ፈልግ

ዮርዳኖስ ወደ ግዛቷ የሚያስገባውን የስደተኞች መተላለፊያ ድንበር መዝጋቷ ተነገረ ዮርዳኖስ ወደ ግዛቷ የሚያስገባውን የስደተኞች መተላለፊያ ድንበር መዝጋቷ ተነገረ 

ዮርዳኖስ ወደ ግዛቷ የሚያስገባውን የስደተኞች መተላለፊያ ድንበር መዝጋቷ ተነገረ

ከዓመታት ወዲህ በእርስ በርስ ጦርነት የምትሰቃይ ሶሪያ፣ ዜጎቿ ወደ አጎራባች አገሮች በመስደድ ዕርዳታ ሲያገኙ መቆየታቸው ይታወቃል። ትናንት በተሰራጨው ዜና መሠረት በጦርነት ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው ወደ አጎራባች አገር ወደ ሆነችው ወደ ዮርዳኖስ ለመግባት ለሚሞክሩ ተፈናቃዮች የናሲብ መተላለፊያ ድንበር መዘጋቱ ሃያ ሺህ የሚሆኑ የሶርያ ተፈናቃይ ስደተኞችን በአደጋ ላይ መጣሉ ታውቋል።

ዮርዳኖስ ወደ ግዛቷ የሚያስገባውን የስደተኞች መተላለፊያ ድንበር መዝጋቷ ተነገረ

ዮርዳኖስ ወደ ግዛቷ የሚያስገባውን የስደተኞች መተላለፊያ ድንበር መዘጋቷ የሶርያ ስደተኞችን ሕይወት በከባድ አደጋ ላይ መጣሉ ተነገረ።

ከዓመታት ወዲህ በእርስ በርስ ጦርነት የምትሰቃይ ሶሪያ፣ ዜጎቿ ወደ አጎራባች አገሮች በመስደድ ዕርዳታ ሲያገኙ መቆየታቸው ይታወቃል። ትናንት በተሰራጨው ዜና መሠረት በጦርነት ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው ወደ አጎራባች አገር ወደ ሆነችው ወደ ዮርዳኖስ ለመግባት ለሚሞክሩ ተፈናቃዮች የናሲብ መተላለፊያ ድንበር መዘጋቱ ሃያ ሺህ የሚሆኑ የሶርያ ተፈናቃይ ስደተኞችን በአደጋ ላይ መጣሉ ታውቋል።

ዮሐንስ መኮንን-ቫቲካን

በሶርያ የዳራ ነዋሪዎች ጦርነቱን አምልጠው ወደ ተጎራባች አገር ወደ ሆነችው ወደ ዮርዳኖስ እንዳይገቡ ድንበር ተዘግቶባቸው እንደሚሰቃዩ ታውቋል። ነዋሪዎቹ በሶሪያ ውስጥ ተጥልለው በሚገኙበት ጊዜያዊ መጠለያ በቂ ምግብ፣ ዉሃና የሕክምና እርዳታ የላቸውም ተብሏል። አሁን ተጠልለው በሚገኙበት መጠለያ ጣቢያ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ያሰጋል ተብሏል። መንገዱ ቢቀናቸው ለእነዚህ ተፈናቃዮች ሕይወታቸውን የሚያድኑበት ብቸኛው መንገድ ወደ ዮርዳኖስ መሻገር መሆኑን በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይረክተርና በአካባቢው ጉዳይ ላይ ጥናት በማድረግ ላይ የሚገኙት ወይዘሮ ሊን ማሊፍ ተናግረዋል። መተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ. ም. ባሰራጨው ዘገባ መሠረት ከሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ. ም. ጀምሮ 66 ሺህ የደቡብ ሶርያ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። የዮርዳኖስ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ልዩ ጸሐፊ የሆኑት ሞንሲኞር ዊልሊያም ሾማሊ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት መልስ ዮርዳኖስ ድንበሯን ለሶርያ ስደተኞች ዝግ ማድረጓን በተመለከተ ከዮርዳኖስ መንግሥት መስማት መልካም ይሆናል ካሉ በኋላ፣ አሁን ዮርዳኖስ ያለችበትን ሁኔታ ሲገልጹ፣ ዮርዳኖስ ባሁኑ ጊዜ አንድ ሚሊየን ሶስት መቶ ሺህ ስደተኞችን ወደ ግዛቷ ተቀብላ በማስተናገድ ላይ መሆኗንና ለእነዚህ ተፈናቃይ ስደተኞች በሙሉ የሚያስፈልገውን የምግብ፣ የመጠጥ ውሃ እና የመጠለያ አቅርቦትን በማመቻቸት ላይ መሆኗን ገልጸዋል። እነዚህን የእርዳታ አገልግሎቶችን ለሶርያ ስደተኞች ለማቅረብ በየዓመቱ በሚሊያርዶች  የሚቆጠር ወጪ እንደሚያስወጣት ገልጸዋል። ዮርዳኖስ ይህን ያህል ወጪ በየዓመቱ ስታወጣ ከዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ምንም ዓይነት እርዳታ እንደማታገኝ ስታሳውቅ፣ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች ተጨማሪ በሺህዎች የሚቆጠሩ የሶርያ ተፈናቃዮችን ወደ አገሯ ማስገባቷ እንደሚያደሄት ገልጻለች።

የዮርዳኖስ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ልዩ ጸሐፊ የሆኑት ሞንሲኞር ዊልሊያም ሾማሊ፣ ዮርዳኖስ ለሶርያ ተፈናቃይ ስደተኞች ድንበሯን መዝጋቷን እንደ ብቸኛ መፍትሄ ከመውሰድ ይልቅ፣ ለተፈናቃዮቹ የምግብ፣ የመጠጥ ዉሃ እና የሕክምና አገልግሎት አቅርቦትን ወደ ሶርያ ድንበር ዘልቃ በመግባት ለማዳረስ ጥረት ብታደርግ መልካም ይሆናል ብለዋል። ሞንሲኞር ዊሊያምስ፣ ዮርዳኖስ እነዚህን የዕርዳታ ቁሳቁሶችን ለሶሪያ ተፈናቃዮች ልታቀርብ ብቁ ናት ብለዋል። ዮርዳኖስ ከትናንት ወዲያ፣ ምግብ፣ የመጠጥ ዉሃ፣ መድሃኒቶችንና ሌሎች የዕርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ 65 ወታደራዊ ካሚዮኖችን ተፈናቃዮች ወደ ተጠለሉበት የሶርያ ግዛት መላኳን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዮርዳኖስ ባገሯ የሚገኙ ግለሰቦችንና ማሕበራዊ ድርጅቶችን አስተባብራ ዕርዳታን በማሰባሰብ፣ በሓሽሚታ ማሕበረሰ በኩል ለደቡብ ሶርያ ተፈናቃዮች እንዲደርስ ታደርጋለች ብለዋል። ዮርዳኖስ ይህን በማድረጓ ከሌሎች ዓለም ዓቀፍ ማሕበረሰብ ጋር በመተባበር፣ በጦርነት ለተፈናቀሉ የሶርያ ዜጎች የዕርዳታ እጇን ለመዘርጋት ሙሉ ፍላጎት ማሳየቷን ሞንሲኞር ዊሊያምስ ገልጸዋል። ሞንሲኞር ዊሊያምስ በማከልም፣ ዮርዳኖስ ደሃ አገር በመሆኗ ከሶርያ ለሚሰደዱት ተፈናቃዮች በሙሉ ዕርዳታን የማቅረብ አቅም የላትም። ሌላኛዋ የሶርያ ተጎራባች አገር የሆነች ሊባኖስም ለሶርያ ተፈናቃዮች የዕርዳታን ቁሳቁስ የማቅረብ አቅሟ የተወሰነ ነው። ስለዚህ ለሶርያ ችግር፣ በተለይም በደቡብ ሶርያ ለተቀሰቀሰው ጦርነት ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው የጦርነቱን ምክንያት ለይቶ በማውጣት፣ ጦርነቱ እንዲቆም የሚያደርግ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማግኘት ነው። ጦርነቱ ያስከተለውን ቀውስ ማስታመም ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። በሶርያ ውስጥ ወታደሮቻቸውን ያሰማሩት የአሜሪካ እና የሩሲያ ሃያላን መንግስታት በሕብረት ሆነው በደቡቡ የሶርያ ክፍለ ሃገር የሚፋለሙትን አማጺ ቡድኖችን ማስወጣት ይኖርባቸዋል። ዞሮ ዞሮ የፕሬዚደንት አሳድ ተዋጊ ሃይሎች ድልን እንደሚቀዳጁ እሙን ነው ብለዋል ሞንሲኞር ዊሊያምስ። በደቡብ ሶርያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ካልተገታ አሁንም ቢሆን ተጨማሪ የሰው ሕይወት ይጠፋል። ስለዚህ ፖለቲካዊ መፍትሄን ከማግኘት ሌላ አማራጭ አይኖርም። ዮርዳኖስም በበኩልዋ ጦርነቱ እንዲያከትም በዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ላይ ጫና እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።

ሞንሲኞር ዊሊያምስ በመጨረሻም የዮርዳኖስ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ከዓለም ዓቀፉ ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅትና ከብሔራዊ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በጎ አድራጊ ድርጅት ከሚገኘው እርዳታ በመታገዝ፣ በዮርዳኖስ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን የኢራቅ ተፈናቃይ ስደተኞችን በመርዳት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።    

05 July 2018, 11:04