ፈልግ

የተ. መ. ድ. ሠራተኞች በአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ያጡትን በናይሮቢ ጉባኤ ላይ በጸሎት ሲያስታውሱ የተ. መ. ድ. ሠራተኞች በአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ያጡትን በናይሮቢ ጉባኤ ላይ በጸሎት ሲያስታውሱ 

በናይሮቢ የአካባቢ ጥበቃን የተመለከተ ጉባኤ በመካሄድ ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በማለት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ለምንኖርባት ምድራችን ተገቢውን እንክብካቤን እና ጥበቃን ልናደርግላት ይገባል በማለት በቅርቡ በቫቲካን ከተማ በተካሄደው የእምነቶች እና የማሕበራዊ እድገት ጉባኤ ላይ በድጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዘጋጅነት ከትናንት ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ላይ የአካባቢ ጥበቃን የተመለከተ ጉባኤ በማካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል። ይህም በተመሳሳይ ርዕሥ ላይ የሚወያይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አራተኛ መደበኛ ጉባኤው መሆኑ ታውቋል። የጉባኤው ስነ ስርዓት የተከፈተው እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ. ም. በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ በደረሰ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡን 19 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች እና ሌሎችንም በሙሉ በጸሎት በማስታወስ እንደሆነ ታውቋል።

የጉባኤው የሥራ ድርሻ፣

ጉባኤውን የሚካፈሉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚገኙ የ193 አባል አገሮች ተወካዮች፣ ሚኒስትሮች፣ የግል ድርጅቶች ተውካዮች እና የትላልቅ ኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች መሆናቸው ታውቋል። የጉባኤው ተካፋዮች የሚወያዩበት ርዕሥም የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ሲሆን በዓለማችን ላይ በከባቢ አየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰ ያለውን አደጋ በጋራ ለመከላከል በሚቻልበት የተግባር መርሃ ግብር ላይ እና ገደብ በሌለው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ላይ እንደሆነ ታውቋል። ከመጠን ያለፈ የተቃጠለ አየር ማመንጨትን ለመቀነስ እንደ አማራጭ ዘመኑ ባፈራቸው አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መጠቀምን፣ የፍጆታ መጠንን መቀነስን፣ የምግብ ብክነትን እና የባሕር ውሃ ንጽሕና መንከባከብን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩበት ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የጋራ መኖሪያችን ለሆነች ምድራችን እንክብካቤን እናድርግላት”።

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በማለት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ለምንኖርባት ምድራችን ተገቢውን እንክብካቤን እና ጥበቃን ልናደርግላት ይገባል በማለት በቅርቡ በቫቲካን ከተማ በተካሄደው የእምነቶች እና የማሕበራዊ እድገት ጉባኤ ላይ በድጋሚ መናገራቸው ይታወሳል። የሰዎች ማሕበራዊ እድገት ዘላቂነት እንዲኖረው የምንኖርበት ዓለም በአካባቢ ጥበቃ ዘዴዎች ላይ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መናገራቸው ይታወሳል።

ባሕርን ከፕላስቲክ ምርቶች ነጻ ማድረግ፣

“ባሕርን ከላስቲክ ምርቶች ነጻ እናድርግ” በማለት እንቅስቃሴውን የጀመረ ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ተንከባካቢ የግል ድርጅት፣ በኢጣሊያ እና እንዲሁም በመላው አውሮጳ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ መጠቀም የማይቻልባቸው የላስቲክ ውጤቶች ገበያ ላይ እንዲቀርቡ የሚል ዘመቻ መጀመሩ ታውቋል።  በኢጣሊያ የድርጅቱ ተወካይ የሆኑት ወይዘሮ ኤቫ አሌሲ፣ የናይሮቢን ጉባኤ ዋና ዓላማ በገለጹበት ጊዜ እንዳስረዱት፣ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የተደቀኑ ችግሮች፣ ከከባቢ የአየር ንብረት ለውጥ ጀምሮ በተለያዩ ተፈጥሮዎች ላይ የሚደርሱ ውድመቶችን በተመለከተ፣ ከመጠን መጠን በላይ የሆነ የተፈጥሮ አቃቀምን ለመቆጣጠር በሚያስችሉ የጋራ ስምምነቶች ላይ ለመድረስ እንደሆነ ገልጸዋል። ወይዘሮ ኤቫ አሌሲ እንደገለጹት በየዓመቱ ወደ 100 ሚሊዮን ቶን የሚጠጉ የላስቲክ ውጤቶች በዓለማችን ውስጥ የጥለው እንደሚገኙ፣ ከእነዚህም መካከል ወደ 9 ሚሊዮን ቶን የሚጠጉ ደግሞ በባሕር እና በውቅያኖሶች ውስጥ እንደሚጣሉ አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

                 

12 March 2019, 16:55