ፈልግ

NAVE DICIOTTI A CATANIA NAVE DICIOTTI A CATANIA 

የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ስደተኞችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል።

የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ አንድ አገር አስቀድሞ ያዘጋጀው ሕግና ደንብ ሊኖረው ይገባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢጣሊያ መንግሥትና በኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት በቅርቡ ወደ ኢጣሊያ እንድገቡ የተፈቀደላቸው ስደተኞች በሮካ ዲ ፓፓ ወደ ተዘጋጀላቸው የመጠለያ ጣቢያ ተወስደዋል። ስደተኞችን የያዘ መርከብ ለአስር ቀናት በባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች እንዳይንቀሳቀስ ተደርጎ መቆየቱ ይታወቃል። ክቡር አባ ማፈይስ እንደገለጹት በሁለቱ ወገኖች የተደረሰው ስምምነት አገራችን እንግዳን ተቀብሎ የማስተናገድን ባሕል ለማዳበር ያግዛል ብለዋል።

በኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እና በኢጣሊያ መንግሥት መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት ከመቶ በላይ ስደተኞችን የጫነ መርከብ ከአንድ ሳምንት የባሕር ላይ ቆይታ በኋላ ስደተኞችን ወደ ኢጣሊያ ግዛት ማጓጓዙ ታውቋል። ሰደተኞቹ ወደ ደቡብ ኢጣሊያ ግዛት ወደ ሆነው ወደ ካታኒያ ወደብ መድረሳቸው ታውቋል። ከመንግሥት ጋር የተደረገውን ድርድር የተሳተፉት የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ፋውንዴሽን ተወካይ የሆኑት ክቡር አባ አልዶ ቦናዩቶ መሆናቸው ታውቋል።  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በአይርላንድ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ቅድስት መንበር ሲመለሱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ስደተኞችን ወደ ኢጣሊያ ግዛት ለማስገባት ከኢጣሊያ መንግሥት ጋር በመደራደር ወደ ስምምነት የደረሱትን የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ፋውንዴሽን ተወካይ የሆኑትን ክቡር አባ አልዶ ቦናዩቶንና ከኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ በኩል ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲየሮ ባሰቲን አመስግነዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ አንድ አገር አስቀድሞ ያዘጋጀው ሕግና ደንብ ሊኖረው ይገባል ብለው ስደተኞችም በደረሱበት አገር ማሕበረሰብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ክቡር አባ ኢቫን ማፈይ በኢጣሊያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማሕበራዊ መገናኛ ክፍል ተጠሪ ሲር ከተሰኘ የቤተክርስቲያን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ከመንግሥት በኩል የተሰጠው ምላሽ ሌላ አማራጭ ስለሌለ መሆኑን ገልጸው ቢሆንም ይህ ምላሽ አገራችን እንግዳን ተቀብሎ የማስተናገድ ባሕል ለማዳበር ያግዛል ብለዋል።  ክቡር አባ ኢቫን እንደገለጹት ወደ ኢጣሊያ የወደብ ከተማ ወደሆነችው ወደ መሲና የደረሱት ስደተኞች ባሁኑ ጊዜ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው በመጠለያ ጣቢያ ከሚያደርጉት የአጭር ቀናት ቆይታ በኋላ በመሐል አገር ወደትገኝ ወደ ሮካ ዲ ፓፓ ከተዛወሩ በኋላ፣ ስደተኞችን ተቀብለው ለማስተናገድ ወደ ተዘጋጁ ሀገረ ስብከቶች እንደሚሄዱ ገልጸዋል። ክቡር አባ ማፈዪስ በማከልም ለስደተኞች የሚደረገውን የመስተንግዶ መጠንና ዓይነት በተመለከተ መንግሥትም በበኩሉ ስደተኞችን በሚመለከቱ የፖለቲካ አቋም ላይ መወያየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። አባ ማፈዪስ በንግግራቸው መጨረሻ በአውሮፓ ውስጥ መሽገን ለስደተኞች በሮቻችንን የምንዘጋ ከሆነ ስደተኞችን ለአደጋ ከመዳረግም በላይ እኛም ተዘግቶብን እንሞታለን ብለው ይህ ከሚሆን ህግና አቅም በፈቀደ መጠን የምንችለውን በማድረግ መፍትሄ ማግኘት ያስፈልጋል ብለዋል።

ስደተኞችን በተመለከተ በመንግሥትና በቤተክርስቲያን መካከል መተጋገዝ ሊኖር ይገባል።

ክቡር አባ አልዶ ቦናዩቶ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት የጣሊያንኛ ቋንቋ ክፍል እንደገለጹት የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ ሌሎች የአውሮፓ መንግሥታት ምንም ዓይነት ምላሽ እንደማይሰጡ አስረድተው፣ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ቆይተው ቅርቡ ወደ ኢጣሊያ የደረሱትን ስደተኞች ለመቀበል የኢጣሊያ መንግሥት የሰጠው በጎ ምላሽ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

በቅርቡ በኢጣሊያ መንግሥትና በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መካከል የተደረሰው ስምምነት በሁለቱ መካከል አዲስ የውይይት መድረክ በመክፈት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል የደቡብ ሮም ክፍለ ከተማ ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ አሌሳንድሮ ሎዩዲቸ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ አሌስንድሮ በማከልም ወደ ፊት ሊጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶች እንዳሉ በመጠቆም እንደተናገሩት የወቅቱ የኢጣሊያ ፖለቲካ በስደተኞች ጉዳይ ላይ ተስፋን የሚሰጥ አቋም እንደሌለው ጠቁመው ይህም በጣሊያን ሕብረተሰብ መካከል ልዩነትን እንደፈጠረ አስረድተዋል።

ስደተኞች ከጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያ ወደ መሀል አገር ይዛወራሉ።

ለአስር ቀን ያህል በባሕር ላይ ከቆዩ በኋላ ወደ ኢጣሊያ ግዛት ወደ ሆነችው ወደ መሲና ከተማ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ስደተኞች በሮም ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኘው ሮካ ዲ ፓፓ ወደተባለ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እንደሚገቡ ክቡር አባ አልዶ ቡዎናዩቶ ተናግረው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአይርላንድ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ቅድስት መንበር ሲመለሱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ስደተኞችን ወደ ኢጣሊያ ግዛት ለማስገባት በኢጣሊያ መንግሥት እና በኢጣሊያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር የተደረሰውን ስምምነት አወድሰው በድርድሩ የተሳተፉትን የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ፋውንዴሽን ተወካይ እና የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤን ማመስገናቸውን ተናግረዋል።

የኢጣሊያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሚና።

ክቡር አባ ቡውናዩቶ ወደ መሃል ሀገር ለሚዛወሩት ስደተኞች የሚሰጠውን የቅድሚያ እርዳታ አስመልክተው እንደተናገሩት ስደተኞቹ ከሁሉ በፊት የጤና ምርመራ እንደሚደረግላቸው ገልጸው ቀጥሎም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሥሯ በሚገኙት ሀገረ ስብከቶች መካከል ለስደተኞች የሚሆን መኖሪያ ቦታዎችን በማፈላለግ፣ በቤተክርስቲያኒቱ ስር ወደሚገኙ በርካታ መንፈሳዊ ተቋማትና እንቅስቃሴዎች፣ ከእነዚህም መካከል ካሪታስ በመባል ወደሚጠራው የእርዳታ መስጫ ማዕከላት እንደሚላኩ አስረድተዋል። ክቡር አባ አልዶ ቡዎናዩቶ በመጨረሻም የኢጣሊያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስደተኞችን ተቀብላ ስታስተናግድ ይህ የመጀመሪዋ እንዳልሆነ ገልጸው እርዳታን ከሚፈልጉ ተረጂዎች ዘወትር የሚቀርብላቸውን ጥያቄ በመቀበል፣ የቅዱስ ወንጌል ምስክርነት በተግባር ለመግለጽ፣ የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ምእመናን ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።   

28 August 2018, 16:51