ፈልግ

NAVE DICIOTTI A CATANIA NAVE DICIOTTI A CATANIA 

አልባንያ ስደተኞችን በመቀበሏ ጥሩ ምሳሌ ሆናለች።

የአልባንያ ዋና ከተማ የትራና ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፍረንዶ፣ የአልባንያ መንግሥት በቅርቡ በአንድ መርከብ ላይ ተሳፍረው ሲጓዙ በኢጣሊያ የባሕር ጠረፍ አስከባሪዎች ተይዘው ለአስር ቀናት ያህል በባሕር ላይ እንዲቆዩ የተደረጉትን ስደተኞች ለመርዳት የወሰዱትን አቋም አወድሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአልባንያ ዋና ከተማ የትራና ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፍረንዶ፣ የአልባንያ መንግሥት በቅርቡ በአንድ መርከብ ላይ ተሳፍረው ሲጓዙ በኢጣሊያ የባሕር ጠረፍ አስከባሪዎች ተይዘው ለአስር ቀናት ያህል በባሕር ላይ እንዲቆዩ የተደረጉትን ስደተኞች ለመርዳት የወሰዱትን አቋም አወድሰዋል። ነገር ግን ሌሎች በርካታ የአውሮፓ ህብረት አገሮች ለሚያሳዩት ቸልተኝነት ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፍረንዶ የአልባንያን መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን፣ መንግሥታቸው ላሳየው በጎ ምሳሌነት ከልብ አመስግነዋል።

የቲራና ዱራሶ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ፍረንዶ ለአልባንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለክቡር አቶ ዲትሚር ቡሻቲ በላኩት የደብዳቤ መልዕክታቸው፣ የአልባንያ መንግሥት በቅርቡ መድረሻን አጥተው በባሕር ላይ ለአሥር ቀናት ያህል የቆዩትና በኋላም ወደ ደቡብ ኢጣሊያ የወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ካታኒያ እንዲገቡ ከተደረጉት ስደተኞች መካከል የተወሰኑትን ተቀብላ ለማስተናገድ ፈቃደኛ በመሆኗ አመስግነዋል። ከባልካን አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው አልባንያ የምትቀበላቸው ሃያ ስደተኞች ከኤርትራ የመጡ መሆናቸው ታውቋል።  የቲራና ዱራሶ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ፍረንዶ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት ስደተኞቹ ባሕር ላይ ካሳለፏቸው የመከራ ቀናት በኋላ በደግነቱ ወደሚታወቀው ወደ አልባንያ ሕዝብ ዘንድ ለመምጣት ዕድል አግኝተዋል ብለዋል።

ለአውሮጳ ሕብረት አገሮች ምሳሌ መሆን፣

የቲራና ዱራሶ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ፍረንዶ፣ የአልባንያ መንግሥት ባደረገው መልካም ተግባር ደስታ የተሰማቸው ቢሆንም በሌላ ወገን በርካታ የአውሮፓ ሕብረት አገሮች በባሕር ላይ ለቀናት የቆዩትን ስደተኞችን ተቀብለው ላለማስተናገድ በወሰዱት ውሳኔ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት በርካታ የአውሮፓ አገሮች ጥንታዊውን የክርስቲና ባሕላቸውን በመዘንጋት ችግር ውስጥ የወደቁትን ስደተኞች ለመርዳት ችላ ማለታቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ የአልባንያና የአይርላንድ መንግሥታት እንዲሁም የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ስደተኞን ተቀብሎ ለማስተናገድ ያሳዩት አዎንታዊ ምላሽ ለሌሎች የአውሮፓ አገሮች መልካም ምሳሌ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

አውሮጳም የስደት ዓመታትን አሳልፏል፣

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ፍረንዶ፣ የአልባንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክብር አቶ ቡሻቲ፣ እኛ አልባንያዊያን ባንድ ወቅት እንደ ኤርትራዊያን ስደተኞች ነበርን፣ ብዙ ዜጎቻች ወደ ኢጣሊያ ተሰደዋል  ያሉትን አስታውሰው በግብፅ አገር እንግዶች ወይም ስደተኞች ሆነን ሳለ ማንም ሰው አይገድልም ወይም አይጨቁንም ምክንያቱም አስቀድሞ ራሱም ስደተኛ ስለነበረ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ ያስታውሰኛል ብለዋል።

የአልባንያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተግባር መሆን ያለበት፣

የቲራና ዱራሶ ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ፍረንዶ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት እንደገለጹት በቤተክርስቲያናቸው የሚገኙት የተለያዩ ተቋማት ቀዳሚ ሚና የሚሆነው ወደ አገራቸው ለመጡት 20 ኤርትራዊያን ስደተኞች መጠላያን የመስዳሰሉ ሌሎች አስፈላጊ እርዳታዎችን ማቅረብ እንደሚሆን ገልጸው፣ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ካሪታስ ከተባለው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እርዳታ ሰጭ ድርጅት ጋር በመተባበር ለተረጅዎቹ የሚደረገውን የዕርዳታ አቅርቦት ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ፍረንዶ በማከልም የአልባንያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከዚህ በፊት ወደ አገራቸው ለመጡት የመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች ማለትም ለሶርያና ለእራቅ ስደተኞች ዕለታዊ የእርዳታ አቅርቦት ሥራን በማከናወን ላይ ትገኛለች ብለዋል።                 

29 August 2018, 16:29