ፈልግ

የትሪፖሊ ሕዝብ መፈናቀል፣ የትሪፖሊ ሕዝብ መፈናቀል፣ 

በሊቢያ ውስጥ ለሕጻናት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ዩኒሴፍ አስታወቀ።

በሊቢያ በመካሄድ ላይ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ለተጎዱት ሕጻናት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ዩኒሴፍ አስታወቀ። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ዛሬ ይፋ ባደረገው ዘገባ እንዳስታወቀው በሊቢያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት በትሪፖሊ እና በምዕራብ የሊቢያ ክፍላተ ሃገራት ለሚገኙ ሕጻናት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጾ በዛሬው ዕለትም በሊቢያ የሰሜን ምዕራብ ክፍለ ሀገር ወደ ሆነችው ሚሱራታ 18 ቶን የእርዳታ ምግብ የጫነ አውሮፕላን መድረሱን አስታውቋል። ዕርዳታውም በአካባቢው በተቀሰቀሰው አመጽ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሕጻናት እና ቤተሰቦቻቸው የሚከፋፈል መሆኑን የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ ገልጿል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአካባቢው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መካከል ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናት መሆናቸውን የገለጸው የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ በአመጹ ምክንያት በርካታ ሰዎች መሞታቸውን እና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው ለስደት መዳረጋቸውን አስታውቆ በአመጾች መካከል ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስባቸው ሕጻናት እና ወላጆቻቸው መሆኑን አስረድቷል። አመጾች በተቀሰቀሱባቸው አካባቢዎች ተሰማርቶ የእርዳታ አገልግሎቱን በማበርከት ላይ የሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዩኒሴፍ የሊቢያ ተወካይ የሆኑት አቶ አብደል ራማን ጋንዱር በመግለጫቸው እንዳስታወቁት ድርጅታቸው በችግር ላይ በወደቁት አካባቢዎች ንጹሕ የመጠጥ ውሃን እና የሕክምና አገልግሎትን በማዳረስ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በሊቢያ የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት አቶ አብደል ራማን ጋንዱር እንደተናገሩት ንጹሕ የመጠጥ ውሃን  ለተጠቃሚው ለማዘጋጀት የሚያግዙ መሣሪያዎችን እና ንጥረ ነገሮችን፣ የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎችን እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ መሥሪያዎች በሚሱራታ እርዳታን ሕዝቡን ለሚጠብቁት እጅግ መሠረታዊ ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በሊቢያ ውስጥ ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ አገልግሎት ተቋማት፣ ከአጋር ድርጅቶች እና ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው ቤተሰቦች እርዳታን በማዳረስ ላይ መሆኑ ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ከትሪፖሊ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር በትሪፖሊ እና በምዕራባዊ የሊቢያ ክፍላተ ሃገራት የእርዳታ አገልግሎቱን በማዳረስ ላይ መገኘቱ ታውቋል። ድርጅቱ አስቸኳይ እርዳታን በመጠባበቅ ላይ ለሚገኝ የትሪፖሊ ከተማ ነዋሪዎች እና በሊቢያ ምዕራባዊ ክፍላተ ሃገራትን ለመርዳት 5.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።   

23 April 2019, 17:51