ፈልግ

MOROCCO-LIBYA-SLAVERY-DEMO MOROCCO-LIBYA-SLAVERY-DEMO 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬም ቢሆን የባርነት አስከፊ ገጽታ እንዳልተወገደ ገለጹ።

በዘመናችን ለባርነት ሕይወት እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሱትም የአምባ ገነናዊ መንግሥት መኖር፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ጦርነቶችና ረሃብ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም የአለም አቀፍ የንግድ ስምሪትም አስተዋጽዖን እንዳደረገ ታውቋል። በዕለታዊ ኑሮአችን ከምንገለገልባቸው ቁሳቁሶች መካከል እንደ ዘመናዊ ስልኮች፣ ቅባቶችና የቤት ውስጥ ዕቃዎች የሚመረቱት፣ በጦርነትና በአመጽ ምክንያት በተሰደዱት፣ በዝቅተኛ የጉልበት ክፍያ ተቀጥረው እንዲሰሩ በሚገደዱት ሰዎች፣ ሴቶችና ሕጻናት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትናንት እሁድ ህዳር 23 ቀን 2011 ዓ. ም. የባርነት አገዛዝ የተወገደበትን ዕለት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው የባርነት አገዛዝ እንዳልተወገደ አስረድተው፣ የሰዎች ስቃይ እንዲጨምር ምክንያት የሚሆነውን የመበላለጥ መንፈስ ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል።      

ከ40 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በባርነት ሕይወት ውስጥ ይገኛሉ፣

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና የሴትኛ አዳሪነት ተግባርን ለማስቀረት በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌን ያጸደቀበት 70ኛ ዓመት ሊከበር በተቃረበበት ባሁኑ ወቅትም ቢሆን ችግሩ ገና እንዳልተወገደ፣ 40.3 ሚሊዮን ሰዎች ዘመናዊ የባርነት ሕይወትን እየኖሩ መሆኑ ሲነገር፣ በዚህ አስከፊ ሕይወት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጉልበታቸውን በመበዝበዝ፣ እንዲሁም በሴተኛ አዳሪነት ተግባር ላይ በመሰማራት፣ ይህም በገንዘብ ሲተመን 354 ሚሊያርድ ዶላር እንደሆነ ተገምቷል። በዘመናችን ለባርነት ሕይወት እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሱትም የአምባ ገነናዊ መንግሥት መኖር፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ጦርነቶችና ረሃብ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም የአለም አቀፍ የንግድ ስምሪትም አስተዋጽዖን እንዳደረገ ታውቋል። በዕለታዊ ኑሮአችን ከምንገለገልባቸው ቁሳቁሶች መካከል እንደ ዘመናዊ ስልኮች፣ ቅባቶችና የቤት ውስጥ ዕቃዎች የሚመረቱት፣ በጦርነትና በአመጽ ምክንያት በተሰደዱት፣ በዝቅተኛ የጉልበት ክፍያ ተቀጥረው እንዲሰሩ በሚገደዱት ሰዎች፣ ሴቶችና ሕጻናት እንደሆነ ታውቋል።

በየጊዜ አዳዲስ ክስተቶች ይፈጠራሉ፣

በተባበሩት መግሥታት፣ ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ከሚከታተል ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር ባወጡት አሃዝ መሠረት ለባርነት ሕይወት የሚዳረጉት የማሕበረሰብ ክፍሎች የድህነት ሕይወት የሚኖሩ፣ ሥራ አጥ ሰዎች፣ ስደተኞች፣ ለሴተኛ አዳሪነት የተሸጡ ሴቶችና ሳይወዱ በግድ ወደ ጋብቻ ሕይወት እንዲገቡ የተደረጉ መሆናቸው ታውቋል። ድርጅቶቹ ከዚህም ባሻገር በየዓመቱ በተለያዩ አዳዲስ ምክንያቶች ወደ ባርነት ሕይወት ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እያደገ መሆኑን ይፋ አድረገዋል።

ለባርነት ሕይወት የተጋለጡ ሴቶች፣

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር፣ በ2016 ዓ. ም. ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ለባርነት ሕይወት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ወጣት ልጃገረዶች መሆናቸውን ገልጾ፣ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ ብቻ 89 ሚሊዮን ሰዎች ዘመኑ ባመጣቸው የባርነት ሕይወት ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል። ድርጅቱ እንዳስታወቀው በባርነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በመካከለኛ የምስራቅ አገሮችና በአረብ አገሮች ውስጥ የሚገኙን ቢያካትት ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል አስረድቷል። ዘመናዊ የባርነት ዓይነቶች በሚባሉት ለምሳሌ በታጣቂ ቡድኖች በኩል ሕጻናትን ለውትድርና አገልግሎት በግዳጅ መመልመልና ሕገወጥ የሰዎች የአካል ክፍሎች ዝውውር ይገኙባቸዋል።

በቁጥር በርካታ ባሮች ያሉባቸው አገሮች፣

የባርነት አገዛዝ የሚስፋፋውና የሚያድገው በጦርነትና ጨቋኝ በሆነ አምባገነናዊ አገዛዞች እንድሆነ የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደ ሰሜን ኮርያ ባሉት አገሮች ከ10 ሰዎች መካከል አንዱ የባርነት ሕይወት ለመኖር እንደሚገደድና ስርዓቱን ለማጠናከር እንዲቻል ነጻ የጉልበት ሥራን እንደሚሠራ ታውቋል። ከሰሜን ኮርያ በተጨማሪ እንደ ኤርትራ፣ ቡሩንዲና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ በመሳሰሉ አገሮች ሰዎች ነጻ የጉልበት አገልግሎት እንዲያበረክቱ መገደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሪፖርቱ ገልጾ፣ በአፍጋኒስታን፣ በማውሪታኒያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በፓክስታን፣ በካምቦዲያና በኢራን ተመሳሳይ ስርዓት እንዳለ ገልጿል። ባርነት እንደ ዩናይትድ ስቴትስ፣ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ሆላንድን በመሳሰሉ ሀብታም አገሮች ውስጥ ምንም ዓይነት ትርፍ እንደማያስገኝ ሪፖርቱ ጠቅሶ ነገር ግን ስደተኞች በብዛት በሚመላለሱባት ኢጣሊያ ንግድ ሆኗል ብሏል። 

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሳሌዢያን፣ ዶን ቦስኮ ሚሺን የተሰኘው ድርጅት ዋና ፕሬዚደንት የሆኑት ጃምፔትሮ ፐተኖን፣ የባርነት አገዛዝ የተወገደበት ዕለት መታሰቢያ ቀን ትርጉም እንዲያብራሩ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ የባርነት ክስተት ከሚታዩባቸው አህጉራት መካከል አፍሪቃም እንደምትገኝ ጠቅሰው የአህጉሩ በርካታ ሕጻናት ከአቅማቸው በላይ የሆነ የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ መገደዳቸውን ገልጸው፣ ሕጻናት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ትክክለኛውን የእድገት ደረጃን ተከትለው ማደግ እንዳለባቸው፣ ወደ ፊት ለሀገራቸው ሃላፊነት የሚሰማቸው ሆነው እንዲያድጉ ዕድሎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። አስከፊ የባርነት ገጽታዎችን ለማስወግድ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚከበረው በዓል፣ የባርነት አስከፊ ገጽታዎችን ለማስቀረት ወይም ለማስወገድ የሚያግዙ ጠቃሚ ሃሳቦችን እንድንጋራ ያደርገናል ብለዋል።

03 December 2018, 16:11