ፈልግ

በአፍሪቃ ውስጥ የሚታይ የውሃ እጥረት፣ በአፍሪቃ ውስጥ የሚታይ የውሃ እጥረት፣  

በአቡ ዳቢ ከተማ ዓለም አቀፍ የውሃ ጉባኤ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ መሠረት፣ በዓለማችን ከ663 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ባሁኑ ጊዜ በሚኖሩበት አካባቢ በቂ ውሃን ካለማግኘታቸው የተነሳ ውሃን ፍለጋ ወደ ሩቅ መንገድ እንደሚጓዙ፣ ሌሎችም ለረጅም ሰዓታት ያህል ተሰልፈው ወረፋን እንደሚጠብቁ ገልጿል። ለውሃ እጥረት ዋነኛው ምክንያት በዓለማችን የተከሰተው የአየር ለውጥ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድረጅት ሪፖርት ገልጾ፣ የአየር ለውጡ አሁን ከሚታየው በላይ የከፋ ችግር እንዳያስከል ስጋቱን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከዛሬ ሰኞ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ ውሃን አስመልክቶ የሚወያይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአረብ ኤምረቶች ዋና ከተማ በሆነችው በአቡዲቢ በመካሄድ ላይ መሆኑን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ አድሪያና ማሶቲ ገልጻለች። ጉባኤው እስከ ሐሙስ ጥር 9 ቀን 2011 ዓ. ም. የሚቆይ ሲሆን ጉባኤው የሚወያየው በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ውስጥ የሚታየውን የውሃ እጥረት ለማቃለል የሚያስችል መንገድ ለመፍጠር እንደሆነ ታውቋል።

በጉባኤው ላይ የሚገኙትም፣ በዓለማችን የሚታየውን የውሃና የተፈጥሮ ሃይል ማነስ በማቃለል ለዓለማችን ሕዝቦች በቂ ውሃን ለማዳረስ ጥረት የሚያደርጉ 35 ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከተለያዩ አገሮች የመጡ ባለሞያ ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል። ድርጅቱ ከዚህ በፊት ይፋ ባደገው ሪፖርቱ ከዓለማችን ሕዝቦች መካከል ሁለት ሚሊያርድ ሰዎች በቂ ውሃን እንደማያገኙ መግለጹ ይታወቃል። ለአካባቢው ሕዝብ የውሃ መጠን ዝቅተኛ በሚሆንባቸው አገሮች መካከል ለምሳሌ በእስራኤልና በፍልስጥኤም፣ በእስራኤልና በሊባኖስ፣ እንዲሁም በሕንድና በቻይና መካከል የግጭት መንሴ እየሆነ መምጣቱን ድርጅቱ ገልጿል።          

የአየር ለውጥ መከሰት ችግሩን እያባባሰ ይገኛል፣

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ መሠረት፣ በዓለማችን ከ663 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ባሁኑ ጊዜ በሚኖሩበት አካባቢ በቂ ውሃን ካለማግኘታቸው የተነሳ ውሃን ፍለጋ ወደ ሩቅ መንገድ እንደሚጓዙ፣ ሌሎችም ለረጅም ሰዓታት ያህል ተሰልፈው ወረፋን እንደሚጠብቁ ገልጿል። ለውሃ እጥረት ዋነኛው ምክንያት በዓለማችን የተከሰተው የአየር ለውጥ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድረጅት ሪፖርት ገልጾ፣ የአየር ለውጡ አሁን ከሚታየው በላይ የከፋ ችግር እንዳያስከል ስጋቱን ገልጿል። በደቡብ አፍሪቃ ከሶስት ዓመት ወዲህ በቂ ዝናብ እንደማይዘንብ፣ በዚህም ምክንያት ከተሞች በውሃ እጥረት ችግር እንደሚገኙ ታውቋል። አሁንም በአፍሪቃ ውስጥ፣ በሰሃል አገሮች መካከል 135 ሚሊዮን ሰዎች፣ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር ባስከተለው አደጋ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ታውቋል። በዓለማችን ከ11 ሰዎች መካከል አንዱ ንጹሕ ያልሆነ ውሃን ለመጠጥ እንደሚጠቀምና በበሽታ ከሚጠቁት ሰዎች መካከል 52 ከመቶ የሚሆኑትም ንጹሕ የልሆነ ውሃን ለመጠጥ የሚጠቀሙ መሆናቸው ታውቋል።

በቂ ውሃ እንዳይኖር ተጽዕኖን የሚያሳድሩ በርካታ ነገሮች አሉ፣

ጥራት ያለው ንጹሕ ውሃ እንዳይኖር ተጽዕኖን የሚያሳድሩ በርካታ ምክንያት መኖራቸውን፣ የሜዲተራኒያን አካባቢ አገሮች የእርሻ ጥናትና ምርምር አስተባባሪ የሆኑት ኢንጂኔር ኒኮላ ላማዳለና ገልጸዋል። እኝሁ ባለሙያ እንደገለጹት፣ የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር ባሁኑ ጊዜ ወደ 6.5 ቢሊዮን እንደሚጠጋና ይህ ቁጥርም በጎርጎሮሳዊያኑ 2050 ዓ. ም. ወደ 9 ቢሊዮን ይደርሳል የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ሪፖርት ጠቅሰዋል። የሕዝብ ቁጥር መጨመር ማለት የመጠጥ ውሃም አቅርቦት ጨመር እንዳለበት ያመለክታል ብለው ከውሃ አቅርቦት ማደግ በተጨማሪ የበቂ ምግብ ፍላጎት ማደግ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የአየር ለውጥ የሚያስከትለው በረሃማነት ሲታከልበት የበቂ ውሃ አቅርቦት ችግርም እየሰፋ መምጣቱ እንደማይቀር አስረድተዋል።

በምግብ ምርት ላይ የሚውል የውሃ መጠንም አለ፣

ውሃ ለመጠጥ ብቻ ሳይሆን ለምግብ ምርትና ለእንስሳት እርባታ ባደጉት አገሮች ዘንድ በከፍተኛ መጠን በጥቅም ላይ እንደሚውል የተገለጸ ሲሆን በእነዚህ አገሮች ውስጥ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የምግብ መጠን በከንቱ ባክኖና ተጥሎ እንደሚቀር ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች የታየው የውሃ መጠን መቀነስ በምግብ ምርት ላይም ተጽዕኖን እንዳስከተል ገልጾ፣ የዓለማችን እርሻ የምግብን ምርት ለማቅረብ 70 ከመቶ የሚሆን የውሃ መጠን እንደሚፈልገው ገልጾ፣ በውሃ ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሕዝቦች መኖራቸውን፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ ምርት ላይ የተሰማሩ ግዙፍ የግል ኩባኒያዎች የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ እንዳለ መዘንጋት እንደሌለበት ያስረዳው የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ሪፖርት፣  ፍትሃዊ የፖለቲካ ስርዓት በኖር፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ መሻሻል፣ የማሕበራዊ እድገት እቅዶችን በተገቢ መልኩ በተግባር ማዋል ለአካባቢ እድገት ትልቅ አስተዋጾን እንደሚያበረከ ገልጿል።

ውሃና ጂኦ ፖለቲካ፣

የሜዲተራኒያን አካባቢ አገሮች የእርሻ ጥናትና ምርምር አስተባባሪ የሆኑት ኢንጂኔር ኒኮላ ላማዳለና እንደገለጹት የውሃን አቅርቦት በተመለከተ ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ገልጸዋል ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑ ከቱርክ ግዛት የሚመነጩና በኋላም ግብጽን፣ ኢራንንና ኢራቅን በሚያቋርጡ የጢሮስና የኤፍራጥስ ወንዞች ላይ የተገነቡ ግድቦች በአገሮች የምግብ ምርት ላይ ያስከተሉት ጫና፣ በተመሳሳይ መልኩ ከዮርዳኖስ የሚነሳው የዮርዳኖስ ወንዝ በእስራኤልና በፍልስጥኤም ውስጥ ያስከተለው የውሃ እጥረት፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የሚነሳ የናይል ወንዝ ለሱዳንና ለግብጽ የውሃ እጥረት ስጋትን እንደፈጠረ ገልጸዋል። 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለውሃ እንክብካቤን ማድረግ ያስፈልጋል።                

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የውሃን ጥቅም በማስመልከት በተለያዩት አጋጣሚዎች መልዕክት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ሲሆን ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. በተከበረው ዓለም አቀፍ የውሃ ቀና ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ ለውሃ ልዩ ትኩረትን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበው ውሃ በቀላሉ ሊገኝ የሚችልና እጅግ አስፈላጊ የእግዚአብሔር ስጦታ ቢሆንም በሚያሳዝን ሁኔታ በርካታ ሕዝቦች በቀላሉ የሚያገኙት ሆኖ አልተገኘም። እያንዳንዱ ሰው ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ማግኘት ያለበት ዋናው ምክንያት በሕይወት በመቆየት ሌሎችንም መሠረታዊ የሆኑ መብቶቹን መለማመድና ማስከበር እንዲችል ስለሚያደርግ ነው። በዓለማች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ንጹሕ የመጠጥ ውሃን የማግኘት መብት ተቀምተዋል ብለው ለዚህም ትልቅ ካሳ ሊከፈለው ይገባዋል ማለታቸው ይታወሳል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል፣

ር. ሊ. ጳ. በመልዕክታቸው፣ ዛሬ በዓለማችን ከሁሉም በላይ ቅድሚያን ሰጥተን ማየት ያለብን ጉዳይ ቢኖር የሰዎች ውጤታማነትና ምርታማነት በሙሉ ለማሕበራዊ እድገት ከመዋል ይልቅ ለግል ጥቅም መዞሩን ነው። በመሆኑም እነዚህ ወደ ግል ጥቅም ብቻ ያዘነበሉ የምርት ውጥኖች ለጋራ ጥቅም እንዲውሉ በማድረግ፣ ወደ ግል ይዞታነት የዞሩ የመጠጥ ውሃ ማምረቻዎችም ሳይቀሩ የሰው ልጅ ውሃን የማግኘት መሠረትዊ መብቱን ያከበሩ መሆን እንደሚገባቸው ጥሪን ማቅረባቸው ይታወሳል፣

ውሃ ለሕዝቦች የጋራ ጥቅም መዋል ያስፈልጋል፣

የሜዲተራኒያን አካባቢ አገሮች የእርሻ ጥናትና ምርምር አስተባባሪ የሆኑት ኢንጂኔር ኒኮላ ላማዳለና በመጨረሻም የውሃ መጠን ማነስ የሚያስከትለውን ችግር ለማቃለል ተግባራዊ የሚሆኑ ሕጎችን ማርቀቅና፣ የውሃ መጠን ዝቅተኛ በሆነባቸው ተጎራባች አገሮች መካከል ሰላማዊ ውይይቶች እንዲደረጉ፣ በከንቱ የሚባክን የውሃ መጠንን መቀነስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 January 2019, 14:32