ፈልግ

በሱዳን የተቃውሞ ሰልፍ የሴቶች ተሳትፎ፣     በሱዳን የተቃውሞ ሰልፍ የሴቶች ተሳትፎ፣  

በሱዳን የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ውስጥ የክርስትና እምነት ተከታይ፣ አባል ሆና መመረጧ ተነገረ።

በሱዳን፣ በከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት እና በተቃውሞ ሰልፍ መሪዎች መካከል በተደረገው የስልጣን ክፍፍል፣ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥትን ለመምራት ከተመረጡት አስራ አንድ የምክር ቤት አባላት መካከል አንዷ የኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆኗ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አይሻ ሙሳ ሳኢድ ከሱዳን ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት አባል መካከል አንዷ ሆና የተመረጠችው ያለፈው ማክሰኞ መሆኑን የወታደራዊ ሽግግር መንግሥት ቃል አቃባይ አስታውቋል። የአይሻ ሙሳ ሳኢድ መመረጥን የምክር ቤቱ አባል በሙሉ የደገፉት ሲሆን ከአስራ አንድ የምክር ቤቱ አባላት መካከል ስድስቱ ከስቪል ማሕበረሰብ፣ አምስቱ ደግሞ ከሠራዊቱ ወገን መሆናቸው ታውቋል። አይሻ ሙሳ ሳኢድ ዳኛ እና በእንግሊዝ አገር በሚገኝ፣ ሊድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በትርጉም ሥራ ላይ ተሰማርታ የሠራች መሆኗ ታውቋል።

በሱዳን ውስጥ በግንቦት ወር በተደረገው የመንግሥት ለውጥ ፕሬዚደንት ኦማር አል በሽርን በመተካት አገሪቱን ሲያስተዳድር የቆየው ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት መሪ፣ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን፣ አሁን የተመረጠውን አዲስ ሉዓላዊ ምክር ቤትን ለሚቀጥሉት ሃያ ሁለት ወራት እንደሚመሩ፣ ከእርሳቸው ስልጣንን  የሚረከበው የስቪል ማሕበረሰብ ተወካይ ለተቀሩት 18 ወራት የሚመራ መሆኑ ታውቋል።

በተቃውሞ ወቅት የክርስቲያኖች ሚና፣

አዲስ በተቋቋመው ሉአላዊ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ውስጥ የክርስትና እምነት ተወካይ እንዲመረጥ የተደረገበት ምክንያት፣ በተቃውሞ ሰልፍ ወቅት የክርስቲያኖች ተሳትፎ እና ሚና ከፍተኛ እንደነበር ስለ ታመነበት ነው ተብሏል። በሱዳን ወታደሩ የአገር አስተዳደር ስልጣንን ከፕሬዚደንት ኦማር አልባሽር ከተረከበበት ከሚያዝያ 2/2011 ዓ. ም. አስቀድሞ የሱዳን የባለሞያዎች ማሕበር፣ ለዘመናት የስነልቦና ገደብ ተጥሎበት የተሰቃየው የሱዳን ክርስቲያን ማሕበረሰብ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርቦ እንደነበር ታውቋል። ይህን ተከትሎ በሱዳን የሚገኙ የፕሮቴስታንት ሐይማኖት መሪዎች ከሙስሊሙ ማሕበረሰ ጋር በመሆን በወታደራዊው ዋና ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት በመገኘት በጋራ መዘመራቸው የሚታወስ ነው።

የክርስቲያኖች ስደት በሱዳን፣

ፕሬዚደንት ኦማር አል በሽር በስልጣን በቆዩባቸው ሰላሳ ዓመታት ውስጥ፣ በአገርቱ የሚገኙ የክርስትያን ማሕበረሰብ ከፍተኛ ስቃይ እና ስደት ይደርስበት እንደነበር እና በዚህም ምክንያት መቀመጫውን በሰሜን አሜሪካ ያደረገው “ኦፐን ዶርስ” የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ ባለፈው ጎርጎሮርሳዊው 2018 ዓ. ም. በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጭቆናን እና ስቃይን ይፈጽማሉ ብሎ ከዘረዘራቸው አገሮች መካከል ሱዳንን በስድስተኛ ደረጃ ማስቀመጡ ይታወሳል።

ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ካረጋገጠች፣ እንደ ጎርጎሮርሳዊው አቆጣጠር ከ2003 ዓ. ም. በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የክርስትና እምነት ተከታዮችን ይዛ መለየቷ የሚታወስ ሲሆን ከዚያ በኋላ በሰሜን ሱዳን በቀሩት በቁጥር ጥቂት በሆኑ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ላይ የኦማር አል በሽር መንግሥት ከፍተኛ ተጽዕኖን ሲያደርግ መቆየቱ ታውቋል። በርካታ ቤተክርስቲያኖች ተቃጥለዋል፣ ብዙዎች ቤተክርስቲያኖች የታነጹት በሕገ ወጥ መንገድ ነው በመባል በመንግሥት ትዕዛዝ እንዲፈርሱ ተደርገዋል ተብሏል። እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር፣ ከ2005 ዓ. ም. ጀምሮ አዲስ ቤተክርስቲያን እንዳይታነጽ ተከልክሎ የቆየ መሆኑ ታውቋል።

ሱዳን ካላት 43 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 4.6 ከመቶ ወይም አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰባ ስምንት ሺህ የክርስትና እምነት ተከታዮች መሆናቸው ታውቋል።

22 August 2019, 15:35