ፈልግ

YEMEN CONFLICT DISPLACED PEOPLE YEMEN CONFLICT DISPLACED PEOPLE 

በየመን በቀን 100 ሕጻናት እንደሚሞቱ የሕጻናት አድን በጎ አድራጊ ድርጅት አስታወቀ።

ከምን ጊዜም የከፋ ቀውስ ይጠብቀናል ያሉት አቶ ፊሊፖ ኡንጋሮ፣ በጦርነቱ ለተጠቃው ሕዝብ አስቸኳይ የምግብና የመድሃኒት ዕርዳታ ካልቀረበለት 11.3 ሚሊዮን ሕጻናት በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ከጦርነት አደጋ ሊተርፉ ይችላሉ ቢባል እንኳ ከፍተኛ ረሃብና ሕመም ይጠብቃቸዋል ብለዋል። ዕድሜአቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 2 ሚሊዮን ሕጻናት የተመጣጣኝ ምግብ እጥረት እንዳለባቸው፣ ከእነዚህም መካከል 400 ሺህ ዘላቂ የምግብ ዋስትናና የሕክምንና እጥረት እንደሚያጋጥማቸው አቶ ፊሊፖ ኡንጋሮ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፉት ቅርብ ሳምንታት ሆዴይዳ በተባለ ግዛት በተካሄደው ሃይለኛ ጦርነት ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆነ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ሕጻናት መሆናቸው ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ብቻ መቶ የሚሆኑ የአውሮፕላን ጥቃቶች መካሄዳቸውን፣ ይህም ባለፈው ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ ከተፈጸመው የአውሮፕላን ጥቃት በአምስት እጥፍ እንደሚበልጥ ታውቋል። ጥቃቱ ቁልፍ የወደብ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን በአካባቢው የሕጻናትን አድን የተሰኘ የእርዳታ ሰጭ ድርጅት፣ የግንኙነት ክፍል ዳይረክተር የሆኑት ፊሊፖ ኡንጋሮ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል። አቶ ፊሊፖ ኡንጋሮ በማከልም በአካባቢው እየተፈጸመ የሚገኘው የአውሮፕላን ጥቃት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለሞት አደጋ እንዳጋለጣቸው፣ በአካባቢው የሚደረገውን የዕርዳታ አቅርቦት በማስተጓጎሉ በቀን በአማካይ 100 ሕጻናት በረሃብና በበሽታ ምክንያት መሞታቸውን ተናግረዋል።

በሆዴይድ አመጽ መቀስቀስ፣

በጦርነት ለተጎዳው ሕዝብ የሚቀርብ በርካታ የዕርዳታ ቁሳቁስ በወደብ ላይ ተከምሮ እንደሚገኝ፣ ወደ እርዳታ ፈላጊዎች እንዳይደርስ መንገዶች በመዘጋታቸው ምክንያት በርካታ ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረትና በሕክምና አቅርቦት አለመኖር ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ አቶ ፊሊፖ ኡንጋሮ ገልጸዋል። በሕክምና መስጫ ጣቢያ የሚገኙ ታካሚዎችም በቦምብ ጥቃት የተነሳ እጅግ በፍርሃት መረበሻቸውን ያስታወቁት አቶ ኡንጋሮ፣ ምንም እንኳን በሕክምና ላይ ቢገኙም ነፍሳቸውን ለማትረፍ ብለው መሸሸጊያ ቦታ ፍለጋ እንደሚሯሯጡ ገልጸው፣ የጤና ማዕከሎች ደህንነታቸው ያልተጠበቀ በመሆኑና የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች የቦምብ ጥቃትን ስለሚፈሩ ወደ ሆስፒታሎች ሄደው መታከምን አይመርጡም ብለዋል።

መቋጫ የሌለው ጦርነት፣

በየመን ከ2007 ዓ. ም. ጀምሮ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ያለፈበት ሃይለኛ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ባለፉት ሦስት አመታት ውስጥ 18 ሺህ የአውሮፕላን ጥቃቶች በሰንዓ ከተማ ብቻ በመካሄዱና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም እንደዚሁ አመጾች በመካሄዳቸው መላዋ የመን መቋጫ በሌለው ጦርነት ውስጥ በመግባቷ ረሃብና በሽታ እንደሰፈነባት ታውቋል። የሳውዲ ጦር የወደብ ከተማ የሆነችውን ሃዴይዳን ከዋና ከተማ ሰንዓ ጋር የሚያገናኘውን ዋና አውራ ጎዳናን በመቆጣጠራቸውና የተቀረውን የሃገሪቱን ክፍል በመነጠላቸው ምግብ፣ መድሃኒትና ነዳጅ ማከፋፈል አይቻልም ተብሏል። የምንዛሪ ዋጋም በስፋት በመቀነሱ በበርካታ ስፍራዎች የእህል ዋጋ ጨምሯል፣ በመሆኑም በርካታ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው እህል ከገበያ የመሸመርት አቅማቸው በእጅጉ ቀንሷል ተብሏል። ባሁኑ ወቅት 8 ሚሊዮን የየመን ሕዝብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚያቀርብለት የምግብ አቅርቦት እነድሚታገዝና፣ በቅርብ ወራት ውስጥ ይህ ቁጥር ወደ 14 ሚሊዮን እንደሚደርስ የሕጻናትን አድን የዕርዳታ ሰጭ ድርጅት፣ የግንኙነት ክፍል ተጠሪ የሆኑት አቶ ፊልፖ ኡንጋሮ ገልጸዋል።

11. 3 ሚሊዮን ሕጻናት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፣

ከምን ጊዜም የከፋ ቀውስ ይጠብቀናል ያሉት አቶ ፊሊፖ ኡንጋሮ፣ በጦርነቱ ለተጠቃው ሕዝብ አስቸኳይ የምግብና የመድሃኒት ዕርዳታ ካልቀረበለት 11.3 ሚሊዮን ሕጻናት በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ከጦርነት አደጋ ሊተርፉ ይችላሉ ቢባል እንኳ ከፍተኛ ረሃብና ሕመም ይጠብቃቸዋል ብለዋል። ዕድሜ አቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 2 ሚሊዮን ሕጻናት የተመጣጣኝ ምግብ እጥረት እንዳለባቸው፣ ከእነዚህም መካከል 400 ሺህ ዘላቂ የምግብና የሕክምንና እጥረት እንደሚያጋጥማቸው አቶ ፊሊፖ ኡንጋኣሮ አስታውቀዋል።

የሕጻናትን አድን ድርጅት አቤቱታ፣

በሃገሪቱ የዕርዳታ እጁን የዘረጋው የሕጻናትን አድን በጎ አድራጊ ድርጅት፣ በየመን በበርካታ ስፍራዎች የሚካሄዱት ጦርነቶችና አመጾች እንዲያበቁ፣ ሌላ ተጨማሪ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም እንዳይከሰት በማለት ድምጹን ያሰማ መሆኑ ታውቋል። ድርጅቱ በማከልም ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማዳረስ የሚያስችል መንገድ እንዲከፈት ያለ ቅድመ ሁኔታ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ከሆኑት ከአቶ ማርቲን ግሪፊትስ ጋር ድርድር እንዲጀመር ጠይቀዋል። ላለፉት አራት ዓመታት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን የየመን ሕጻናትን ያስታወሱት የበጎ አድራጊው ድርጅት የግንኙነት ክፍል ተጠሪ የሆኑት አቶ ፊሊፖ ኡንጋሮ እንዳስገነዘቡት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የተካሄደው አሰቃቂ የአውሮፕላን ጥቃት የዓለም መንግሥታት መሪዎች ያስተላለፉት ውሳኔዎች ምንም ዓይነት መፍትሄን እንዳላስገኘ ያመልክታል ብለው ዓለም ዕቀፉ ማሕበረሰብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱን በማጠናከር፣ በሰው ሕይወት ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲያበቃ፣ ዘላቂ ሰላም በየመን እንዲወርድ የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት ያስፈልጋል ብለዋል።              

08 November 2018, 16:31