ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስደተኞችን አጽናኑ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ያለፈው እሁድ ታህሳስ 28 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ፣ በስፍራው ከተሰበሰቡት ምዕመናንና እንግዶች ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባደረሱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ መድረሻ አጥተው ለቀናት ያህል በመርከብ ላይ ለሚገኙት ስደተኞች፣ የአውሮጳ ሕብረት አገሮች ፈጣን ዕርዳታን እንዲያደርጉላቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጠይቀዋል። ስደተኞቹ በተሳፈሩባቸው ሁለት የነፍስ አድን የግል ድርጅት መርከቦች ውስጥ የስነ አእምሮ መታወክን ጨምሮ ለተለያዩ መከራዎች መጋለጣቸውን፣ የመርከብ ላይ ሪፖርተር የሆኑት አቶ ቫሌሪዮ ኒኮሎሲ፣ በቪዲዮ ምስል መልዕክታቸው ገልጸዋል።
የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ አቶ ኤንዞ ሚላኔሲ፣ በብራሴል የአውሮጳ አገሮች ጉዳይ ምክር ቤት ስብሰባን ለመካፈል በሄዱበት እንዳስገነዘቡት የስደተኞቹ ጉዳይ ሊነሳ ይችል ይሆናል፣ ነገር ግን ቀዳሚ የመወያያ ርዕስ አይሆንም ብለዋል። 49 ስደተኞችን ያሳፈሩት ሁለት የዕርዳታ መርከቦች ባሁኑ ጊዜ ወደ ማልታ ደሴት ተጠግተው እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን በእነዚህ መርከቦች ላይ ከተሳፈሩት ስደተኞች መካከል አንዳንዶቹ ምግብ መውሰድ ማቆማቸውን የእርዳታ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።
የ49 ስደተኞች ሕይወት ለመታደግ ቃል የገባ አገር የለም፣
የአውሮጳ ሕብረት አገሮች ዲፕሎማሲ ምንጭ ገለጻ መሠረት ወደ አስር የሚጠጉ የአውሮጳ አገሮች፣ ከእነዚህም መካከል ኢጣሊያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ፖርቹጋል፣ ሉክስምበርግ፣ ሆላንድ እና ሮማኒያ ስደተኞችን ለማስተናገድ ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን በቅድሚያ የማልታ መንግሥት 49 ስደተኞ የተሳፈሩባቸውን መርከቦች፣ ወደቡን ክፍት በማድረግ፣ ስደተኞችን ወደ አገሩ የተቀበለ እንደሆነ ነው ብለዋል። ነገር ግን ባሁኑ ወቅት ወደ ማልታ ደሴት ተቃርበው በሚገኙት የዕርዳታ ሰጭ መርከቦች ውስጥ ከሚገኙት 49 ስደተኞች በተጨማሪ በቅርቡ የባሕር ጠረፍ አስከባሪዎች የተቀበሏቸው ሌሎች 249 ስደተኞችም መኖራቸውን የማልታ መንግሥት ገልጿል። ፖላንድንና ሃንጋሪን ጨምሮ ሌሎች የምስራቅ አውሮጳ አገሮች ስደተኞችን ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ታውቋል። የጣሊያን መንግሥት አቋም ግልጽ ነው ያሉት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ማቴዎ ሳልቪኒ እንዳስገነዘቡት ለሕገ ወጥ ስደተኞችና ወንጀለኞች ዕድል አንሰጥም፣ በመሆኑም የትኛውም የኢጣሊያ ግዛት ድንበሮችና ወደቦች ዝግ ሆነው ይቆያሉ ብለዋል።
ከዕርዳታ ሰጭ መርከብ ላይ የስደተኞችን ሁኔታ የሚገልጽ ምስክርነት ቀርቧል፣
አቶ ቫሌሪዮ ኒኮሎሲ፣ ስደተኞቹ ከተሳፈሩበት መርከብ ላይ በላኩት የቪዲዮ ምስክርነት እንደገለጹት በመርከቡ ላይ ከተሳፈሩት ስደተኞች መካከል አንዳንዶቹ በጭንቀት ላይ እንደሚገኙና የስነ አእምሮ መታወክም እንደሚታይባቸው ገልጸው፣ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ለሚገኙት ስደተኞች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የላኩት መልዕክት ታላቅ መጽናናትን አስገኝቶላቸዋል ብለዋል።