ፈልግ

በጦርነት የተጠቁ የጋዛ አካባቢ ሕጻናት፣            በጦርነት የተጠቁ የጋዛ አካባቢ ሕጻናት፣  

“ዩኒሴፍ” የ40 ሚሊዮን ሕጻናት ሕይወት ከሞት ለማትረፍ ጥሪ አቀረበ።

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በተፈጥሮ አደጋ እና በጦርነት በተጠቁ ሀገሮች ለሞት አደጋ የተጋለጡ 40 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናትን ሕይወት ለማትረፍ ይቻል ዘንድ የእርዳታ ጥሪ አቀረበ። የሕጻናት መርጃ ድርጅት ለሕጻናት ተብለው የተነደፉ የዕርዳታ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግለት በማለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መጠየቁን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ሮቤርታ ጂሶቲ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ በማከልም በ59 አገሮች ውስጥ የሚገኙ 41 ሚሊዮን ሕጻናት ተፈጥሮ ባስከተለው አደጋ፣ በአመጾች እና በጦርነቶች የተጠቁ መሆናቸውን አስታውቆ በእነዚህ አገሮች ውስጥ በሚኖሩ ሕጻናት ላይ የሚደርሱትን ችግሮች ለማቃለል ከተጠየቀው የገንዘብ መጠን ግማሹን ብቻ ከለጋሽ አገሮች ያገኘ መሆኑን ገልጿል።

የቀረውን የእርዳታ መጠን ለማሰባሰብ የሶስት ወር ጊዜ፣

በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ. ም. ለማሰባሰብ የታቀደው የገንዘብ መጠን 4.16 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ያስታወቀው የሕጻናት መርጃ ድርጅት የተፈጥሮ አደጋ እና ጦርነት በበዛባቸው አገሮች ውስጥ ለሚገኙ ሕጻናት የጤና፣ የትምህርት፣ የተመጣጣኝ ምግብ አቅርቦት እና ከአደጋ የመከላከል አገልግሎትን ለማዳረስ የሚያግዝ መሆኑን ገልጾ እስካሁን ሊገኝ የቻለው የዕርዳታ መጠን ግማሽ ከመቶ ብቻ መሆኑ አስታውቋል። የሕጻናት መርጃ ድርጅት ከዚህ ጋር በማማያዝ እንዳስታወቀው የተቀረውን የእርዳታ መጠን ለማሰባብሰብ የቀረው ጊዜ ሦስት ወር ብቻ መሆኑን ገልጿል። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ስደተኞች እና ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን አገሮች ሲዘረዝር፣ በእስያ፣ በፓክስታን፣ በሶርያ እና በአጎራባች አገሮች ውስጥ 2.5 ሚሊዮን ስደተኞች እና ተፈናቃዮች የሚገኙ መሆኑን አስታውቆ፣ በቱርክ፣ በሊባኖስ፣ በዮርዳኖስ፣ በኢራቅ፣ በግብጽ፣ በየመን፣ በባንግላዲሽ፣ በአፍሪቃ ውስጥ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፣ በካሜሩን፣ በቡርኪና ፋሶ፣ በኢትዮጵያ፣ በሊቢያ፣ በናይጄሪያ፣ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን፣ በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ በሃይቲ፣ በቨነዙዌላ መኖራቸውን አስረድቷል።

የሕጻናትን መሰረታዊ ጥያቄዎችን መመለስ፣

በሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት የሚጎሳቆሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት በዓለማችን እንድሚገኙ፣ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሄንሬታ ፎሬ አስገንዝበዋል። በቂ እርዳታ ካልተደረገላቸው በቀር እነዚህ ሕጻናት ትምህርታቸውን መከታተል እንደማይችሉ፣ በቂ ሕክምናን እና ተመጣጣኝ ምግብ እንደማያገኙ፣ ለአመጽ እና ለጥቃት የተጋለጡ መሆናቸውን አስረድተዋል። ግጭቶችን እና ጦርነቶችን ለማስወገድ ከሚደረጉት ጥረቶች በተጨማሪ ለሕጻናት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማቅረብ እርዳታ ለጋሽ አገሮች እና ድርጅቶች እገዛ እንደሚያስፈልግ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሄንሬታ ፎሬ አስገንዝበዋል።

የሕጻናት መብት ድንጋጌ 30ኛ ዓመት፣

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እንዳስታወቀው በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት፣ የአዳጊ ወጣቶች መብት ድንጋጌ ከጸደቀ 30 ዓመት ሊያስቆጥር መቃረቡን አስታውቆ፣ በበርካታ አገሮች ዘንድ የሕጻናት እና አዳጊ ወጣቶች መብት በተግባር እንዳልተገለጸ፣ የማሕበራዊ ሕይወት መሻሻልም ያልታየ መሆኑን ድርጅቱ አስረድቷል፣  

የተደረሱ ግቦች እና ገና ተግባራዊ የሚደረጉ ግቦች፣

ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ዕድሜ ያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆናቸው ሕጻናት ሞት 50 ከመቶ በላይ መቀነሱ እና ለሕጻናት የሚቀርብ የተመጣጣኝ ምግብ እጥረትም እንደዚሁ መቀነሱ ታውቋል። አሁንም በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ ያስታወቀው የሕጻናት መርጃ ድርጅት 262 ሚሊዮን ሕጻናት እና አዳጊ ወጣቶች የትምህርት ዕድል እንዳላገኙ፣ 650 ሚሊዮን አዳጊ ወጣቶች 18 ዓመት ዕድሜ ሳይሞላቸው ወደ ትዳር ዓለም እንደሚገቡ፣ ከ4 ሕጻናት መካከል አንዱ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2040 ዓ. ም. ድረስ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ የማያገኝ መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት አስታውቋል።    

23 October 2019, 15:32