ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት፤ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት፤ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ የ2019 ዓ. ም. የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።

በኖርዌይ የሚገኘው የኖቤል የሠላም ሽልማት ኮሚሽን ይህን ከፍተኛ ሽልማት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ለመስጠት የውሰነው በተለይም ከጎረቤት አገር ከሆነች ኤርትራ ጋር የነበረው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ላደረጉት ጥረት መሆኑን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ዘጋቢ ፌደሪኮ ፍራንቸስኮኒ የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚሽን በቲዊተር ድረ ገጹ ይፋ ባደረገው መልዕክቱ እንዳስታወቀው ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ የተሰጠው የ2019 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሽልማት ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ እርቀ-ሰላም እንዲሁም በምስራቅ እና በሰሜን ምስራቅ የአፍሪቃ አገሮች ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ጥረት ላደረጉት በሙሉ እውቅና መስጠቱን አስታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ1998 እስከ 2000 ዓ. ም. በጦርነት ውስጥ የነበሩትን እና እስካለፈው ዓመት ድረስ ተራርቀው የቆዩትን ኢትዮጵያን እና ኤርትራን ወደ ሰላም እና እርቅ ለማድረስ በሁለት አገሮች መሪዎች በኩል የተደረሰውን ስምምነት ኮሚሽኑ አስታውሷል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ጋር በቫቲካን በተወያዩበት ወቅት፤
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ጋር በቫቲካን በተወያዩበት ወቅት፤

ኮሚሽኑ በተጨማሪም አሁንም ቢሆን ብዙ ሥራ የሚጠብቃቸው ቢሆንም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በአገራቸው ከፍተኛ ለውጦችን ያስመዘገቡ እና ለበርካታ ዜጎቻቸው የመልካም ሕይወት ተስፋን፣ እርቅን፣ አንድነትን እና ማሕበራዊ ፍትህን በማምጣት ጉልህ ሚናን መጫወታቸውን አስታውቋል።

ከፋይል የተገኘ፤
ከፋይል የተገኘ፤

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ የ2019 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊነታቸው ሲነገራቸው ክብር የተሰማቸው መሆኑን ገልጸው የተሰጣቸው ሽልማትም “ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አፍሪቃ የተሰጠ ሽልማት ነው” ማለታቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ መሠረት ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ፣ ከክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ የድጋፍ እና እርካታቸውን የገለጡበት መልዕክት የተላከላቸው መሆኑን ገልጾ ጠቅላይ ጸሐፊው በማከልም “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ታሪካዊ ወዳጅነትን መልሶ ለመገንባት እገዛ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ አመራራቸው ለአፍሪቃ እና ለሌሎች አገሮች መሪዎች እጅግ መልካም ምሳሌ ሆኗል” ማለታቸውን አስታውቋል። ከአምነስቲ ኢጣሊያ ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ እንደዚሁ የአድናቆት መልዕክት የደረሳቸው ሲሆን ማሕበሩ የጀመሩትን በጎ ተግባር ማበርከታቸውን እንዲቀጥሉበት እና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የበለጠ መሥራት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን መጠየቁ ታውቋል።    

በብዙ ታዛቢዎች ዘንድ የዘንድሮን የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የመብት ተሟጋች የሆነችው ስዊድናዊቷ የ16 ዓመት ታዳጊ፣ ግሬታ ተንበርግ እንደምትሆን ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል አንዷ የነበረች ብትሆንም ኮሚሽኑ የበኩሉን አስተያየት ከመስጠት መቆጠቡ ታውቋል። የኖቤል የሠላም ሽልማት አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዚደንት አቶ ቤሪት ሬይስ አንደርሰን ሲናገሩ “ሽልማቱ ሲገባቸው ነገር ግን ሳይወስዱ የሚቀሩ ሰዎችን በተመለከተ የምንሰጠው ምንም አስተያየት አይኖረንም” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከኤርትራ ጋር ካደረጉት የሰላም ስምምነት ባሻገር ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ከመድረሳቸው አስቀድመው በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ያመጣሉ ተብሎ በብዙ ታዛቢዎች ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለባቸው የ43 ዓመት ዕድሜ ወጣት መሆናቸው ታውቋል። የፖለቲካ እስረኞችን መፍታታቸው፣ በባዕድ አገር ለቆዩት እና እንደ አሸባሪ ይቆጠሩ ለነበሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እና ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እውቅናን በመስጠት ወደ አገራቸው እንዲገቡ ማድረጋቸው፣ በገዛ ፓርቲያቸው ውስጥ የተስፋፋውን ሙስና ማጋለጣቸው፣ የአገሪቱን የኤኮኖሚ ስርዓት ለማሻሻል ጥረት ማድረጋቸው እና ሌሎችንም በርካታ የተሃድሶ እርምጃዎችን መውሰዳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ካደረጓቸው ጥረቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
12 October 2019, 08:51