ፈልግ

ኤል-ፓሶ ከተማ በሚገኝ የገበያ ማዕከል የከፈተው ተኩስ ተቃውሞ፣ ኤል-ፓሶ ከተማ በሚገኝ የገበያ ማዕከል የከፈተው ተኩስ ተቃውሞ፣ 

የአሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ሕዝቡ ጥላቻን እና ዘረኝነትን ከሚቀሰቅሱ ንግግሮች እንዲቆጠብ አሳሰቡ።

በሰሜን አሜሪካ ሕዝቦች መካከል ዘረኝነትን እና ጥላቻን የሚዘሩ ጽሑፎች እና ንግግሮች እየተስፋፉ መምጣታቸው ያሳሰባቸው የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ሕዝቡ ከዚህ አደገኛ መንገድ እንዲመለስ አሳስበዋል። ሰሞኑን በሁለት የሰሜን አሜሪካ ከተሞች፣ ማለትም በማዕከላዊ ምዕራብ ኦሃዮ ግዛት በሆነችው በዴይተን እና በደቡባዊ ቴክሳስ ግዛት፣ ኤል-ፓሶ ከተማ በተከፈተው የተኩስ ጥቃቶች የ31 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ዋና ምክንያቱ፣ በሕዝቡ መካከል ጥላቻን እና ዘረኝነትን የሚያንጸባርቁ ጽሑፎች እና ንግግሮች በመብዛታቸው ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የ21 ዓመት ዕድሜ ወጣት፣ ሐምሌ 27/2011 ዓ. ም. በደቡባዊ ቴክሳስ ግዛት፣ ኤል-ፓሶ ከተማ በሚገኝ አንድ የገበያ ማዕከል ውስጥ በከፈተው ተኩስ የ22 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የሳታወሱት የብጹዕ ጳጳሳት ጉባኤ ሦስት ኮሚሲዮኖች ሊቃነ መናብርት በመግለጫቸው እንዳስታወቁት “በሕዝቡ መካከል የተሰራጩ እና ጥላቻን የሚቀሰቅሱ ሀሳቦች እና ጽሑፎች ለአንዳንድ የጥቃት ድርጊቶች ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል።

የጥላቻ ንግግሮች የሚያስከትሉት መዘዞች፣

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በተጨማሪም በመጨረሻዎቹ ዓመታት በስደተኞች፣ በጥገኝነት ጠያቂዎች፣ በሙስሊሞች እና በአይሁዶች ላይ የሚነሱ የቅራኔ ስሜቶች በአሜሪካ ሕዝብ መካከል የጥላቻ ስሜት እንዲያድግ ማድረጋቸውን አስረድተዋል። በቴክሳስ ግዛት፣ ኤል-ፓሶ ከተማ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ውስጥ በተከፈተው ተኩስ ለሞቱት 22 ሰዎች እና በ2007 ዓ. ም. ፒትስቡርግ በሚገኝ ምኩራብ ለተፈጸመው ግድያ ምክንያቱ የጥላቻ እና የዘረኝነት ንግግሮች መስፋፋታቸው ነው ብለዋል።

ከፋፋይ የሆኑ የጥላቻ ንግግሮች ስብዕናን ይቀንሳል፣

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ለአገሩ የፖለቲካ ባለስልጣናት እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው በሙሉ ባቀረቡት መልዕክታቸው፣ በሕዝቡ መካከል በሚንጸባረቅ ዘረኝነት እና የሃይማኖት ግትርነት ምክንያት የተፈጠርው ቁስል በአስቸኳይ የሚፈወስበትን መንገድ እንዲገኝ አሳስበዋል። ዘርን ፣ ሃይማኖትን እና ጎሳው መሠረት ያደረጉ ከፋፋይ የጥላቻ ንግግሮች እና ጽሑፎች ብጥብጥን ስለሚቀሰቅሱ ሕዝቡም ከዚህ መቆጠብ እንዳለበት አሳስበዋል።

የተባበረ እና እንግዳ ተቀባይ መሆን ያስፈልጋል፣

የጥላቻ ንግግሮች እና ጽሑፎች ወደ አመጽ የሚመሩ መሆናቸውን ያስረዱት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች እና መላው የሰሜን አሜሪካ ሕዝብ በጋራ በመሥራት የእንግዳ ተቀባይነት ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የሜክሲኮ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት አቤቱታ፣

የሜክሲኮ ካቶሊካዊ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳትም በበኩላቸው በሰሜን አሜሪካ በተከሰተው የሰው ሕይወት መጥፋት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፣ በአገሩ እየተስፋፋ የመጣው የዘረኝነት እና የጥላቻ ንግግር ቅራኔን እና አመጽን የሚፈጥር መሆኑን አስረድተው፣ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት፣ የሜክሲኮ እና የሰሜን አሜሪካ መንግሥታት፣ እንዲሁም ዜጎቻቸው በሙሉ ለሰላም ጠንክረው መሥራት ያለባቸው ጊዜ አሁን መሆኑን በመልዕክታቸው አስታውቀዋል። 

10 August 2019, 17:28