ፈልግ

ስደተኛ ሕጻናት ወደ ኢጣሊያ ደርሰው ስደተኛ ሕጻናት ወደ ኢጣሊያ ደርሰው  

በኢጣሊያ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ለስደተኛ ሕጻናት እገዛ እየተሰጠ መሆኑ ተነገረ።

የቅዱስ ዶን ቦስኮ ማሕበር፣ በአራት ትላልቅ የኢጣሊያ ከተሞች ውስጥ 387 ተንከባካቢ የሌላቸው ብቸኛ ሕጻናትን የሚከታተል አንድ የአገልግሎት መስጫ ተቋም በመክፈት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቋል። ሕጻናቱን በማስተማር እና የምክር አገልግሎትን በመስጠት የሚያግዙ የአውራ ጎዳና ላይ መምህራን፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎች እና የነጻ አገልግሎት ሰራተኞች መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅዱስ ዶን ቦስኮ ማሕበር፣ ያለ ተንከባካቢ የቀሩትን ስደተኛ ሕጻናት የሚከታተል የአገልግሎት ዘርፍ ጀመረ። የቅዱስ ዶን ቦስኮ ማሕበር፣ በአራት ትላልቅ የኢጣሊያ ከተሞች ውስጥ 387 ተንከባካቢ የሌላቸው ብቸኛ ሕጻናትን የሚከታተል አንድ የአገልግሎት መስጫ ተቋም በመክፈት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቋል። ሕጻናቱን በማስተማር እና የምክር አገልግሎትን በመስጠት የሚያግዙ የአውራ ጎዳና ላይ መምህራን፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎች እና የነጻ አገልግሎት ሰራተኞች መሆናቸው ታውቋል።

በአንድ ምቾት በሌለበት አዳራሽ ውስጥ ለወራት ያህል ከ120 በላይ ሰዎች ተጠልለው ይገኛሉ። በቂ ውሃ እና ምግብ አያገኙም። ውጭ ቆመው የሚጠብቋቸው ዘቦች እንደፈለጉ ለመውጣት ለመግባት እድል አይሰጧቸውም። አዳራሹ ጽዳት ይጎለዋል። የሚተኙበት የመሬት ላይ ምንጣፍ በተባይ የተወረረ በመሆኑ ሰላማዊ እንቅልፍ አያስተኛቸውም። ከውጭ ሆነው የሚጠብቁን፣ መሣሪያ ታጣቂ ዘቦች አንድ ቀን፣ ጠዋት በማለዳ ከአዳራሹ ወጥተን በአንድ ጀልባ ላይ እንድንሳፈር አደረጉን ያለው፣ የ15 ዓመት ዕድሜ ናይጀሪያዊ ሕጻን፣ በ2007 ዓ. ም. ወደ ኢጣሊያ እንዴት እንደገባ በማስታወስ ገልጿል። ይህ ሕጻን ወደ ኢጣሊያ እንደደረሰ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ለጥቂት ዓመታት ከቆየ በኋላ ካታኒያ በምትባል አንድ የደቡብ ኢጣሊያ ከተማ ውስጥ የጎዳና ላይ ተዳዳሪ ሆኖ ይኖራል። በዚህ መልኩ የሚኖሩ በርካታ ስደተኛ ሕጻናት ያለ ተንከባካቢ፣ በየመንገዱ ዳር ተበራክተው ይታያሉ። ሁኔታው አስከፊ፣ የእነዚህን ሕጻናት ሰብዓዊ ክብር የሚቀንስ መሆኑን በመገንዘብ፣ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከተመሠረቱ የገዳማዊያን ማህበራት መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ ዶን ቦስኮ ማህበር፣ አንድ ፕሮጀችት ከፍቷል። የፕሮጀክቱ መጠሪያ “ታስፈልገኛለህ” ይባላል።

ከሁለት ዓመታት ወዲህ፣ በመጀመሪያ በሮም ከተማ፣ ቀጥሎም በቶሪኖ፣ በናፖሊ እና በካታኒያ ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት፣ የሳለዚያን ዶን ቦስኮ ማሕበር በብሔራዊ ደረጃ ሲያካሂድ ከነበረው ማሕበራዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋሙ ጎን ለጎን፣ በኢጣሊያ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ በየመንገዱ ዳር ተበታትነው የሚገኙትን ጠባቂ እና ተንከባካቢ የሌላቸው ስደተኛ ሕጻናትን የሚረዳ ማሕበር በማቋቋም ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ እንክብካቤዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።

የማሕበሩ ፕሬዚዳንት ክቡር አባ ጆቫኒ ዳንድሬያ እንደገለጹት፣ በጎዳና ላይ የምናገኛቸው ሕጻናት፣ ከወላጆቻቸው የሚሰጣቸውን መደበኛ የአስተዳደግ መንገድና እንክብካቤን ሙሉ በሙሉ ማግኘት የማይችሉ፣ ወላጆቻቸውን ጥለው የተሰደዱ፣ መኖሪያቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ፣ በእንዲህ ዓይነት ሕይወት፣ በየዕለቱ ከባድ ችግር የሚደርስባቸው አስረድተዋል። ክቡር አባ ጆቫኒ በማከልም ብዙን ጊዜ የጎዳና ላይ ሕይወት ለሁሉም የተጋለጠ ነው። የሚተኙትም ሜዳ ላይ በመሆኑ በቀላሉ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል።

እንደ አባ ጆቫኒ ገለጻ መሠረት፣ ማሕበሩ ዘንድሮ በመጀመሪው ግማሽ ውስጥ ያሰባሰቧቸው 387 ሕጻናት ሰዉን በቀላሉ የሚቀርቡ፣ ነገር ግን ከጎዳና ላይ ሕይወት ካካበቱት ልምድ የተነሳ በጥርጣሬ  የተሞሉ በመሆናቸው ልባቸውን ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል። አባ ጆቫኒ፣ የአንድ ሕጻን ገጠመኝ ሲናገሩ፣ ሕጻኑ ብዙ የሚያስቁ፣ የሚቃለዱ ሰዎችን እንደተዋወቃቸው ቢናገርም፣ ከዚህ ሳቅ እና ፈገግታ በስተጀርባ ሁል ጊዜ ጥፊ አይጠፋም ማለቱን አስታውሰዋል። ይህ በመሆኑ እነዚህን ሕጻናት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማቅረብ አስቸጋሪ ቢሆንም ቀስ በቀስ፣ ያለፉትን ከባድ የሕይወት ገጠመኞችን ሳያስታውሷቸው በቀላል ጉዳዮች ውይይት በመክፈት ወደ ሰላማዊ ሕይወት ማድረስ ይቻላል ብለዋል።

ሴቭ ዘ ችልድረን ወይም ሕጻናትን አድን ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅት ዘገባ መሠረት በ2009 ዓ. ም. ወደ ኢጣሊያ የገቡ ሕጻናት ቁጥር 17 ሺህ 337 እንደ ሆኑ ታውቋል። ከእነዚህም መካከል 5000 የሚጠጉ በትላልቅ ከተሞች ውስጥ በሚገኙት መናሄሪያዎች አካካባቢ የሚኖሩ በሆናቸው በየቀኑ በሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወይም ለጾታዊ ጥቃት የተጋለጡ ናቸው። የማሕበሩ ፕሬዚዳንት አባ ጆቫኒ እንደገለጹት እነዚህ ወጣቶች ወደ አውሮጳ ለመምጣት ሲያስቡ የመጀመሪያ ምኞታቸው ሥራ ማግኘት፣ ቀጥሎም ከሚያገኙት የጉልበት ክፍያ ገንዘብ ማጠራቀም ከቻሉ መልሰው ለወላጆቻቸው መላክ፣ ምክንያቱም ወደ ኢጣሊያ ለመምጣት የሚሆን የመጓጓዣ ገንዘብ በብድር ስላገኙ ያንን ብድር መክፈል ስላለባቸው ነው ብለዋል። አንዳንዶቹ በእድሜ ማነስ ምክንያት ወደ ሥራው ዓለም መግባት ስለማይችሉ ለጊዜው በአንድ የማሕበር ቤት ውስጥ እንዲቀመጡ ይደረጋሉ። ነገር ግን ይህን ደንብ ስለማይቀበሉ ወይም ስለማይፈልጉ የተሰጣቸውን የመኖሪያ ስፍራቸውን ጥለው ወደ ጎዳና ሕይወት ይገባሉ።

የጎዳና ላይ ሕይወት የሚኖሩ ሕጻናትን የሚንከባከብ ድርጅት ሕጻናቱን በማስተማር እና የምክር አገልግሎትን በመስጠት የሚያግዙ የጎዳና ላይ መምህራንን፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎችን እና የነጻ አገልግሎት ሰራተኞችን ያቀፈ በመሆኑ አስፈላጊ የሆኑ  የዕውቀትት፣ የስነ ልቦና እና ሊደርስ ከሚችለው ጥቃት የመከላከል አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል። ይህ ከተሟላ በኋላ ቋንቋ እንዲማሩ፣ ማሕበራዊ አገልግሎትን ማግኘት እንዲችሉ የጥገኝነት ወይም የስደተኛ የእውቅና ሰነድ እንዲያወጡ ይደረጋል። ቀጥሎም ወደ ሥራው ዓለም የሚያስገባቸውን የሞያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እንደሚመቻችላቸው ክቡር አባ ጆቫኒ ገልጸዋል። ሆኖም ግን እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉ ከአስር ሕጻናት መካከል አንዱ ብቻ ቢሆንም ማህበሩ ተስፋን ባለመቁረጥ ለሕጻናቱ አማራጮችን በመፈለግ ራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋል ያሉት አባ ጆቫኒ፣ እያንዳንዱ ሕጻን በሁሉም ረገድ መልካም ሆኖ እንዲያድግ ዕድል ስላለው በመምህራኖቻችን በኩል አስፈላጊው እገዛ ይደረግለታል ብለዋል። በመጨረሻም እያንዳንዷ ቀን አዲስ ስለ ሆነች፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ የጸጋ በረከት የሆነው ተስፋ፣ የሕጻናቱን ልብ በመለወጥ ወደ መልካም ሕይወት ይመራቸዋል ብለዋል። 

27 July 2018, 16:08