ፈልግ

donne indiane nello stato federale di Orissa, India donne indiane nello stato federale di Orissa, India 

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት እንዲያበቃ ጥሪ ቀረበ።

በሁሉም የማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ለሴቶች የሚሰጥ አድናቆት አስፈላጊ በመሆኑ በሥራ ቦታም ሆነ አስፈላጊ ውሳኔዎችን በሚደረጉባቸው የተለያዩ ቦታዎች፣ በቤተክርስቲያንና በማህበራዊ መዋቅሮች በሙሉ የሴቶች ተሳትፎ ተረጋግጦ እውቅናን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበው ነበር።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ህዳር 16 ቀን 2011 ዓ. ም. በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወም የተከበረውን ዓለም አቀፍ ቀን ምክንያት በማደረግ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስር የተዋቀሩ ማሕበራት በጋራ ሆነው ድምጻቸውን አሰምተዋል። ዕለቱን ምክንያት በማድረግ የኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ ንግግር አድርገዋል።

በሴቶች ላይ የሚደርሱትን በደሎች ለማስቀረት ሰላማዊ ሰልፎች፣ ስብሰባዎችና ታላላቅ ጉባኤዎች በቂ አይደሉም፣ ሞራላዊ ባሕል እንዲሰርጽ የሚያደርጉ ጠንካራ ማሕበራት መቋቋም ይኖርባቸዋል፣ ማሕበረሰብም በሴቶች ላይ የሚደርሱትን በደሎችና ጥቃቶችን ሲመለከት በዝምታ ማለፍ የለበትም፣ ሴቶችም በበኩላቸው የሚደርስባቸውን ጥቃት አሳንሰው በመመልከት በዝምታ ማሳለፍ የለባቸውም፣ ድምጻቸውን በማሰማት ማጋለጥ ይኖርባቸዋል በማለት በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስር የተዋቀሩ ማሕበራዊ ድርጅቶች አቋማቸውን ገልጸዋል። ማህበራቱ በማከልም ለችግሩ ፈጣን መፍትሄን ለማስገኘት ለቤተሰብ፣ ለፖለቲካዊና ሕጋዊ መንገዶች ድጋፍን በመስጠት የቤተሰብን ሕይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ፣ የሴቶችንም የግልና ማሕበራዊ ሕይወት ለማሻሻል ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ ድርጅቶቹ አሳስበዋል።

የትምህርት ጥቅም፣

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙትን የዓመፅ ክስተቶች በቁጥር መገመት አስቸጋሪ እንደሆነ፣ በኢጣሊያ የሕዝብ ቆጠራ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ገልጾ ምክንያቱንም ሲዘረዝር በኢጣሊያ ውስጥ የተዋቀሩ ካቶሊካዊ ማሕበራት ቅድሚያን ሰጥተው የሚንቀሳቀሱት በሰው ልጅ ሕይወት ክቡርነትና ሊሰጠው ስለሚገባ አክብሮት ግንዛቤ መስጠትና በጎኑም ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን ማፈላለግ እንደሆነ ገልጿል። ማሕበራቱ በስፋት እየሠራም ያለው ማሕበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ ሥራ በመንግሥታዊ ተቋማት መካከል በስፋት እየተከናወነ እንዳለ ብሄራዊ መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ለመንግሥታዊ ተቋማት የቀረቡ ጥያቄዎች፣

በዚህም መሠረት የሴቶች ማሕበራትና የተለያዩ ድርጅቶች በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በማጠናከር፣ በኢጣሊያ ውስጥ ባሉት ክፍላተ ሀገራት ጉዳዩን በመከታተል ላይ የሚገኙ ግለሰቦችም ቢሆኑ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸም የኃይል ጥቃት ለመቆጣጠር የወጡ ደንቦች በሙሉ ተፈጻሚነትን እንዲያገኙ ለመንግሥት አቤቱታን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አቋማቸውን ገልጸዋል።

ዕለቱን ምክንያት በማድረግ የቪዲዮ ምስል መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፣ የኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ እንደገለጹት፣ በሴት ላይ በደልን የሚፈጽም ራሱ ወደዚህ ዓለም እንዴት እንደመጥ ያልተረዳና የሴቶችን እናትነት በውል ያልተገነዘበ ነው ብለዋል። ብጹዕነታቸው በማከልም በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትና በደል እየተስፋፋ መምጣቱን ገልጸው ይህን በደል በማንኛውም ደረጃ በጽኑ መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቤተክርስቲያን በሴቶች ላይ የሚደርሱትን ጥቃቶች በጽኑ እንደምትቃወም ገልጸው፣ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ሴቶች የሚያስፈልገውን የምክር አገልግሎት በማበርከት ላይ መሆኗን አስረድተዋል። ብጹዕነታቸው ካህናት እንደመሆናቸውን ለምክር አገልግሎት ብለው ከሚመጡ በራካታ የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት ሴቶች መርጃዎች እንደሚደርሷቸው ገልጸዋል። ስለዚህ ለነዚህ ሴቶች የበለጠ አቀባበልና ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ፣ የኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ ገልጸው በመጨረሻም

በሁሉም የማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ለሴቶች የሚሰጥ አድናቆት አስፈላጊ በመሆኑ በሥራ ቦታም ሆነ አስፈላጊ ውሳኔዎችን በሚደረጉባቸው የተለያዩ ቦታዎች፣ በቤተክርስቲያንና በማህበራዊ መዋቅሮች በሙሉ የሴቶች ተሳትፎ ተረጋግጦ እውቅናን ማግኘት ይኖርበታል ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት አስታውሰዋል።  

28 November 2018, 15:22