ፈልግ

የፔሩ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት   የፔሩ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት  

የፔሩ ካቶሊካዊ ጳጳሳት፣ ሕዝቡ ተስፋው እንዳይጨልምበት፣ ሙስናን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

የደቡብ አሜሪካ አገር የሆነችው ፔሩ 197ኛው የነጻነት ቀን አከብራለች። የአገሩ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ ተስፋችንን እንዳያጨልምብን በሃገሪቱ የተስፋፋውን ሙስና መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዜና አጠናቃሪ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የደቡብ አሜሪካ አገር የሆነችው ፔሩ በዛሬው ዕለት 197ኛው የነጻነት ቀን ማክበሯ ታውቋል። በዕለቱም በርካታ ሕዝባዊ ዝግጅቶችም ቀርበዋል። የአገሩ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ ተስፋችንን እንዳያጨልምብን በሃገሪቱ የተስፋፋውን ሙስና መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

የፔሩ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሚገኙበትን አስቸጋሪ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ሞራላዊ ሁኔታን፣ በተለይም ያልተስተካከለ የፍትህ ሥርዓትን ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳት፣ በሁሉም ማሕበራዊ ተቋማት ለውጥ እንደሚያስፈልግ፣ ተቋማት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚያደርጉት ጉዞ ዋስትና እንዲኖራቸው ያስፈልጋል ብለዋል።

የፔሩ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው አጥብቀው እንደገለጹት፣ በድህነት የሚሰቃዩትን እና የሕይወት ዋስትና እና ጥበቃ የማይደረግላቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ እንዳሉ ገልጸዋል። በመሆኑም እያንዳንዳችን፣ ሕግንና ሥርዓትን የሚረዳ ማህበረሰብ በማዘጋጀት የተጣለብንን ሃላፊነት በታማኝነት እና ግልጽነት ባለው መልኩ መወጣት ያስፈልጋል ብለዋል። በማከልም ከበስተጀርባችን በድህነት የሚማቅቁትን እና ምንም የሕይወት ዋስትና የሌላቸውን ዜጎችን ሳንዘነጋ ለጋራ ጥቅም መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዘንድሮ በጥር ወር ላይ ፔሩን በጎበኙበት ወቅት የተናገሩትን መልዕክት ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳት፣ ሙስናን መዋጋት ረጅም ሂደት የሚያስፈልገው እና የሁሉን ዜጋ ተሳትፎን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የቤተ ክርስቲያን እረኞች እንደመሆናችን፣ ለሰው ልጆች በሙሉ ፍቅር የተሞላበት አገልግሎትን በመስጠት ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ባሁኑ ወቅት በአገራቸው እየተበራከተ ለመጣው አመጽ፣ የሕይወት ዋስትና ማነስ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ በድህነት የሚሰቃዩት የበርካታ ዜጎች ሕይወት እንዳሳሰባቸው ገልጸው፣ ከእነዚህ ማሕበራዊ ችግሮች ለመላቀቅ የሕዝቡ ማሕበራዊ እና የግል እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።

የፔሩ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት የነጻነት ቀናቸውን ምክንያት በማድረግ ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው፣ መንግስታቸው እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለ ስልጣናት በሙሉ፣ ከሁሉም በላይ የሕጻናትንና የወጣቱን ማሕበራዊ ሕይወት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ የወደ ፊት ዕጣ ፈንታቸው ያማረ እንዲሆን ለማድረግ ትክክለኛ የፖለቲካ ውሳኔዎችን እንዲወስዱ አሳስበዋል። ወጣቶች በሃገሪቱ የፖለቲካ መሪዎች ላይ ከፍተኛ እምነት ስለጣሉ፣ ተስፋ ቢሶች መሆን የለባቸውም ካሉ በኋላ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በማስታወስ የፔሩ ሕዝብ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ተስፋ እንደሌለው መሆን የለበትም ብለው፣ በፔሩ ሕዝብ ዘንድ የቆየው ሞራላዊ እሴት ተጠብቆ እንዲቆይ በማሳስወብ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።  

26 July 2018, 16:28