ፈልግ

በአውሮጳ ውስጥ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ታስቦ ዋለ።

ከስድስት ዓመት በፊት፣ መስከረም 23/2006 ዓ. ም. የሜዲቴራኒያንን ባሕር ለመሻገር ሲሞክሩ የሞቱትን 363 ስደተኞች በማስታወስ ትናንት ሐሙስ መስከረም 23/2012 ዕ. ም. ብሔራዊ የሐዘን ቀን ታስቦ መዋሉ ታውቋል። ዕለቱ የሐዘን ቀን መታሰቢያ ሆኖ እንዲውል በአውሮጳ አገሮች ከታወጀበት ከስድስት ዓመት ወዲህ የሜዲቴራኒያንን ባሕር ለመሻገር ሲሞክሩ የሞቱት የስደተኞች ቁጥር ከ 15,000 በላይ መድረሱን የስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለከተ መሆኑን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ ሊንዳ ቦርዶኒ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዕለቱ በደረሰው አደጋ የሞቱት ስደተኞች ትክክለኛ ቁጥር እስካሁን በውል ባይታወቅም የ194 ስደተኞች አስከሬን ከባሕር ሊገኝ እንደተቻለ፣ የ363 ስደተኞች አስከሬን ያልተገኘ መሆኑ ተነግሯል። ይህን ያህል ቁጥር በመጫን ይጓዝ የነበረ መጠነኛ ጀልባ፣ ወደ ኢጣሊያ የወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ላምፔዱሳ ለመድረስ እንደነበር ይታወሳል።

ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይደገም፣

የአውሮጳ አገሮች በጋራ ሆነው ባስተላለፉት ውሳኔ ይህን የመሰለ አደጋ በስደተኞች ላይ እንዳይደገም በማለት፣ በተከሰተው አደጋም የተሰማቸውን ሐዘን በገለጹበት ዕለት፣ መስከረም 23 ቀን የአደጋው ሰለባ የሆኑ ስደተኞች መታሰቢያ ብሔራዊ ቀን እንዲሆን መወሰናቸው ይታወሳል። ያም ሆኖ በስደተኞች ላይ እጅግ አሳዛኝ የሆነ አደጋ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሜዲተራኒያን ባሕር ላይ በደረሱት አደጋዎች 15, 000 ስደተኞች ሕይወታቸውን እንዳጡ፣ ከእነዚህም መካከል 678ቱ ሕጻናት መሆናቸውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣

የስደተኞችን ጉዳይ በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሃገራት መሪዎች እና ሕግ አውጪ ክፍሎች ሃላፊነትን እንዲወስዱ፣ ከትውልድ አገራቸው ለመሸሽ የሚገደዱ ሰዎች ደህንነቱ በተጠበቀ የመተላለፊያ መንገዶች ወደሚፈልጉት አገር የሚጓዙበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ እና በሚደርሱበት አገርም መልካም መስተንግዶ ተደርጎላቸው አስፈልጊው እገዛ እንዲደረግላቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ዘንድሮ በተከበረው 105ኛ ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ባሰሙት ንግግር በአንዳንድ አገሮች በመካሄድ ላይ ያሉትን ጦርነቶች በጦር መሣሪያ ምርት እየደጎሙ ያሉት አግሮች በጦርነቱ ምክንያት የሚፈናቀሉትን እና የሚሰደዱትን አቅመ ደካሞች፣ እናቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶችን ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኞች ሆነው አልተገኙም ማለታቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መስከረም 18/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ እንዳስገነዘቡት “ባልንጀራን መውደድ ማለት የሚደርስላቸውን አጥተው በየመንገዱ ወድቀው ችግር ላይ ለሚገኙት በሙሉ የእርዳታ እጆቻችንን መዘርጋት እንደ ሆነ አስረድተዋል። የአውሮጳ አገሮች አደጋው ከተከሰተበት ከስድስት ዓመት ወዲህ ተጨማሪ አደጋ በሜዲቴራኒያን ባሕር በሚከሰትበት ጊዜ ሕይወትን ከማዳን ይልቅ ድንበሮቻቸውን መዝጋትን መምረጣቸው ታይቷል።

የማልታው ጉባኤ፣

በቅርቡ በማልታ የተካሄደው የአውሮጳ አገሮች ጉባኤ በታሪክ ለመጀመሪያ ሃላፊነትን በጋራ ወስደው፣ የአውሮጳ ሕብረት የፍትህ እና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ምክር ቤት የሚያስቀምጣቸውን ደንቦች ተፈጻሚ ለማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችንም ተግባራዊ ለማድረግ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሰብዓዊ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የነፍስ አድን አገልግሎታቸውን በስፋት ለማከናወን   ውሳኔ ላይ መደረሳቸው ይታወሳል። 

04 October 2019, 16:43