ፈልግ

አካባቢን ከጸረ ሰው ፈንጂ መሣሪያ ነጻ የማድረግ ጥረት፣             አካባቢን ከጸረ ሰው ፈንጂ መሣሪያ ነጻ የማድረግ ጥረት፣  

ሰባት ሺህ ያህል ሰዎች በጸረ ሰው ፈንጂ መሣሪያ አደጋ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በዓለማችን፣ በሃምሳ አገሮች ውስጥ በተካሄደው አሰሳ ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በጸረ ሰው ፈንጂ አደጋ መሞታቸውን በጎርጎሮሳውያኑ 2019 ዓ. ም.  በጄኔቫ እና በኦስሎ የቀረቡት ሪፖርቶች አመልክተዋል። ሪፖርቶቹ ከሃያ ዓመት በፊት በካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ የተደረሰውን የጸረ ሰው ፈንጂ መሣሪያዎች እቀባ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰዱትን እርምጃዎች የሚገልጽ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሪፖርቱ እንደገለጸው የሰላም ስምምነቶችን መፈራረም ይቻላል፤ የተኩስ አቁም ስምምነቶችንም መፈራረም ይቻላል። ነገር ግን መሬት ውስጥ ተቀብረው የሚቀሩት ፈንጂዎች የጦርነቶች እና የግጭቶች ቀጣይ ቅርሶች ሆነው ይቆያሉ ብሏል። ከሃያ ዓመት በፊት በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር መጋቢት 1/1999 ዓ. ም. በካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ የተደረሰው ዓለም አቀፍ ስምምነት የጸረ ሰው ፈንጂዎች ምርት እና ሽያጭ  የሚያግድ መሆኑ ይታወሳል።

የኦታዋን ስምምነት 164 አገራት ሲያጸድቁት 33ቱ አልተቀበሉትም፣

የኦታዋን ስምምነት 164 ሃገራት ያጸደቁ መሆናቸውን የገለጸው ሪፖርቱ በስምምነቱ ላይ ያልተገኙ ሰሜን አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ እስራኤል፣ ኢራን፣ ግብጽ፣ ሳውድ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሲሆኑ በጠቅላላው 33 አገሮች ስምምነቱ ላይ እንዳልተገኙ ሪፖርቱ አስታውቋል።

ስምምነቱ የጸረ ሰው ፈንጂዎች ምርት፣ ግብይት እና ክምችትን ይከለክላል።፣

የኦታዋው ስምምነት በእያንዳንዱ አገር የጸረ ሰው ፈንጂዎች እንዳይመረቱ፣ ገበያ ላይ እንዳይውሉ እና እንዳይከማቹ ከመከልከልም በላይ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በማብራራት ለየአገራቱ በቂ መረጃ እንዲደርስ የሚጠይቅ ሲሆን በተጨማሪም በአደጋው ለተጠቁት ሰዎች የካሳ ክፊያ እንዲሰጣቸው የሚያዝ መሆኑ ታውቋል።

ሰዎች አጠገብ የሚፈነዱ የጦር መሣሪያዎች፣

ጸረ ሰው ፈንጂ መሣሪያዎች በአካባቢያቸው ሰው ወይም መኪና ሲያልፍ በፍጥነት በቀላሉ በመፈንዳት ጉዳት የሚያደርሱ ሲሆን ብዙን ጊዜ የአደጋው ተጠቂዎች የሚሆኑት ሕጻናትን እና ወታደሮች መሆናቸው ታውቋል። እነዚህ ጸረ ሰው ፈንጂዎች በተቀበሩበት ቦታ ለአሥራዎች ዓመታ የሚቆዩ መሆናቸው ታውቋል።

ንጹሃን ዜጎች ይጠቃሉ፣

ጸረ ሰው ፈንጂዎች ብዙን ጊዜ በንጹሃን ዜጎች ላይ አደጋን እንደሚያስከትሉ የገለጸው ሪፖርቱ የሚገኙትም ሰዎች በሚረማመዱበት መንገድ፣ በእርሻ ውስጥ፣ በጫካዎች፣ በረሃማ አካባቢዎች እና በድንበሮች አካባቢ የሚገኙ ሲሆን ይህም ሰዎች ዕለታዊ ተግባሮቻቸውን እንዳያከናውኑ ያግዳሉ በማለት ሪፖርቱ አስታውቋል።

60 አገሮች በጸረ ሰው ፈንጂዎች ተበክለው ይገኛሉ፣

ዓመታዊ ሪፖርቱ እንደገለጸው እስከ ዛሬ በጸረ ሰው ፈንጂዎች የተበከሉ አገሮች 60 እንደሆኑ ገልጾ ከእነዚህም መካከል 34ቱ የኦታዋ ስምምነትን የፈረሙ፣ 22ቱ ስምምነቱን ለመፈረም ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ እና የተቀሩት 4ቱ በስምምነቱ ወቅት ያልተገኙ መሆናቸው ታውቋል። ጸረ ሰው ፈንጂዎች በብዛት የሚገኙባቸው አገሮች አፍጋኒስታን፣ አዘርባዣን፣ አንጎላ፣ ቦስኒያ፣ ኤርዞጎቪና፣ ካምቦዲያ፣ ቻድ፣ ክሮዋሺያ፣ ኢራቅ፣ ምዕራብ ስሃራዊ፣ ታይላንድ፣ ቱርክ እና የመን መሆናቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።

በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. ሦስት ሺህ ሰዎች ሞተዋል፣ አራት ሺህ የሚጠጉ ቆስለዋል፣

በጸረ ሰው ፈንጂ መሣሪያ የሚሞት የሰው ቁጥር በአራት አመት ውስጥ ከፍ ማለቱን የገለጸው ዓመታዊ ሪፖርት ባለፈው የጎርጎሮሳዊው ዓመት ብቻ 3,059, የቆሰለው የሰው ቁጥር 3,837, በጠቅላላው 6,897 ሰዎች የአደጋው ሰለባ መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 November 2019, 15:52