ፈልግ

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከበር ያደረጉት የዓለም የወጣቶች ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከበር ያደረጉት የዓለም የወጣቶች ቀን  

ብጹዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ፥ የዓለም የወጣቶች ቀን አስፈላጊነት ዛሬም ከፍተኛ እንደሆነ ገለጹ

በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ ዴ ማንዶካ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ከተመሠረተ 40 ዓመታትን ማስቆጠሩን ገልጸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1984 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን አስፈላጊነቱ ዛሬም ቢሆን ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፥ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተጀመረው ይህ እንቅስቃሴ ያስገኛቸውን በርካታ ፍሬዎች አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የዓለም ወጣቶች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከበር ታላቅ ተነሳሽነት የሰጣቸውን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ፥ እንዲሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓላትን ከዓለም ወጣቶች ጋር በኅብረት ማክበራቸውን በማስታወስ፥ በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ ዴ ማንዶካ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ ምስጋናቸውን ያቀረቡት፥ ከአርባ ዓመታት በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 14/1984 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተከበረውን የዓለም የወጣቶች ቀን ለማስታወስ ሮም ውስጥ በሚገኝ በቅዱስ ሎውረንስ ማዕከል ቅዳሜ ሚያዝያ 5/2016 ዓ. ም. ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ እንደ ነበር ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ንግግር፥ የዓለም የወጣቶች ቀናት ብዙ የተስፋ፣ የፍቅር እና የወጣቶች ፍሬ በቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥ እንዲፈጠር ማድረጉን አፅንዖት ሰጥቷል።

በቅድስት መንበር የባህል እና የትምህርት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ሃላፊው በእለቱ ለወጣቶች እንደተናገሩት፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ወደ እኔ ቅረቡ፣ ንኩኝ፣ እዩኝም’ በማለት ሁሉንም ይጋብዛል” ብለዋል። “ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ፥ የክርስቶስ አስፈላጊነት ረቂቅ ጽንሰ-ሃሳባዊ እውነት ሳይሆን በእጃችን ነክተን የተረዳነው ነው” በማለት ገልጸዋል።

በዓለም የወጣቶች ቀናት፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣቶች አማኞች የመሆናቸውን ደስታ፣ የሰውን ወንድማማችነት በመገንዘብ፣ በመተቃቀፍ፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በመደማመጥ፣ በመሳቅ እና በለቅሶ ይህንን የቤተ ክርስቲያንን ተሞክሮ ተረድተው በደስታን እንደሚለማመዱት ገልጸዋል።

“ይህም ሕይወትን ይለውጣል፣ የታላላቅ ሰዎች ታሪክንም ለውጧል፤ የእኛንም የሕይወት ታሪካችንን መለወጥ ቀጥሏል” በማለት አስረድተዋል። “ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልካቾች ብቻ እንድንሆን አይፈልግም፤ በዓይናችን አይተናል፣ በጆሮአችን ሰምተናል፣ በእጃችንም ነክተናል” የምንል ምስክሮቹ እንድንሆን እንደሚፈልግ እና ይህም የወንጌል መልዕክተኛ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያደርገን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶች ታሪክ ሲያልፍ ቆመው የሚመለከቱ ሳይሆን ነገር ግን በታሪክ መካከል የምሥራች እንዲናገሩ መጠየቃቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ወጣቶች የመጀመሪያዎቹ የወንጌል መልዕክተኞች ናቸው” ማለታቸውን ጠቅሰዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ ቁስሎቻችሁን ይፈውሳል፣ አዲስ አድማስን ይከፍትላችኋል፣ የሞትን ባሕል ሳይሆን የሕይወት ባሕል እና የፍቅርን ሥልጣኔ እንድትገነቡ ያደርጋችኋል” ብለው፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እያንዳንዱን የዓለም የወጣቶች ቀንን እንደ ማመሳከሪያ በመውሰድ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመመልከት የምትረዳን መሆኑን ብፁዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ ደ ሜንዶንቻ ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ ዴ ማንዶካ፣ በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ከሆኑት አቶ ግለይሰን ዴ ፓውላ ሱዛ እና በቅዱስ ሎውረንስ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከሚሰጥ የሻሎም ማህበረሰብ አባላት ጋር በመሆን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርበዋል። በማግሥቱ እሑድ ሚያዝያ 6/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ሎውረንስ ማዕከል የካህናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ብፁዕ ካርዲናል አልዓዛር ዩ ሄንግ-ሲክ መሪነት የቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል።

ከመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት በኋላ ከአርባ ዓመታት በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1984 ዓ. ም. በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተነሳሽነት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ የተገኙት በርካታ ሰዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል።

ቀጣዩ የዓለም ወጣቶች ቀን በደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2027 ዓ. ም. የሚከበር ሲሆን፥ ከዚያ በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2025 ዓ. ም. በጣሊያን ሮም ላይ የወጣቶች ኢዮቤልዩ እንደሚከበር ይጠበቃል።

15 April 2024, 17:17