሩን የገለጹት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊው በሌላ ወገን በአገሮች መካከል የሚታዩ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ልዩነቶች ክፍፍል መፍጠሩን አስታውሰው ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆኑ ሁለት አገሮችን፣ እነርሱም የቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ መንግሥት እና ሰሜን አሜርካን ጠቅሰዋል። በእነዚህ ሁለት በኤኮኖሚ በበለጸጉት አገሮች መካከል ያለው የንግድ እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ልዩነት እያደገ የሚመጣ ከሆነ ዓለማችን በሁለት ጎራ እንደሚከፈል እና ይህም በአገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ሊጎዳው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተመሠረተበት 75ኛ ዓመት በቅርቡ እንደሚከበር ያስታወሱት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ የክብረ በዓሉ ቀዳሚ ዓላማ የመንግሥታቱ ድርጅት እስካሁን ተግባራዊ ለማድረግ የጣራቸውን የሰላም ማስከበር፣ የማሕበራዊ እድገት እና የሰብዓዊ መብቶች ማስጠበቅ ጥረቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማሳሰብ ነው ብለዋል። መፍትሄን የሚሹ አዳዲስ ችግሮች መከሰታቸውን የገለጹት አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ ከእነዚህም መካከል የአየር ንብረት ቀውስ አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደንቦች እና መመሪያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያግዙ ዓለም አቀፍ መብቶች ጥበቃ መጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

ዋና ጸሐፊው በማከልም ድርጅታቸው ስር ነቀል ተሃድሶ እንደሚያስፈልገው ገልጸው በተባበሩት መግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከ75 ዓመት በፊት በተረቀቀው ደንብ እየተመራ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 December 2019, 16:17