ፈልግ

በፓክስታን ክርስቲያን ልጃ ገረዶች በጸሎት ላይ እንዳሉ፣ በፓክስታን ክርስቲያን ልጃ ገረዶች በጸሎት ላይ እንዳሉ፣ 

በፓክስታን፣ ምዕመናን እምነታቸውን ለመቀየር እንደሚገደዱ፣ መብታቸውንም እንደሚያጡ ተገለጸ።

በፓክስታን ውስጥ ካራቺ ከተማ፣ አነስተኛ የምዕመናን ቁጥር ያላቸውን የሂንዱ እና የክርስትና እምነት ተከታዮችን የሚያሳትፍ ጉባኤ ከዛሬ ነሐሴ 2/2011 ጀምሮ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል። በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ የእስልምና ሐይማኖትን ጨምሮ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ በፓክስታን የካራቺ ሊቀ ጳጳስ የነበሩ ብጹዕ ካርዲናል ዮሴፍ ኩት የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል። ጉባኤውን ከሚካፈሉት መካከል አንዷ እና የሕግ ባለሞያ የሆኑት ወይዘሮ ታባሱም ዩሳፍ እንዳስታወቁት፣ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የእምነት ተከታዮች ላይ የመብት ጥሰት እንደሚፈጸምባቸው ገልጸው፣ በፓክስታን የሚገኙ እና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ እምነቶች ምዕመናን አስቸጋሪ ሕይወት እየኖሩ መሆናቸውን በሚገባ ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የካቶሊክ እምነት ተከታይ እና የሕግ ባለሞያ የሆኑት ወይዘሮ ታባሱም ዩሳፍ፣ በካራቺ ስለተዘጋጀው ጉባኤ አላማ ሲያስረዱ፣ በፓክስታን ውስጥ አነስተኛ የምዕመናን ቁጥር የሚገኙባቸው እምነቶች፣ ከእነዚህም መካከል የሂንዱ እና የክርስትና እምነት ተከታይ ወጣት ሴቶች እና አዛውንት እምነታቸውን ቀይረው፣ የእስልምናን እምነት ለመከተል የሚገደዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የሕግ ባለ ሞያው በማከልም በፓክስታን ውስጥ በዓመት ቢያንስ አንድ ሺህ የሚሆኑ ወጣት ልጃገረዶች እንደሚጠለፉ፣ እንደሚደፈሩ፣ ተገድደው እምነታቸውን የሚቀይሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የአነስተኛ ቁጥር ምዕመናን ቀን የሚታሰብበት፣

በካራቺ ከተማ የሚካሄደው ጉባኤ፣ እሁድ ነሐሴ 5/2011 ታስቦ የሚውለውን በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ምዕመናን ቀንን ምክንያት በማደረግ እና በዕለቱ የሚቀርቡ ሃሳቦችን እና መልዕክቶችን ለማሰባሰብ የታቀደ መሆኑ ታውቋል። የጉባኤው አዘጋጆች እንደገለጹት ዕለቱ በፓክስታን ውስጥ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የእምነት ተከታዮችን መብት ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ምዕመናን ወደ ፊት በቁጥርም ሆነ በማሕበራዊ ሕይወት የሚያድጉበትን መንገድ ለማመቻቸት የታለመ መሆኑን አስረድተዋል። የሕግ አዋቂ ወይዘሮ ታባሱም ዩሳፍ እንዳስታወቁት አነስተኛ የምዕመናን ቁጥር ከሚገኝበት የሐይማኖት ተቋማት የሚመጡ ወጣቶች የተሻለ የትምህርት እና የሥራ ዕድል የማይሰጣቸው መሆኑን ገልጸው፣ ጉባኤውን የሚካፈሉ፣ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ በፓክስታን የካራቺ ሊቀ ጳጳስ የነበሩ ብጹዕ ካርዲናል ዮሴፍ ኩት እና ሌሎችም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የሚፈርሙበትን ባለ 10-ነጥብ የመፍትሄ ሃሳቦችን መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

የፍትህ እና የመብት ጥያቄዎች፣

የጉባኤው ተካፋዮች ከሚፈርሙባቸው የመብት እና የፍትሕ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ጋብቻን መፈጸም የሚቻልበት የእድሜ ገደብን 18 ዓመት ማድረግ፣ በአንቀጽ 9 ላይ የተገለጸው እና የወጣት ልጃገረዶች ጥልፊያ እና እምነታቸውን እንዲቀይሩ ለሚገደዱበት የሕግ ከለላ እንዲደረግላቸው የሚጠይቅ መሆኑ ታውቋል። በፓክስታን ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች የሕግ ከለላን ከመጠየቅ ባሻገር፣ በሃገሪቱ ለተዘረጉት የማሕበራዊ እድገት ውጥኖች የሚያደርጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑ እንዲታወቅላቸው የሚፈልጉ መሆኑ ታውቋል። አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት በአገሪቱ ፌዴራላዊ መንግሥት ውስጥ የሚወክላቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዲቋቋምላቸው የሚጠይቅ መሆኑ ታውቋል። የሕግ ባለሞያ፣ ወይዘሮ ታባሱም ዩሳፍ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ በተለይም ለምዕራቡ ዓለም ባቀረቡት አቤቱታ፣ በፓክስታን ውስጥ በቁጥር አነስተኛ ምዕመናን ላሏቸው የሐይማኖት ተቋማት መብት እና ፍትህ መከበር ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጠይቀው በፓክስታን ለመብት እና ፍትህ መከበር ድምጹን ሲያሰማ የቆየውን እና በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን በማድረግ ለሚታወቅ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የሕግ ባለሞያ፣ ወይዘሮ ታባሱም ዩሳፍ፣ በማከልም በበጎ ሥራቸው እና በጸሎታቸው ከፓክስታን ሕዝብ ጎን ላልተለዩት፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በመላው የፓክስታን ክርስቲያን ማሕበረሰብ ስም ምስጋናን አቅርባላቸዋለች።

የእምነት ነጻነት መከበር አለበት፣

በመላው ፓክስታን፣ እሁድ ነሐሴ 5/2011 ታስቦ የሚውለው አናሳ የእምነት ተከታዮች ቀን፣ የእምነት ተከታዮቹ በአገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ መታየት እንደሌለባቸው፣ ልዩነትም እንዳይደረግባቸው፣ ከአገሩ ዜጎች ጋር እኩል የመብት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ፣ ስደት እና መንገላታት የሌለበት ሰላማዊ፣ ነጻ እና ፍታሃዊ ሕይወትን ለመኖር የሚያስችላቸው መብት እንዲከበርላቸው የሚያሳስብ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት ጭንቀት በመረዳት፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን ማጣት እና የእምነት ነጻነታቸውን መነፈግ በመረዳት፣ ይህን አስከፊ ጭቆናን ለማስወገድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የዓለሙ ማሕበረሰብ ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን የበዓሉ አዘጋጆች አስታውቀዋል።

በክርስቲያን ልጃ ገረዶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት፣

በፓክስታን ውስጥ በርካታ ክርስቲያን ልጃ ገረዶች፣ የእስልምናን እምነት አንቋሽሸዋል፣ የነብዩን መሐመድ ስም አጥፍተዋል በሚል ሰበብ፣ የሐሰት ክስ ተመስርቶባቸው ላልተወሰነ ጊዜ ወደ እስር ቤት የሚወረወሩ መሆናቸውን የሕግ ባለሞያ የሆኑት ወይዘሮ ታባሱም ዩሳፍ ገልጸው፣ በዚህ ሰበብ ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2014 ዓ. ም. የታሰሩ ሁለት ልጃገረዶች መኖራቸውን አስታውሰዋል። የሕግ ባለሞያ ከዚህም ጋር በማያያዝ ክርስቲያን ልጃ ገረዶች እምነታቸውን እንዲቀይሩ እና የእስልማናን እምነት ለመቀበል የሚገደዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
08 August 2019, 16:49