ፈልግ

ነፍሰ ጡር፣ ነፍሰ ጡር፣ 

ሴቶች የዓለም እና የቤተክርስቲያን ተስፋ መሆናቸው ተገለጸ።

“ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን የአገልግሎት ሚና ለማሳደግ ከተፈለገ በቂ ስፍራ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል” ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ያስታወሱት ወይዘሮ ማርያ ሊያ ዘርቪኖ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ የወንዶች የበላይነት መኖሩን ገልጸው፣ ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን ቦታ ቢሰጣቸውም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ዕድል ካለተሰጣቸው በስተቀር ዋጋ አይኖረውም ብለው፣ የምንፈልገው ስልጣንን ሳይሆን ሴቶች እንደ ሴትነታቸው በብቃት ለሚያበረክቱት የቤተክርስቲያን አገልግሎት እውቅና ቢሰጣቸው መልካም ይሆናል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓለም ካቶሊካዊያን ሴቶች ሕብረት በቅድስት መንበር በኩል ከሚገኙ የእንግሊዝ እና የፔሩ ኤምባሲዎች ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ሴቶች የዓለም እና የቤተክርስቲያን ተስፋ መሆናቸው ተገለጸ። ማርች 8 በመባል የሚታወቀው እና ዘንድሮ በየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በሮም በተደረገው ስብሰባ ላይ የሕብረቱ አባል አገሮች ተወካይ ሴቶች ተገኝተዋል።

ሴቶች በዓለማችን የሚደርሱ ስቃዮችን በፍቅር እና በይቅርታ ማስወገድ እንደሚችሉ በስብሰባው ላይ የተገለጸ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ተስፋን በመሰነቅ፣ ጥላቻን በፍቅር በማሸነፍ፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ ቸርነትን እና ርህራሄን በማሳየት ትልቅ የቤተክርስቲያን እና የዓለም ተስፋ መሆናቸውን የዓለም ካቶሊካዊያን ሴቶች ሕብረት አባላት አስገንዝበዋል።

ሴቶች የቤተክርስቲያን ተስፋ ናቸው፣

ስብሰባውን የከፈቱት የሕብረት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ማርያ ሊያ ዘርቪኖ በንግግራቸው እንደገለጹት ሴት የፍቅር፣ የሰላም እና የርሕራሄ ተስፋን ለማሳደግ ትልቅ ጥረትን የምታደርግ ናት ብለዋል። ወይዘሮ ማርያ ሊያ ዘርቪኖ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ያደረጉትን ንግግር የጠቀሰው የቫቲካን የዜና አገልግሎት፣ ሴቶች ተስፋን በማድረግ በዓለማችን የሚታዩትን ችግሮች በመቀነስ ተግባር እንዲሳተፉ የሚያስችል እድል ቢሰጣቸው እና መድረኩ ቢመቻችላቸው መልካም ይሆናል ማለታቸውን ገልጿል። መፍትሄን የሚሹ በርካታ ችግሮች እንዳሉ የገለጹት ወይዘሮ ማርያ ሊያ ዘርቪኖ ሴቶች የቤተክርስቲያን ተስፋ በመሆናቸው የበኩላቸውን አስተዋጾኦ ማበርከት ይችላሉ ብለዋል።  “ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን የአገልግሎት ሚና ለማሳደግ ከተፈለገ በቂ ስፍራ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል” ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ያስታወሱት ወይዘሮ ማርያ ሊያ ዘርቪኖ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ የወንዶች የበላይነት መኖሩን ገልጸው፣ ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን ቦታ ቢሰጣቸውም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ዕድል ካለተሰጣቸው በስተቀር ዋጋ አይኖረውም ብለው፣ የምንፈልገው ስልጣንን ሳይሆን ሴቶች እንደ ሴትነታቸው በብቃት ለሚያበረክቱት የቤተክርስቲያን አገልግሎት እውቅና ቢሰጣቸው መልካም ይሆናል ብለዋል።                                                                 

የባሕል ለውጥ ሊኖር ይገባል፣

የዓለም ካቶሊካዊያን ሴቶች ሕብረት የተመሠረተው እ. አ. አ. በ1910 ዓ. ም. ሲሆን ዋና ዓላማውም በቤተክርስቲያንና በሕብረተሰብ መካከል ሴቶችን በማሳተፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ እንደሆነ ወይዘሮ ማርያ ሊያ ዘርቪኖ ገልጸው ከዚያን ጊዜ ወዲህ በዓለም ዙሪያ፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የተመሠረቱት በመቶዎች የሚቆጥሩ ካቶሊካዊ የሴቶች ማሕበራት በ66 አገሮች ዘንድ ተደራጅተው መኖራቸውን አስታውቀዋል። በእርግጥ ሴቶች የቤተክርስቲያን ተስፋ ናቸው ያሉት የሕብረቱ ሊቀመንበር ወይዘሮ ማርያ ሊያ ዘርቪኖ በቁምስና ውስጥ ተደራጅተው የሚገኙ ማሕበራት፣ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የወደቁትን፣ የተሰደዱትን፣ የቤተሰብ ሃላፊነት ያለባቸው ብቸኛ ሴቶችን፣ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ ውስጥ በመግባት በዘመናዊ ባርነት የሚሰቃዩትን በማገዝ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። ዘመናዊ የባርነትን ሕይወት ከሚኖሩ ከ40 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 71 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮ ማርያ ሊያ ዘርቪኖ ይህን ችግር ለማስወገድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በተባለው ሐዋርያዊ መልእክታቸው እንደተናገሩት ሁሉ የደሆችን ጩሄት ማዳመጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሴቶች የቤተክርስቲያን የጀርባ አጥንት ናቸው፣       

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ዶክተር ፍላሚኒያ ጆቫነሊ፣ ቅድስት መንበር የሴቶችን በርካታ ችግሮች ለማቃለል 43 ዓመታትን የወሰደ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን አስረድተዋል። ይህ የረጅም ጊዜ ጥረት ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን የአገልግሎት ሚናን ከፍ እንዲል ማድረጉን አስረድተው፣ የራሳቸውን የአገልግሎት ሚናን  እንደ ምሳሌ ወስደው አሁን የሚገኙበት የአገልግሎት ዘርፍ ከበርካታ ሰዎች ጋር ለመገናኘት እድል የከፈተ መሆኑን ገልጸው ይህም አገልግሎታቸውን ወደ ፊት ለማስኬድ አግዞኛል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ “የአፍሪካ ሚና” ባሉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ሴቶች የቤተክርስቲያን የጀርባ አጥንት ማለታቸውንም አስታውሰዋል።  

07 March 2019, 17:38