ፈልግ

በኢንዶኔዢያ የሰብዓዊ መብት መከበር ጥያቄ ሲቀርብ፣             በኢንዶኔዢያ የሰብዓዊ መብት መከበር ጥያቄ ሲቀርብ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የሰው ልጅ ሁል ጊዜ ቅዱስ እና መብቱም የማይጣስ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት የተደነገገበት 71 ዓመት ምክንያት በማድረግ የትዊተር መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው የሰው ልጅ ሁል ጊዜ ቅዱስ እና መብቱም የማይጣስ መሆኑን ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ71ኛ ጊዜ የሚከበረውን ሰብዓዊ መብት ድንጋጌን በማስመልከት ከአሚኔስቲ ኢንተርናሽናል ቃል አቃባይ ከሆኑት ከአቶ ሪካርዶ ኑሪ ጋር የቫቲካን ሬዲዮ ቃለ ምልልስ ማድረጉን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ አንቶኔላ ፓሌርሞ የላከችልን ዘገባ አሳታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ በማንኛውም ጊዜ እና የዕድገት ደረጃ ውስጥ “የሰው ልጅ ሁል ጊዜ ቅዱስ እና መብቱም የማይጣስ ነው” ብለው ይህ ውሳኔ ውድቀት የሚያጋጥመው ከሆነ ግን ለደህንነቱ ጠንካራ እና ዘላቂ መሠረቶች አይኖሩትም ብለዋል። የቅዱስነታቸውን ጥሪ መሠረት በማድረግ በሰጡት አስተያየታቸው በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ እና ከለላ ያልተደረገላቸው ሰዎች ሰብዓዊ መብት ማስጠበቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በጣሊያን የአሚኔስቲ ኢንተርናሽናል ቃል አቃባይ የሆኑት አቶ ሪካርዶ ኑሪ ለቫቲካን ሬዲዮ ገልጸዋል። ቃል አቃባዩ አክለውም በዓለም ዙሪያ ሰብዓዊ መብታቸውን ለማስከበር የሚታገሉ የወንዶች እና የሴቶች ማሕበራት ጥረት፣ የሰብዓዊ መብት የተደነገገበትን ዋና ዓላማ ከሚገልጽ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድምጽ ጋር የሚተባበር እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ወጣቱ ትውልድ ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር እንዲነሳሱ ያስፈልጋል፣

የሕጻናትን መብት የሚያስጠብቅ ሕግ የተደነገገበት 30ኛ ዓመት በተከበረበት ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ ጥቅምት 20/2019 ዓ. ም. ማሕበራዊ እና ኤኮናሚያዊ ለውጦችን ለማምጣት ወጣቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ መጠቀሱ ይታወሳል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አንቶኒዮ ጉቴረዝ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው ወጣቶች ለመብታቸው፣ ለሰላም፣ ለፍትሕ እና ለእኩልነት የበኩላቸውን አስተዋጽዖን እንዲያደርጉ ማበረታታት ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ በመልዕክታቸው በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ወጣቶች ተደራጅተው ወደ አደባባይ በመውጣት ለሰብዓዊ መብታቸው፣ ለእኩልነታቸው፣ ለወጣት ሴቶች መብት መከበር፣ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ በብቃት እንዲሳተፉ እና ሃሳባቸውንም በነጻነት የሚገልጹበት መድረክ ሊኖር ይገባል ማለታቸው ይታወሳል። እያንዳንዱ ሰው ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ እና ባሕላዊ መብቱን መጠቀም አለበት ማለታችው ታውቋል። የሚኖርበት አገር፣ ዘር፣ ሐይማኖት፣ ጾታ፣ የፖለቲካ አቋም፣ የአካል ብቃት እና የገቢ መጠን ልዩነቶች ሳያግዱት መብቱን ማስጠበቅ መቻል አለበት ማለታቸው ታውቋል።

ጉዳት የደረሰባቸው የማሕበረሰብ ክፍሎች፣

በከፍተኛ ማሕበራዊ ችግር ውስጥ በተለይም አመጽ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙትን ሕጻናት ያስታወሱት፣ በጣሊያን የአሚኔስቲ ኢንተርናሽናል ቃል አቃባይ ክቡር አቶ ሪካርዶ ኑሪ በዘመናችን ያጋጠሙንን ሦስት ማሕበራዊ ቀውሶች ሲይሳታውሱ እነርሱ፣ በየቦታው የሚከሰቱ አመጾች፣ የሕዝቦች መሰደድ እና የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ሪካርዶ ኑሪ በማከልም እነዚህ ማሕበራዊ ቀውሶች ምንም ዓይነት ጥፋት የሌለባቸውን የማሕበረሰብ ክፍሎችን ከእነዚህም መካከል ሕጻናትን እና ሴቶችን የሚያጠቃ መሆኑን አስታውቀው፣ በመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች ውስጥ የሚቀሰቀሰው አመጽ እና ጦርነት ድርጅታቸውን ማሳሰቡን ገልጸዋል።

ሰብዓዊ መብት ማስከበር ሂደት ገና ብዙ ይቀረዋል፣

ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበት እስካሁን ከተደረጉት ጥረቶች በላይ ወደ ፊት የሚሠሩ ሥራዎች ብዙ ናቸው በማለት ያስታወቁት ክቡር አቶ ሪካርዶ ኑሪ ሰብዓዊ መብትን ማስከበት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸው፣ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ከተደነገገበት ከጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1948 ዓ. ም. ወዲህ አንዳንድ እድገቶች የታዩበት መሆኑ ቢታወቅም በብዙ አገሮች ዘንድ ሰብዓዊ መብት እየተከበረ አይደለም በማለት ተናግረዋል። በተለይ በኤኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ዘርፎች ብዙ ሥራ እንዲሠራ ይጠበቃል ያሉት አቶ ሪካርዶ በእነዚህ ዘርፎች ላይ ለውጥ እንዲታይ የሚጠይቁ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በኢራቅ፣ ኢራን፣ ሊባኖስ፣ ቺሊ እና ሆንግ ኮንግ ላይ በመደረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ልዩነቶች እና ጥላቻ በተስፋፋበት አውሮፓ ውስጥም የሰብዓዊ መብቶች ጥያቄ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
11 December 2019, 14:43