ፈልግ

የባሕር ላይ ነፍስ አድን መርከቦች፣ የባሕር ላይ ነፍስ አድን መርከቦች፣  

በሜዲቴራንያን ባሕር ላይ የሚገኙትን ስደተኞች ነጻ ለማውጣት ተማጽኖ ቀረበ።

ስደተኞችን ያሳፈረች፣ ለቀናት የደቡብ ኢጣሊያ ደሴት ከሆነች ከላምፔዱሳ የወደብ ከተማ በስምንት መቶ ሜርት ርቀት እንድትቆም የተደረገች መርከብ ነጻ እንድትደረግ በማለት የላምፔዱሳ ከተማ ቆመስ የሆኑት ክቡር አባ ካርሜሎ ላ ማግራ ተማጽኖአቸውን አቀረቡ። ክቡር አባ ካርሜሎ ተማጽኖአቸውን ባቀረቡበት ወቅት፣ ተቸግረው እርዳታን በመጠየቅ ላይ የሚገኙትን ሰዎች ጩሄት ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ተገቢ አይደለም ብለዋል። ስደተኞቹ ወደ ወደብ ከተማ ላምፔዱሳ እንዲገቡ ፍቃድ የሚያገኙ ከሆነ ቁምስናቸው እነዚህን ስደተኞች በክብር ተቀብሎ ለማስተናገድ፣ አስፈላጊውን እርዳታ ሁሉ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ክቡር አባ ካርሜሎ ላ ማግራ መናገራቸውን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ፣ ፌደሪኮ ፒያና የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የላምፔዱሳ ከተማ ቆመስ፣ ክቡር አባ ካርሜሎ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ የስደተኞች ነፍስ አድን መርከብ ወደ ወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ላምፒዱሳ እዳይደርስ ሲታገድ ይህ የመጀመሪያ እንዳልሆነ ገልጸው፣ እገዳው የእርዳታ ጠያቂዎችን የቆዳ ቀለም መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ መንገድ ነው ብለዋል። “ኦፐን አርምስ” የተባለ የባሕር ላይ እርዳታ አቅራቢ መርከብ በውስጡ 88 ስደተኞችን ማሳፈሩን እና በውስጡ የሚገኙ ስደተኞች፣ ያለ ምንም ዓይነት እርዳታ፣ ለቀናት ያህል በባሕር ላይ እንዲቆዩ በመደረጋቸው ምክንያት ከፍተኛ የአካል እና አእምሮ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ክቡር አባ ካርሜሎ አስረድተዋል። በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አባ ካርሜሎ ከጥቂት ቀናት በፊት፣ ከመርከቡ ተሳፋሪዎች መካከል ዘጠኙ ለሕክምና እርዳታ ሲባል በወደቡ አካባቢ ወደሚገኝ አንድ የሕክምና መስጫ ማዕከል መወሰዳቸው አስታውቀዋል። በነፍስ አድን መርከብ ውስጥ ከሚገኙ ተሳፋሪዎች መካከል ሌሎች ዘጠኙ፣ ወደ ባሕር ዘልለው በመግባት ለማምለጥ ሲሞክሩ በባሕር ወደብ ጠባቂ ፖሊሶች ተይዘው ከሞት እንዲተርፉ መደረጋቸው ታውቋል። የላምፔዱሳ ቆመስ፣ ክቡር አባ ካርሜሎ፣ በመርከቡ ውስጥ በሚገኙ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ የሚያበቃበት ጊዜ መቃረቡን ተናግረው፣ መፍትሄውም ሰደተኞቹ ከመርከብ እንዲወርዱ ማድረግ እና አስፈላጊውን እርዳታ ማቅረብ ብቻ ነው ብለዋል።

በኢጣሊያ ውስጥ፣ የፖለቲካ አቀንቃኞች ሃገሪቱን እየደረሰ ያለውን ቀውስ ከስደተኞች ጉዳይ ጋር በማዛመድ የዜጎችን ልብ ለመስረቅ ይሞክራሉ በማለት አባ ካርሜሎ የኢጣሊያ ፖለቲከኞችን ኮንነዋል። በዜጎቻቸው ልብ ውስጥ የተዘራው የጥላቻ እና የፍርሃት ስሜት ተገቢ አለመሆኑን ክቡር አባ ካርሜሎ ተናግረው በትክክል የተመለከትን እንደሆነ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆነው እርዳታን በመለመን ላይ የሚገኙት በመርከቡ ውስጥ የሚሰቃዩ ስደተኞች እንጂ የኢጣሊያ ሕዝብ አይደለም ብለዋል።

የ“ኦፐን አርምስ” እና “ሲ ዎች” የተሰኙት የባሕር ላይ ነፍስ አድን መርከቦች፣ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ጥቂት ስደተኞችን ይዘው ወደ ላምፔዱሳ ወደብ እንዲገቡ እና የስደተኞች ሕይወት ከሞት አደጋ እንዲተርፍ መደረጉን የገለጹት አባ ካርሜሎ፣ በሌላ ወገንም ቢሆን ከዚህ በፊት በግል ጀልባዎች የተሳፈሩ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ላምፔዱስ ወደብ ደርሰው ሕይወታቸው እንዲተርፍ መደረጉን አስታውሰዋል። ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ ስደተኞች ወደ ኢጣሊያ ድንበር ወይም ወደብ እንዲደርሱ መንገድ የሚያመቻቹ የግል እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ብቻ እንዳልሆኑ አባ ካርሜሎ አስረድተዋል፣ እነዚህ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶችም ቢሆኑ ውድ የሆነውን የሰውን ሕይወት ከሞት አደጋ ለማትረፍ ጥረት ያደርጋሉ እንጂ የሚያስወቅስ ምንም ዓይነት ተግባር አልፈጸሙ ብለዋል።

የላምፔዱሳ ቤተክርስቲያን ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ ነው፣

የላምፔዱሳ ቁምስና ስደተኞችን ተቀብሎ እርዳታን በማቅረብ የመጀመሪያ ተጠቃሽ ነው ያሉት ክቡር አባ ካርሜሎ፣ ቁምስናው በእርግጥም ስደተኞች ወደ ላምፔዱሳ ከተማ እንደገቡ የሚያገኙት የመጀመሪያ ማረፊያ እንደሆነ ገልጸው፣ ቁምስናው ለስደተኞች የሚያስፈልገውን አስቸኳይ እርዳታን በማቅረብ እንደሚታወቅ ገልጸው፣ ከዚህም በተጨማሪ ስደተኞች ቁምስናው የሚያቀርበውን የኢንተርኔት አገልግሎት በመጠቀም ለወላጆቻቸው እና ለዘመዶቻቸው ደህንነታቸውን የሚገልጹበት ቦታ መሆኑን አስረድተው፣ ቁምስናው ይህን አገልግሎቱን የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
21 August 2019, 15:54