ፈልግ

የሶርያ ተፈናቃዮችን ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስችል የእርዳታ እጅ ማስፈለጉ ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮፍራም አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት፣ የሶርያ ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዝ የእርዳታ እጅ እንደሚያስፈልግ አሳሰበ። የድርጅቱ የቴሌቪዥን መገናኛ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዮናታን ዱሞ በሶርያ ያደረጉት ጉብኝት በማስመልከት በቪዲዮ ምስል አማካይነት ባቀረቡት ሪፖርት እንዳስታወቁት፣ በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው የተሰደዱት የሶርያ እናቶች ከስደት መልስ  የሚያጋጥማቸው የኑሮ ሁኔታ እጅግ ከባድ መሆኑን ገልጸዋል። ወደ ቀድሞ መኖሪያ አካባቢያቸው በሚመለሱበት ጊዜ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ ለልጆቻቸው የዕለት ጉርሻን ለማግኘት ሩቅ መንገድ ተጉዘው በከባድ የእርሻ ሥራ ላይ እንደሚሰማሩ፣ ይህ ሁሉ ተዳምሮ የኑሮ ሁኔታን ከአቅማቸው በላይ እንዳደረገባቸው አስረድተዋል።

የድርጅቱ ሠራተኛ የሆኑት ማርዋ አዋድ በበኩላቸው እንደገለጹት በሶርያ ስምንት ዓመታትን ካስቆጠረ ጦርነት በኋላ ዕለታዊ ፍጆታን በበቂ ሁኔታ ማግኘት ከባድ መሆኑን ተናግረው ባሁኑ ወቅት ከ3 ሚሊዮን የምግብ እርዳታን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። ከዚህም ጋር ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው በመመለስ ላይ የሚገኙን ተፈናቃዮች መልሶ ለማቋቋም ድርጅታቸው ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከ8 እስከ 9 ዕድሜ ሕጻናት ጦርነቱን ያስታውሱታል፣

በተባበሩት መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮፍራም ድርጅት ውስጥ የቴሌቪዥን መገናኛ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዮናታን ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ጦርነቱ እያከተመ ያለ መሆኑ ቢታወቅም በሶርያ አሁንም ቢሆን መቃለል ያለባቸው በርካታ ማሕበራዊ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል። በሶርያ ውስጥ ሆምስ ከተማ ሙሉ በሙሉ መውደሙን የገለጹት አቶ ዮናታን ከተሰደዱበት ወደ ሥፍራው የሚመለሱት ነዋሪዎች ምንም ዓይነት የሚጠቅም ነገር እንደማያገኙ አስረድተው ከተማዋን መልሶ ለመገንባት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። በቁጥር ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ እና እድሜአቸው ከ8 – 9 ዓመት ያላቸው ሕጻናት ትምህርታቸውን ሳይከታተሉ መቆየታቸውን አስታውሰው ባሁኑ ጊዜ የሚያስታውሱት ሌላ ነገር ሳይሆን ያሳለፉትን ጦርነት ብቻ እንደሆነ ገልጸው ይህም ለሶርያ የወደፊት ዓጣ ፈንታ መልካም አለመሆኑን አስረድተዋል።

ሶርያዊያን እንዳይራቡ የግብርና አገክግሎት እቅድ ይዘረጋ፣

በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮፍራም፣ የቴሌቪዥን መገናኛ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዮናታን ከሶርያ ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛው እንደሚራብ እና 83 ከመቶ በድሕነት ሕይወት ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ገልጸው፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰ ለዚህ ሕዝብ ዘላቂነት ያለውን የእርዳታ እጅ መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠይቀው ይህ ካልሆነ ግን አገሩ ወደ ጦርነት ተመልሶ እንዳይገባ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ሕዝቡ ዕለታዊ ቀለብ ሊኖረው ያስፈልጋል፣ ትምህርት እና መጠለያም ያስፈልጋል ያሉት አቶ ዮናታን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በሌሎች የዓለማችን አካባቢዎች ለምሳሌ በደቡብ ሱዳን እና በየመን ለሚገኙ የጦርነት አደጋ ተጠቂዎች እርዳታን በማዳረስ ላይ እንደሚገኝ አስታውቍኣል። ድርጅታቸው በጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉትን ወደ መኖሪያቸው አካባቢያቸው ተመልሰው እንዲገቡ የሚያስችል የግብርና አገልግሎት ፕሮጀክቶች እንዳሉት አቶ ዮናታን ገልጸዋል።

ሰባት የድርጅታቸው አባላት በኢትዮጵያው የአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው አልፏል፣

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው የአውሮፕላን አደጋ ሰባት የድርጅታቸው ሠራተኞች የአደጋው ሰለባ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ዮናታን እርሳቸውም አደጋ ወደ በዛበት የዓለም ክፍሎች በብዛት እንደሚጓዙ ገልጸው መላው የሥራ ተባባሪዎቻቸው በዚህ አደገኛ ሥራ ላይ የተሰማሩት ዓለምን ለመርዳት ፍላጎት ስላደረባቸው ነው ብለዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮፍራም ከሰማንያ በላይ አገሮች ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረው ዋና ዓላማውም በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት በረሃብ ለሚጠቁ አገሮች ሕዝቦች የምግብ እና የመጠለያ እርዳታ አገልግሎትን ለማቅረብ መሆኑን አስረድተዋል።

በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ውስጥ 5.6 ሚሊዮን የሶርያ ስደተኞች ይገኛሉ፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም፣ ሶርያ ባሳለፋቻቸው ስምንት የጦርነት እና የአመጽ ዓመታት፣ በረሃብ እና በድህነት ለሚሰቃይ የሶርያ ሕዝብ እርዳታን ሲያቀርብ መቆየቱን የገለጹት አቶ ዮናታን ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በአገር ውስጥ እንዲፈናቀሉ ለበርካቶች ደግሞ አገራቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል ብለው ወደ መካከለኛው የምስራቅ አገሮች የተሰደዱት 5.6 ሚሊዮን የሶርያ ስደተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።

16 March 2019, 15:52