ፈልግ

ዓለም አቀፍ የእናቶች ጡት የማጥባት ልማድ መታሰቢያ ሳምንት፤  ዓለም አቀፍ የእናቶች ጡት የማጥባት ልማድ መታሰቢያ ሳምንት፤  

ጡት በማጥባት ልማድ የልጅን ሆነ የእናትን ሕይወት ከሞት ማዳን የሚቻል መሆኑ ተገለጸ።

እናቶች ልጆቻቸውን ጡት በማጥባት ከተለያዩ በሽታዎች መከላከል እንደሚችሉ እና ውጤታማ የተፈጥሮ መንገድ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ። በዚህም ምክንያት በዓመት ከ800 ሺህ በላይ ሕጻናትን ከሞት ማትረፍ የሚቻል መሆኑንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አክሎ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሐምሌ 25 - ነሐሴ 1/2011 ዓ. ም. ድረስ በሚታሰበው እና የእናቶችን ጡት የማጥባት ልማድ ለማሳደግ በታቀደው መርሃ ግብር አማካይነት እጅግ ቀላል እና ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ዕድሜአቸው ከ5 ዓመት በታች የሆናቸውን፣ 823 ሺህ ሕጻናትን እና 20 ሺህ እናቶችን ከሞት ማትረፍ የሚቻል መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጤና ጥበቃ እና የሕጻናት መርጃ ድርጅት በጋራ በመሆን ባስተባበሩት ሳምንት፣ በእናቶች ጡት ወተት ማጣት ምክንያት የሚሞቱት ሕጻናትን ለመታደግ የሚያስችል ደንብ፣ የአገራቱ መንግሥታት፣ በኢጣሊያ ውስጥ በፍሎሬንስ ከተማ በ1982 ዓ. ም. መፈረማቸው ይታወሳል።

40 ከመቶ ሕጻናት ብቻ የእናት ጡት ወተት ያገኛሉ።              

በተባበሩት መንግሥታት፣ የጤና ጥበቃ ድርጅት ሕጻናት ከተወለዱ ከአንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ 6 ወር ድረስ የእናት ጡት እንዲጠቡ የሚመክር መሆኑ ታውቋል። ከስድስት ወር በኋላ ከጡት ወተት ሌላ በተለያዩ ደረጃ የሚዘጋጁ ተጨማሪ ምግቦች ለሁለት ዓመታት ያህል እንዲሰጣቸው የጤና ድርጅቱ የሚመክር መሆኑ ታውቋል። ነገር ግን በተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅቱ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት በዓለማችን ከ6 ወር ዕድሜ በታች የሆኑ፣ 43 ከመቶ ሕጻናት ብቻ የእናት ጡት ወተት የሚያገኙ መሆናቸውን ገልጿል።

የእናት ጡት ወተት ፍቱን መድሓኒት ነው፣

የእናት ጡት ወተት ፍቱን መድሓኒት መሆኑን ያስታወሰው፣ በተባበሩት መንግሥታት የጤና ጥበቃ ድርጅት፣ በሕጻንነት ዕድሜ የሚሰጥ የእናት ጡት ወተት፣ ሕጻናት ጤናማ እድገት እንዲኖራቸው እና በመጀመሪያዎቹ ወራት የሚሰጡ ክትባቶችን ሊተካ የሚችል መሆኑን አስታውቋል። አዲስ የተወለዱ ሕጻናት በመጀመሪያዎቹ ቀናት ወይም ሳምንታት ከእናት ጋር የሚያደርጉት የቆዳ ንክክዎች የእናት ጡት ወተትን ለማግኘት ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳድግ መሆኑን የገለጸው የድርጅቱ ሪፖርት ከእናት የሚያገኙት የሰውነት ሙቀት ከበሽታ ለመከላከል ያግዛል ብሏል። የእናት እና የሕጻን የቆዳ ግንኙነት፣ የሕጻኑን የጡት ወተት ፍላጎት ከማሳደጉ በተጨማሪ እናትም ለልጇ በቂ ወተትን እንድታመነጭ ያግዛታል በማለት ሪፖርቱ ገልጿል።

ጡት ማጥባት የእናቶችን በነቀርሳ የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል፣

ጡት የማጥባት ልማድ ጠቃሚ ጎኖች እንዳሉት ያስታወሰው፣ በተባበሩት መንግሥታት፣ የጤና ጥበቃ ድርጅት፣ የእናቶችን በነቀርሳ በሽታ የመያዝ ዕድልን እንደሚቀንስ፣ የድህረ ወሊድ ደም መፍሰስን እንደሚከላከል፣ የስኳር እና የልብ በሽታን የሚከላከል መሆኑን አስታውቋል።

ለጤና ጥበቃ የሚወጣውን ወጭ ይቀንሳል፣

ጡት ማጥባት እናትን እና ሕጻንን ሊያጠቃ ከሚችል በሽታ መከላከል ብቻ ሳይሆን ለጤና ጥበቃ የሚወጣውን ወጭ እንደሚቀንስ ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል።

ሕጻናት ላሏቸው ቤተሰቦች እና በሥራ ለተሰማሩት ሴቶች የሚደረጋ ማይበራዊ አገልግሎቶች፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጤና ጥበቃ እና የሕጻናት መርጃ ድርጅት በጋራ በማስተባበር ዘንድሮ እየተከበረ ያለው የእናቶች ጡት የማጥባት ባሕል ማሳደጊያ ዝግጅት በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት፣ ብዙ ሕጻናት ላላቸው ቤተሰቦች እና ሥራ ለሚበዛባቸው እናቶች የተለያዩ ማሕበራዊ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው አሳስቧል። እስካሁን በዓለማችን 40 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች ብቻ በመንግሥታቸው በኩል ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው፣ ከእነዚህም መካከል 15 ከመቶ የሚሆኑ የአፍሪቃ እናቶች መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።

ለእናቶች እና ለአባቶች የሚደረግ የገንዘብ ክፍያ፣

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት እንዳስታወቀው ሕጻናትን ተከታትሎ ለማሳደግ ጊዜ እና አቅም ለሚያንሳቸው ቤተሰቦች በተለይ ለእናቶች ቢያንስ የ18 ወራት ከሥራ ገበታ ውጭ የሆነ የደሞዝ ክፍያ እንዲደረግላቸው፣ አባቶችም ሕጻናትን በእንክብካቤ ማሳደግ የሚችሉበት የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ ይህም የቤተሰብን እና የማሕበረሰብን መልካም አስተዳደግ ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 August 2019, 16:12