ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዩክሬን የሰላም ስብሰባ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዩክሬን የሰላም ስብሰባ ላይ  (ANSA)

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለዩክሬን ሰላም ስብሰባ ላይ የሩስያ አለመገኘት ጉባኤውን ጎዶሎ ያደርገዋል አሉ

በጣሊያን የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ሰላም ለመፍጠር በተዘጋጀው ዝግጅት ጎን ለጎን ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ለዩክሬን ሰላም ለማምጣት በተካሄደው የከፍተኛ ደረጃ የሰላም ጉባኤ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በስዊዘርላንድ በሳምንቱ መጨረሻ ለዩክሬን ሰላምን ለማምጣት ታስቦ የተካሄደውን ከፍተኛ የሰላም ጉባኤን “ጠቃሚ” ሲሉ ገልጸው፣ ነገር ግን “በብዙዎቹ ተሳታፊዎች እንደተነገረው የሩስያ በጉባኤው አለመገኘት ጥረቱን ጎዶሎ ያደርገዋል” ካሉ በኋላ፥ “ሰላም ሁል ጊዜ የሚመጣው በአንድነት ሲሰራ ነው” ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው የኢጣሊያን የህግ አውጪዎች ምክር ቤት ለሰላም ግንባታ በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም ወቅት የቫቲካን ልዑካንን በመምራት በታዛቢነት የተገኙበትን በስዊዘርላንድ ሉሴርኔ ከተማ ላይ የተደረገውን ጉባኤ አስመልክተው አስተያየት ሰጥተዋል።

ሰላም እና የወንድማማችነት መርህ ብቻ

“ከብዙዎች ሰምቻለሁ እናም ሃሳቡን ወድጃለሁ፥ እኛ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ እንዳልሆንን እና እዚህ የመጣነው በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሰላም መንገድ ለመፈለግ ነው” ብለዋል ካርዲናሉ።

ሰላም ከሚለው ቃል ጋር የተቆራኘውን “ትክክለኛ” የሚለውን ቅጽል አስፈላጊነት በመድገም፥ “ትክክለኛ ሰላም... በዓለም አቀፍ ህግ መርሆዎች ላይ የተመሰረተ እና የተባበሩት መንግስታት ቻርተርን በጥብቅ የተከተለ ነው” ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናሉ በመቀጠል፣ “በሥርዓቶች ውስጥ ተጨባጭ የሆነ አተገባበርን የሚያስገኝ በወንድማማችነት መርህ፣ በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ ወንድማማቾች ለመሰማማት ጥረት ካላደረግን በፍፁም ግጭቶችን ማሸነፍ አንችልም” ብለዋል።

እምነት ማጣት

የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሉት “ዛሬ ላይ የሚያጋጥመን ትልቁ ችግር ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጥቂት ብቻ ካልሆነም ጨርሶ በጉዳዩ ላይ እየሰሩ አይደለም፥ ይህ ደግሞ ፍጹም የጋራ መተማመንን ያሳጣል፥ ከእንግዲህ በኋላ እርስ በርስ መተማመን አንችልም፥ ለዚያም ነው የተለመዱ እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች እየጨመሩ ያሉት፥ ብሎም ሁሉም ሰው እራሱን ከማያምኑት እና ከማያከብሩት እየተከላከለ መሆኑን ማረጋገጥ የሚፈልገው” ብለዋል።

የጦር መሳሪያ ንግድን የሚያባብሱ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች

ብጹእ ካርዲናሉ ከጦር መሣሪያ ንግዱ ጀርባ “ትልቅ የኢኮኖሚ ፍላጎቶች አሉ” በማለት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን አባባል በማስተጋባት፥ መንግስታት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዳንድ መስማት የማይፈልጓቸው ቃላት ያሉ ይመስላል፥ የግብይት መመዘኛዎች ቡድኖችን እና መንግስታትን ሲመሩ፡ “ሊቃነ ጳጳሳቱ የጦር መሳሪያ በብዛት መሰራጨት እንዲቆም ጥሪ ማድረጋቸው ምክንያታዊ ነው፣ ነገር ግን በእርግጥ ይህ ጥሪ አይሰማም” ብለዋል ካርዲናል ፓሮሊን።

“ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጥሪያቸውን አጥብቀው በመቀጠላቸው ቆራጥ ናቸው፥ ይሄንን ጭብጥ በተደጋጋሚ አጥብቀው ይናገራሉ፥ እናም ቀስ በቀስ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

የድጋፍ እጆች ወደ ዩክሬን

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለዩክሬን ድጋፍ ስለ ማድረግ ላይ በጣሊያን ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ስላለው ክርክር ሲጠየቁ፥ ይህንን ችግር ለመፍታት ብቸኛው መንገድ አንድ ላይ መሰብሰብ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ውይይት መጀመር ነው፥ ይህ ከሆነ ብቻ የጦር መሳሪያ መላክን ማቆም ይቻላል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሉት የመጀመሪያው እርምጃ በሁለቱ ወገኖች ማለትም ሩሲያ እና ዩክሬን መካከል በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት እና ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ድርድር መጀመር አለበት ብለዋል።

ስለዚህ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የውይይት ጠረጴዛ ላይ አለመገኘታቸው በእርግጠኝነት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፥ “ሰላም የሚመጣው በሁለቱም ሃገራት ጥረት ነው፣ ካልሆነ ግን አንዱ ካልተሳተፈ ሰላም ሊኖር አይችልም” ብለዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን በጣሊያን ውስጥ ሕግ የሆነውን “የተለያየ የራስ ገዝ አስተዳደር” ጉዳይንም በማንሳት በክርክሩ ላይ እንዳልተሳተፉ ገልጸው “በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስጠት የለብንም፣ እነሱ ጣሊያናዊ ናቸው፥ እኛ ጣልቃ ለመግባት የተለየ ብቃት የለንም” ካሉ በኋላ፥ ይሁን እንጂ “አንድነትን ለማጎልበት የሚረዳ ማንኛውም ነገር ጥሩ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የሊባኖስ ጉብኝት

በመጨረሻም ካርዲናሉ በሊባኖስ መገናኛ ብዙሃን እንደተነገረው በሊባኖስ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ጉብኝት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የሊባኖስ ጉብኝታቸው በቅርብ ጊዜያት ከእስራኤል ጋር በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የግጭት አቅጣጫ የሚቀይር በሚመስለው ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ወይም በቅድስት ሀገር የሰላም ተልእኮ እንዳልሆነ የተናገሩት ካርዲናሉ፥ “በአካባቢው የሚገኙ ‘ኦርደር ኦፍ ማልታ’ የተባለው ማህበር ሃላፊዎች ሥራቸውን እንድጎበኝ ጋብዘውኝ ነው፥ ማህበሩ በሊባኖስ ውስጥ በተከሰተው ቀውስ ምክንያት በተፈጠረው ማህበራዊ ቀውስ ላይ ትልቅ ሥራ እየሰራ ይገኛል፥ የሊባኖስ ቀውስ አስቸጋሪ ነው፣ በእርግጠኝነት የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ ሁሌም እንደሚያደርገው፥ ተቋማዊ መፍትሔ ለማግኘት የተቻለንን ለማገዝ እንሞክራለን ብለዋል።

ሰላም ለማግኘት ያለው ተስፋ

ብጹእ ካርዲናል ፓሮሊን በህግ መወሰኛ ምክር ቤት ከተደረገው ውይይት በኋላ ከብፁዕ ካርዲናል ማትዮ ዙፒ ጋር በመሆን ለሰብአዊ እና ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች በተዘጋጀ ዘርፈ ብዙ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈው፣ በዚሁ አጋጣሚ በድጋሚ ስለ ሰላም ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል።

የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አንድምታ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ግጭቶች እየሰፉ፣ እየተወሳሰቡ፣ እየጠነከሩ ይሄዳሉ የሚል ሥጋት ያለበት ማንኛውም ሁኔታ ከፍተኛ ያለመረጋጋትን ይፈጥራል” ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጂ7 የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሳተፍን እና በስዊዘርላንድ በተካሄደው የሰላም ጉባኤ ላይ መገኘታቸውን ጨምሮ በቅርቡ የተደረጉት ዝግጅቶችን አስመልክተው “የተዘራው ዘር ፍሬ አፍርቶ አንድ ነገር ሊያመጣ ይችላል” በማለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ቀርበው ንግግር ያደረጉት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን “በጦርነት በተከበብንበት በዚህ ጊዜ የሰላምን ጉዳይ ልብ ልንል ይገባል” ሲሉ ለሁሉም ክርስቲያኖች ጥሪ አቅርበዋል።

“ሰዎች ተስማምተው እንዳይኖሩ በሚከለክላቸው የጦርነት ደመናዎች የብዙ አገሮች ሰማይ ጨልሟል” ያሉት ካርዲናሉ፣ “በዓለማችን ላይ አዳዲስ ጦርነቶች መበራከታቸውን እና በርዕዮተ ዓለም አቋሞች ላይ የመጋጨት አዝማሚያን እያየን ነው” ብለዋል። ስለዚህ “ፍትሕን እና ፖለቲካን የሚያስተዳድሩትን በወንጌል እና በስነምግባር መርሆች ተመርተው በዘላቂነት እንዲሰሩ ለማነቃቃት” ቁርጠኝነት ያስፈልጋል” ብለዋል።

“የማግለል አስተሳሰብን እና ጭፍን ጥላቻን የሚያባብሱ አመለካከቶችን በማስወገድ ወጣቶችን ወደ አካታችነት ባህል እንዲመጡ ማስተማር መጀመር እንደሚያስፈልግ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ብጹእ ካርዲናል ፓሮሊን በመጨረሻም “እጣ ፈንታችን ሞት ሳይሆን ሕይወት ነው፣ ጥላቻ ሳይሆን ወንድማማችነት ነው፣ ግጭት ሳይሆን ስምምነት ነው፣ ሰላም የምድርን ሁሉ ዕጣ ፈንታ የሚያበራና የሚመራ ኮከብ ነው። የእግዚአብሔርን አሰራር የሚያሰናክል እና የሰውን ልጅ ክብር የሚያራክስ መሳሪያ ከእጃችን ላይ የወደቀ ይሁን” በማለት ደምድመዋል።
 

20 June 2024, 14:05