ፈልግ

ለጥቃት የተጋለጡ ሕጻናት፣ ለጥቃት የተጋለጡ ሕጻናት፣ 

ባለፈው የአውሮጳዊያኑ 2018 ዓ. ም. በርካታ ሕጻናት የተጎዱበት ዓመት እንደነበር ተገለጸ።

በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በተጨማሪም ጦርነት የሚካሄድባቸው አገራት፣ የመንግስታቱ ድርጅት ባስቀመጣቸው ድንጋጌዎች መሰረት የሕጻናትን መብት ለማስጠበቅ፣ በሕጻናት ላይ የሚደርሰውንም የሞት አደጋ ለመከላከል የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ተማጽኗል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፉት 12 ወራት ውስጥ አመጽ በሚካሄድባቸው የዓለማችን ክፍሎች በሰዎች ሕይወት ላይ የደረሰው ስቃይ ከፍተኛ እንደነበር በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አስታወቀ። የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ በማከልም ከተለያዩ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በዓለማችን ውስጥ በጦርነት በተጠቁ አካባቢዎች ለሚገኙት በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሕጻናት ዕርዳታ ማከፋፈሉን፣ ከጥቃትም ለመከላከል መቻሉን ገልጿል።

ባለፈው የአውሮጳዊያኑ 2018 ዓ. ም. ጦርነት በተካሄድባቸው ወይም አመጽ በተቀሰቀሰባቸው የዓለማችን አካባቢዎች ሕጻናት ለጦርነት መመልመላቸው፣ ጾታዊ ጥቃትም እንደደረሰባቸው የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ ገልጾ በሶርያ፣ የመን፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ፣ ናይጀሪያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሚያንማር፣ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕጻናት ያለፈው የአውሮጳዊያኑ አመት እጅግ አሰቃቂ እንደነበር ድርጅቱ በአመቱ መገባደጃ ላይ ባወጣው ሪፖርቱ ገልጿል።

በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በተጨማሪም ጦርነት የሚካሄድባቸው አገራት፣ የመንግስታቱ ድርጅት ባስቀመጣቸው ድንጋጌዎች መሰረት የሕጻናትን መብት ለማስጠበቅ፣ በሕጻናት ላይ የሚደርሰውንም የሞት አደጋ ለመከላከል የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ተማጽኗል። የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ በማከልም ሕጻናት በሚገለገሉባቸው ተቋማት ላይ፣ ከእነዚህም መካከል በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎች በሌሎችም ሕዝባዊ ተቋማት ላይ የሚደርሱትን ውድመቶች እንዲከላከሉ ጠይቋል። መንግስታት ባላቸው ተጽዕኖን የማድረግ አቅማቸውን በመጠቀም በሕጻናት ላይ የሚደርሱትን ማናቸውንም ጥቃቶች እንዲያስቆሙ አሳስቧል። በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት የኢጣሊያ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ አንድረያ ያኮሚኒ እንደገለጹት ባለፈው የአውሮጳዊያኑ 2018 ዓ. ም. በሕጻናት ላይ የደረሰው ዓይነት ስቃይ ከዚህ በፊት እንዳልደረሰ ገልጸው ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱንም አስረድተዋል። ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አንድን አገር በጦርነት ለማጥቃት በሚወሰደው እርምጃ የሕጻናትን ሕይወት ማጥፋት፣ ንጹሕን ዜጎችን ማጥቃት፣ በአቅመ ደካሞች ላይ አደጋን መጣል ዋነኛ ስልት እየሆነ መምጣቱን ገልጸው ይህም የሚያመለክተው የዓለም መንግስታት መሪዎች በየአገሮቻቸው የሰብዓዊ መብት ማስጠበቅ ግዳጃቸውን በትክክል አለመወጣታቸውን ገሃድ ያደርጋል ብለዋል። ይህን በመገንዘብ ለመንግስታቱ መሪዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሞት አደጋን ለመከላከል በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸውን አቶ አንድርያ ያኮሚኒ ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ባሁኑ ጊዜ በ190 አገሮች ውስጥ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አንድረያ ያኮሚኒ ድርጅታቸው አገልግሎቱን በሚያበረክትባቸው አገሮች በሙሉ የሕጻናትን መብት ለማስከበር በትጋት እንደሚሰራ ጠቅሰው ጦርነቱ እጅግ በከፋባቸው አገሮች፣ ለምሳሌ በሶርያ ሃይለኛ ጦርነት እየተካሄደ ከምድር በታች ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ለሕጻናት የመማር ዕድል እንዳመቻቸ አስረድተው በዚህ ሁኔታ በየመንና በሚያንማር ጦርነቱን በመሸሽ ላይ የሚገኙ የበርካታ ሕጻናት ሕይወት መታደጉን አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የድርጅታቸው ሰራተኞች፣ ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አገሮች የስነ ልቦና ቀውስ ለደረሰባቸው በርካታ ሕጻናት የምክር አገልግሎትን ለመስጠት መሰማራታቸውን ገልጸዋል። ለጦርነት ተመልምለው በውጊያ ላይ የተሰማሩ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት የጦር መሳሪያቸውን አስቀምጠው ከወላጆቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ እንዲጀምሩ ድርጅታቸው ሰፊ አስተዋጽዖ ማደረጉን አቶ አንድረያ አስረድተዋል።

በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ፣ ጦርነት በሚካሄድባቸው አገሮች ውስጥ ከሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር የጠበቀ ግንኙነትን በማበጀት እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች በመድረስ የመጠጥ ውሃን በማቅረብ፣ ሕጻናትን ከሞት አደጋ በመከላከል ሌሎችንም አገልግሎቶችን ለማቅረብ መቻላቸውን አቶ አንድረያ አስረድተዋል። ይህ ከተለያዩት ድርጅቶች ጋር ለመተባበር የወጠኑት እቅድ ለአገልግሎታቸው ስምረት ትልቅ እገዛ ማድረጉን ያስታወቁት አቶ አንድረያ በተባበሩት መንግስታት ድንጋጌ ውስጥ የተቀመጠውንና በዋናነት የሕጻናትን ፍላጎት ማሟላት እንደሚገባ የሚጠይቀውን አንቀጽ ከሞላ ጎደል ተግባራዊ ለማድረግ አስችሎናል ብለዋል።

በአውሮጳዊያኑ አዲስ ዓመት 2019 ዓ. ም. በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕጻናት መብት የተደነገገበት 30ኛ ዓመት የሚከበርበት እንዲሁም የጀኔቭ ስምምነት 70ኛ ዓመት የሚከበርበት በመሆኑ ይህን ምክንያት በማድረግ ለየተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገሮች በሙሉ የሕጻናትን መብት እንዲያስጠብቁ፣ የሚደርስባቸውን ጥቃት እንዲከላከሉ፣ በኢጣሊያ የተባበሩት መንግስታት፣ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ አንድረያ ያኮሚኒ ጥሪ አቅርበዋል። በተለያዩ አገሮች የሚካሄዱትን ጦርነቶች ለማስቆም አሁንም ብዙ ሥራ መሰራት እንዳለበት የሚያምኑት አቶ አንድረያ፣ ይህ ነው ለማይባል ጥፋት፣ ለሰው ልጅ ሕይወት ጥፋት ምክንያት የሚሆኑት ጦርነቶች እንዲያበቁ፣ በሕጻናት ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ድርጅታቸው እንደማይቀበል ገልጸው ጦርነት የሚካሄድባቸው አገሮች ሕጻናትን ከሞት አደጋ የመከላከል ግዴታ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። አለበለዚያ ግን ሕጻናትና ወላጆቻቸው፣ መላው ሕብረተሰብም በጦርነቱ ምክንያት ዛሬ ብቻ ሳይሆን በሚቀጥሉት ዓመታትም ለከባድ ስቃይ እንደሚዳረጉ አስረድተዋል።

አቶ አንድረያ ያኮሚኒ፣ በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ፣ ከአምስት አመት በፊት በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ተንከባካቢ ያጡትንና የተበታተኑትን ወደ 6000 የሚጠጉ ሕጻናት ከወላጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማድረጉን አስታውሰዋል። እንደዚሁ ባለፈው የአውሮጳዊያኑ ዓመት 2018 ዓ. ም. በባንግላዲሽም የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የተጠለሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሮንጊያ ጎሳ ሕጻናት፣ በጦርነት ምክንያት ከደረሰባቸው የስነ ልቦና መታወክ ለመፈወስ መቻሉን አስታውቀዋል። የሕጻናት መርጃ ድርጅት በተመሳሳይ መልኩ በኢራቅ ውስጥ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው እናቶችና ሕጻናት ልዩ አገልግሎት በማበርከት ላይ እንዳለ አቶ አንድረያ ያኮሚኒ ገልጸዋል።                                         

02 January 2019, 15:44