ፈልግ

ጀኔራል ቪክቶር ፖግረብኒ፣ የሩስያ ጦር ሃይል አዛዥ ሆነው፣                                                                ጀኔራል ቪክቶር ፖግረብኒ፣ የሩስያ ጦር ሃይል አዛዥ ሆነው፣  

በሩስያ ኮሚኒስት ስርዓት፣ “ዘመኑ አስቸጋሪ ቢሆንም እምነትን ማጣት አያስፈልግም”።

“ትክክለኛ የእምነት ሕይወት የምንኖር ከሆነ፣ በሰው ዘንድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘንድ አድናቆትን ልናትርፍ እንችላለን፤ ካህን እሆናለሁ ብዬ አልገመትኩም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የደሃውን ጸሎት አድምጦ መልስ መስጠቱ እውን ነው” በማለት ክቡር አባ ቪክቶር ፖግረብኒ ያሳለፉትን የሕይወት ታሪካቸውን ዘርዝረው ተናግረዋል።

“በልጅነት እድሜ ካህን የመሆን ምኞት ነበረኝ”። ምኞታቸው ተሳክቶላቸው፣ የዛሬ ሰባት ዓመት፣ ማለትም ታህሳስ 28/2004 ዓ. ም. የክህነት ማዕረግን ተቀብለዋል። ቪክቶር የክህነት ማዕረግ ሲቀበሉ ዕድሜአቸው 66 ዓመት እና የልጅ ልጅን ያደረሱ አዛውንት ናቸው።  የቪክቶር የሕይወት ታሪክ ሲታይ በሶቭዬት ሕብረት መንግሥት፣ በውትድርና ያገለገሉ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአባ ቪክቶር ታሪክ የሚጀምረው በሞልዶቪያ፣ ስሎቦዚያ-ራስኮቭ ከምትባል መንደር ነው። ይህች መንደር በርካታ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህናት እና አንድ ጳጳስ የተገኙባት በመሆኗ ለነዋሪዎቿ ታላቅ ምስጋናን የምናቀርብበት አጋጣሚ ነው። የስሎቦዚያ-ራስኮቭ ነዋሪዎች ማንንም ሳይፈሩ፣ እምነታቸውን ለመመስከር ባላቸው ጽኑ ፍላጎት፣ አቅማቸውን በማስተባበር በስፍራው ቤተክርስቲያን ገንብተዋል። ወቅቱም የሩሲያ ኮሚኒስት ስርዓት ሁሉን ነገር የተቆጣጠርበት ጊዜ ነበር።

እምነትን ሳያጡ ውትድርናው ዓለም መምረጥ፣

ቪክቶር በሶቭየርት ሕብረት ባሕር ሃይል ለማገልገል በተመለመለበት ጊዜ ለክህነት ሕይወት የነበረው ሕልም ተሰበረ። የተወለደበት አካባቢውንም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለስ ትቶ የሄደ መሰለው። መደበኛውን የውትድርና አገልግሎቱን ካጠናቀቀ በኋላ የውትድርና ማዕረጉ እያደገ በመምጣቱ በአዛዥነት፣ ቀጥሎም ለሌላ ከፍተኛ ማዕረግ የሚያበቃውን ስልጠና በወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ገብቶ ተማረ። ከትውልድ መንደሩ የራቀ ቢሆንም ምኞቱን እውን የሚያደርግበት እና ወደ ዘርዕ ክህነት ትምህርት ቤት ገብቶ መንፈሳዊ ትምህርቶችን የመማር ፍላጎቱ በልቡ ውስጥ ይመላለስ ነበር። ቪክቶር ታሪኩን ሲገልጽ “ወላጆቼ ያወረሱኝን እምነት፣ ያስተማሩኝን ሁሉ እያስታወስኩ ኖሬአለሁ። በውትድርናው ዓለም ሆኜ ባገለገልኩባቸው ዓመታት በሙሉ ከፍተኛ አክብሮት ሲሰጠኝ የኖርኩ ሰው ነኝ። ወደ መንበረ ታቦት ፊት በመቅረብ መልካም ባል ለመሆን ቃል የገባሁ ባለ ትዳር ነኝ” በማለት አስረድቷል።

ክቡር አባ ቪክቶር ከቀኝ በኩል ሁለተኛው፣
ክቡር አባ ቪክቶር ከቀኝ በኩል ሁለተኛው፣

የቅዱስ ወንጌል መጽሐፍ በእጁ መገኘቱ ሪፖርት ተደርጓል፣

አባ ቪክቶር በኮሚኒስት ስርዓት እምነትን በተግባር እየገለጹ መኖር አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸዋል። በውትድርናው ዓለም በነበሩበት ጊዜ ያጋጠማቸው መጥፎ ገጠመኝ መኖሩን ሲያስታውሱ፣ የቅዱስ ወንጌል መጽሐፍን ይዘው መገኘታቸውን አለቃቸው ማወቃቸው ነበር። ሌላው በትውልድ መንደራቸው ለሚገነባው ቤተክርስቲያን በስውር የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ፖሊስ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። አጋጣሚው በፈቀደ ሁሉ በውትድርና ባገለገሉባቸው አካባቢዎች፣ ወደ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እየሄዱ ጸሎት እንደሚያቀርቡ አባ ቪክቶር ተናግረዋል። ይህን ሲያደርጉ በወታደራዊ ደህንነት ዓይን እንዳገቡ ይጠነቀቁ ነበር። በሰዎች በማይጠረጠሩበት አኳኋን ከሥራ ተባባሪዎቻቸው መካከል የካቶሊክ እምነት ተከታይ ካለ ብለው ይፈልጉ እንደነበር ገልጸዋል።

ደስተኛ የትዳር ሕይወት መኖር፣

ሕይወታቸው በመልካም አቅጣጫ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አባ ቪክቶር፣ የሁለት ልጆች አባት እና የልጅ ልጅን ለማየት መብቃታቸውን፣ ባለቤታቸውን ከልብ የሚወዱ መሆናቸውን እና ታናሽ ወንድማቸውም ካህን መሆናቸውን ገልጸዋል።

እምነትን በነጻነት መከተል መቻል፣

ክቡር አባ ቪክቶር ከቺሲናው ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶን ኮሳ ጋር ከመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መልስ፣
ክቡር አባ ቪክቶር ከቺሲናው ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶን ኮሳ ጋር ከመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መልስ፣

በሩስያ፣ የኮሚኒስት ስርዓት በወደቀ ጊዜ የቪክቶር ሕይወት ሙሉ በሙሉ ሊቀየር ችሏል። የአምልኮ ነጻነት በመገኘቱ እምነታቸውን ከራሳቸው አልፎ ለልጆቹም ያለ ምንም ስጋት ማስተማር ችለዋል። ቪክቶር ባሁኑ ጊዜ ከውትድርናው ዓለም በጡረታ የተገለሉ ሲሆን ወደ ትውልድ መንደራቸው ተመልሰው ከልጆቹ እና ከቤተሰቦቹ ጋር የደስታ ሕይወት በመኖር ላይ ይገኛሉ። በ2000 ዓ. ም. ባለቤታቸው በሞት ሲለዩዋቸው  ብቻውን በመቅረታቸው ወደ ልጅነት ሕይወት ተመልሰው፣ በዚያን ጊዜ በልባቸው ይመላለስ የነበረውን የክህነት ሕይወት ማሰብ ጀመሩ። ከልጅነት ሕይወት አንስቶ በልባቸው ውስጥ ታትሞ የቀረ የጥሪ ሕይወት በመሆኑ ወደ ኬቭ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ዘንድ ሄደው በልባቸው ያለውን ሃሳብ አካፈሏቸው። ሃሳባቸውን ባካፈለበት በተመሳሳይ ዓመት ወደ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ፍቃድ ተሰጣው። ወደ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት በገቡ በአራት ዓመታቸው በድጋሚ በመንበረ ታቦት ፊት ቆሙ። በዚህን ጊዜ ታዲያ የክህነትን ምስጢር ለመቀበል በመሆኑ በታሕሳስ 28/2004 ዓ. ም. መላው ቤተሰብ እና በክህነት አገልግሎት ላይ የሚገኝ ታናሽ ወንድማቸው በተገኙበት የክህነት ማዕረግን ተቀብተዋል።

የክህነት ማዕረግ በተቀበሉ ዕለት የተሰማቸው ደስታ ወደር የለውም ያሉት ክቡር አባ ቪክቶር የልጅነት ጊዜያቸውን እና የትውልድ መንደራቸውን እና ካቶሊካዊ ምዕእምናን እንዲያስታውሱ ማድረጉን ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዘለዓለማዊ ዕረፍት የተለዩዋቸን ባለቤታቸውን እንዲያስታውሱ ማድረጉን ተናግረው በሰማዩ ቤትም በደስታ እያረፉ እንደሚገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ወደ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ከመግባታቸው አስቀድሞ የልጆቻቸውን ሃሳብ የጠየቁት ክቡር አባ ቪክቶር፣ ልጆቻቸው በክህነት ጥሪያቸው ተደስተው መልካም ምኞታቸውን የገለጹላቸው መሆኑን አስረድተው በዓላማዬ የበለጠ ብርታትን እንዳገኝ፣ ያሳለፉትን ከባድ ዘመን፣ የትዳር ሕይወትንም በማስታወስ፣ ይህ ሁሉ ለክህነት አገልግሎት ያላቸውን ምኞት እንዳጠናክር አድርጎኛል ብለዋል። በዩክሬን፣ የኬቭ ከተማ ጳጳስም ለቪክቶር የክህነት ማዕረግ ከሰጡ በኋላ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን የሚያበረክቱበትን እና ሃላፊነታቸውን በታማኝነት የሚወጡበትን፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን የሚገኙበትን ቁምስና እንዲመሩ ማድረጋቸው ታውቋል።

የክሬሚያ ምዕመናን እንዲያገለግሉ ተጠርተዋል፣

አሁንም ቢሆን አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያልተለዩዋቸው ክቡር አባ ቪክቶር፣ ከዚህ በፊት የሶቭየት ሕብረት ወታደር ሆነው ያገለገሉ እና የሩስያ ዜግነት ያላቸው በመሆኑ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሩስያ እና በዩክሬን መንግሥታት መካከል በተፈጠረው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት በመካከላቸው ያለው ግንኙነት መልካም ካለመሆኑ የተነሳ፣ አባ ቪክቶር በዩክሬን ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ማበርከት እንደማይችሉ ተረድተዋል። ይህ ሲሆን አባ ቪክቶር በሩስያ ስር በምትገኝ ክሬሚያ ግዛት ሄደው በሲንፈሮፖሊ ቁምስና ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ማበርከት የሚችሉበትን ፈቃድ ከኦዴሳ ሃገረ ስብከት ጳጳስ ማግኘታቸው ታውቋል።

ዘንድሮ 73ኛ ዓመታቸውን ያከበሩት ክቡር አባ ቪክቶር፣ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ሲያበረክቱ ከቆዩበት ክሬሚያ ተመልሰው፣ ልባቸው ወዳረፈባት የትውልድ መንደር፣ ስሎቦዚያ ራስኮቭ መመለስ የሚችሉበትን ፍቃድ ከቺሲናው ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶን ኮሳ ጠይቀዋል። የቺሲናው ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶን ኮሳ የአባ ቪክቶርን ጥያቄ ከተቀበሉ በኋላ ስለ አባ ቪክቶር ሕይወት ሲናገሩ፣ “ክቡር አባ ቪክቶርን በሀገረ ስብከቴ እንዲያገለግሉ ስጋብዛቸው እና በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ ካህናት ጋር ሳስተዋውቅ፣ ክቡር አባ ቪክቶር፣ በሩስያ ኮሚኒስት ስርዓት ወቅት ረጅም እና አስቸጋሪ ሕይወት የኖሩ፣ ቢሆንም በሕይወት ዘመናቸው ሙሉ ደስተኛ መሆናቸውን ያሳዩ፣ በክህነት ሕይወታቸውም ትጉ የወንጌል መስካሪ መሆናቸውን ተናግረዋል። በሀገረ ስብከታቸው ለአገልግሎት ሲመደቡ ለዕለታዊ አገልግሎት ከሚያስፈልጋቸው ቁሳቁስ ሌላ ምንም ያልነበራቸው እና አባታዊ የክህነት አገልግሎታቸውን ለማበርከት የተዘጋጅ መሆናቸውን የክሬሚያው ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶን ኮሳ ተናግረዋል።

ክቡር አባ ቪክቶር ወደ ትውልድ መንደራቸው ወደ ሆነችው ወደ ስሎቦዚያ ራስኮቭ በደረሱ ጊዜ ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል አንዱ የወላጆቻቸውን መካነ መቃብር መጎብኘት ሲሆን ከዚህም ጋር ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ተመልሰውን ያሳለፏቸውን በርካታ ታሪኮችን እንዲያስታውሱ፣ እነዚህም የቁምስናውን ምዕመናን፣ የክህነት ጥሪያቸው መጀመሪያን፣ ምድራዊ የክርስትና ጉዞ የጀመሩበትን ሕይወት ተመልሰው እንዲያስታውሱ ማድረጋቸው ታውቋል። ክቡር አባ ቪክቶር ያሳለፉትን ሕይወት የሚያስታውሱ የፎቶ ምስሎችን በመመልከት የውትድርና ህይወታቸውንም አስታውሰዋል። “ትክክለኛ የእምነት ሕይወት የምንኖር ከሆነ፣ በሰው ዘንድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘንድ አድናቆትን ልናትርፍ እንችላለን፣ ካህን እሆናለሁ ብዬ አልገመትኩም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የደሃውን ጸሎት አዳምጦ መልስ መስጠቱ እውነት ሆኗል” በማለት ክቡር አባ ቪክቶር ያሳለፉትን የሕይወት ታሪካቸውን ዘርዝረው ተናግረዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
01 August 2019, 16:46