ፈልግ

የዩክሬይን እና የሩስያ ጦርነት ቀውስ የዩክሬይን እና የሩስያ ጦርነት ቀውስ  (AFP or licensors)

ቫቲካን በሰው ልጅ ክብር ላይ የሚፈጸሙ የከባድ ጥሰቶች ዝርዝር አዲስ ሠነድ ይፋ አደረገ

በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ለማዘጋጀት አምስት ዓመታትን የወሰደ እና ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ስለ ጦርነት፣ ስለ ድህነት፣ በስደተኞች እና በሴቶች ላይ ስለሚደርስ የመብት ጥሰት፣ ስለ ውርጃ እና ስለ ማዕጸን ኪራይ፣ በሕክምና እገዛ ስለሚፈጸም የነፍስ ማጥፋት፣ ስለ ሥርዓተ-ጾታ ፅንሰ-ሃሳብ እና የዲጂታል ጥቃትን በማስመልከት የቀረቡ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮዎችን መሠረት ያደረገ፥ ‘Dignitas infinita’ ወይም “ገደብ የለሽ የሰው ልጅ ክብር” የተሰኘ አዲስ ሠነድ ይፋ አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሦስት ምዕራፎች ያሉት ይህ ሠነደ በሰው ልጅ ክብር ላይ የሚፈጸሙ አንዳንድ ከባድ ጥሰቶችን ለሚዘረዝረው አራተኛው ምዕራፍ መሠረት የሚጥል ሲሆን ይህም በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ላዘጋጀው፥ ‘ዲግኒታተስ ኢንፊኒታ’ ወይም “ገደብ የለሽ የሰው ልጅ ክብር” የተሰኘ አዲስ ሠነድን፣ የዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ 75ኛ ዓመትን የሚያስታውስ እና በክርስቲያናዊ የሰው ልጅ ጥናት ውስጥ የሰብዓዊ ክብር አስፈላጊነትን እንደገና የሚያረጋግጥ ነው።

የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የአምስት ዓመት ሥራ ፍሬ የሆነው ይህ ሠነድ ዋና አወቃቀሩ የቅርብ ጊዜ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮዎች በሕክምናው እና በሕይወት ሳይንስ ዘርፎች ላይ የሚነሱትን ፍልስፍናዊ፣ ማኅበራዊ እና ሕጋዊ ጉዳዮችን የሚያጠኑ በርካታ የሥነ-ምግባር ወይም የ “ባዮኤቲክስ” ጥናቶች ቁልፍ ጭብጦችን አካትቷል። ሠነዱ በውስጡ ከያዛቸው ከባድ የሰው ልጅ ክብር ጥሰቶች ዝርዝር ከተጠቀሱት መካከል ውርጃ፣ በሕክምና እገዛ የሚፈጸም ነፍስ ከማጥፋት እና ከማዕጸን ኪራይ ጎን ለጎን ጦርነት፣ ድህነት እና ሕ-ገወጥ የሰዎች ዝውውር እንደ የሰው ልጅ ክብር ጥሰቶች ተዘርዝረዋል።

አዲሱ ሠነድ በሰው ሕይወት መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ ብቻ በማትኮር በሰው ልጅ ክብር ላይ የሚሰነዘሩ ሌሎች ጥቃቶችን የሚዘነጋ እና ለስደተኞች ጥበቃ እና ለፅንስ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ ሊደረግለት በሚገባው እንክብካቤ ላይ በሚያተኩሩ አስተምህሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስወገድ አስተዋፅዖ የሚያደርግ ነው።

መሠረታዊ መርሆች

ሠነዱ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ክፍሎች አማካይነት መሠረታዊ መርሆችን የሚያስታውስ ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያን በራዕይ ብርሃን በመታገዝ “በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን እና በኢየሱስ ክርስቶስ የተዋጀውን የሰው ልጅ ስብዕናን በቆራጥነት ደግማ ያረጋገጠችበት ነው” (1)።

ይህ የሰው ልጅ የማይገረሰስ ክብር ከሁሉም የባህል ለውጦች በስተቀር ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የሚዛመድ እንደሆነ ተገልጿል (6)። ሰብዓዊ ክብር የእግዚአብሔር ስጦታ በመሆኑ ገና ያልተወለደ ሕጻን፣ የማገናዘብ ችግር ያለበት ሰው ወይም በዕድሜ ብዛት ሕመም ውስጥ የሚገኝ አረጋውያንም የሚጋሩት ነው (9)።

“ቤተ ክርስቲያን የሰዎች የኑሮ ሁኔታ ወይም ባሕሪያቸው ምንም ይሁን ምን ሁሉም ሰዎች እኩል ክብር እንዳለው ትመሰክራለች” (17)። ይህንንም የምታደርገው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጽ መሠረት ሴቶች እና ወንዶች በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ መሆናቸውን በማስተማር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን በመልበሱ “የሥጋን እና የነፍስን ክብር አረጋግጧል” (19)። በትንሳኤውም የሰው ልጅ ከሁሉም በላይ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን ለመፍጠር መጠራቱን ገልጾልናል (20)።

የእያንዳንዱ ሰው ክብር

ሠነዱ “ሰብዓዊ ክብር” በሚለው እና “የግል ክብር” በሚለው አገላለጽ መካከል ያለውን አለመግባባት አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን፥ “የግል ክብር” የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች “አንድ ሰው 'ማመዛዘን የሚችል' እንደሆነ ብቻ በማለት ስለሚረዱት ነው" (24)።

በመሆኑም በእነርሱ ግንዛቤ “በማህፀን ውስጥ ያለ ወይም ገና ያልተወለደ ሕጻን የግል ክብር እንደሌለው፣ በሌሎች ላይ ጥገኛ ሆኖ የሚኖር የዕድሜ ባለጸጋ ወይም የአእምሮ ሕመም ያለበት ሰው የግል ክብር እንደሌለው ያስባሉ። ቤተ ክርስቲያን በተቃራኒው የእያንዳንዱ ሰው ክብር ውስጣዊ በመሆኑ በሁሉም አጋጣሚዎች እና ሁኔታዎች ውስጥ ጸንቶ እንደሚኖር” (24) ትናገራለች ።

ሠነዱ በተጨማሪም “የሰብዓዊ ክብር ጽንሰ-ሃሳብ አልፎ አልፎ የአዳዲስ መብቶች መበራከትን ለማስረዳት በዘፈቀደ ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጾ፥  እያንዳንዱን የግል ምርጫ ወይም ፍላጎትን የመግለፅ እና የመገንዘብ ችሎታ መረጋገጥ አለበት” (25) ሲል አጽንዖት ሰጥቷል።

የጥሰት ዓይነቶች ዝርዝር

አንዳንድ በሰው ልጅ ክብር ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ጥሰቶችን በዝርዝር ያቀረበው ሠነዱ ቀጥሎም፥ እንደ ግድያ፣ ዘር ማጥፋት፣ ፅንስ ማስወረድ እና ሆን ተብሎ ራስን ማጥፋት በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሁሉ የሰውን ክብር የሚጻረሩ እንደሆኑ መታወቅ እንዳለበት እንዲሁም አካላዊ እና አእምሮአዊ ስቃይ ባድረስ ተገቢ ያልሆነ የሥነ-ልቦና ጫና እንደሆነ ያስረዳል።

ሠነዱ ከሰው ሕይወት በታች የሆነ የኑሮ ሁኔታ፣ የዘፈቀደ እስራት፣ ከአገር መባረር፣ ባርነት፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ የሴቶች እና የሕጻናት ሽያጭ፣ ለግለሰቦች ነጻነት እና ኃላፊነት ቅድሚያን ከመስጠት ይልቅ ትርፍን ለማግኘት ሲባል የሚደረጉ የጉልበት ብዝበዛዎች የመሳሰሉ በሰው ልጅ ክብር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ያጠቃልላል። “ሁኔታው ምንም ይሁን ምን የእያንዳንዱን ሰው የማይገሰስ ክብር የሚጥስ በመሆኑ የሞት ቅጣትም በሰው ልጅ ክብር ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደሆነ ተጠቅሷል (34)።

ድህነት፣ ጦርነት እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር

ድህነትን በማስመልከት የተጠቀሰው የመጀመሪያው ነጥብ፥ “በዘመኑ ካሉት ታላላቅ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች መካከል አንዱ” (36) እና ከዚያም ቀጥሎ “የሰውን ክብር የሚክድ እና ዘወትር ሽንፈትን ብቻ የሚያተርፍ ሌላው አሳዛኝ ተግባር ጦርነት” (38) ሲሆን ይህም “ሊሆን የሚችለውን ለመናገር ቀደም ባሉት ዘመናት ውስጥ የተብራሩትን የፍትሃዊ ጦርነቶች ምክንያታዊ መመዘኛዎች መጥራት በአሁኑ ጊዜ ከባድ ሆኗል” (39)።

በስደተኞች ላይ ስለሚደርስ ስቃይ የሚያብራራው ሠነዱ፥ “ሕይወታቸው አደጋ ላይ የሚወድቅበት ምክንያት ቤተሰብ ለመመሥረት፣ ለሥራ ወይም እራስን ለማስተዳደር የሚያስችል መንገድ ባለመኖሩ” መሆኑን ይገልጻል (40)።

ሠነዱ በመቀጠልም በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በተጨባጭ እየታየ ያለ አስነዋሪ ተግባር እና ሰለጠንን በሚሉ ማኅበረሰቦች የሚፈጸም አሳፋሪ ተግባር” መሆኑን ከመግለጽ በተጨማሪ በዝባዦች እና ደንበኞቻቸው የህሊና ምርመራ እንዲያደርጉም ይጋብዛል (41)።

ሠነዱ እንደዚሁም የአካል ክፍሎች እና ሕብረ ሕዋሳት ግብይትን፣ የወንዶች እና የሴቶች የፆታ ብዝበዛን፣ የጉልበት ብዝበዛን፣ ሴተኛ አዳሪነትን ጨምሮ የአደንዛዥ ዕፅ እና የጦር መሣሪያ ንግድን፣ ሽብርተኝነትን እና የተደራጁ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን መዋጋት እንደሚያስፈልግ ያሳስባል (42)።

ጾታዊ ጥቃትን የጠቀሰው ሠነዱ በተጨማሪም ይህም “በሚሰቃዩ ሰዎች ልብ ውስጥ የማይጠፋ ጠባሳን ትቶ እንደሚያልፍ ገልጾ፥ ዕድሜ ልክ ሊቆዩ የሚችሉ እና በምንም መንገድ ሊፈውሱ የማይችሉ መከራዎች” (43) መሆናቸውን ገልጿል።

ከዚያም በሴቶች ላይ በሚደርስ መድልዎ እና ጥቃት ላይ የተወያየው ሠነዱ፥ ከእነዚህም መካከል በእናት እና በልጅ ላይ ተጽእኖን የሚያሳድሩ አስገዳጅ ውርጃዎች፣ ብዙውን ጊዜ የወንዶችን ራስ ወዳድነት ለማርካት ሲባል የሚፈጸም ከአንድ ሴት በላይ ጋብቻ” (45) የተዘረዘረ ሲሆን፥ በሴቶች ላይ የሚፈጸም የግድያ ተግባርንም ያወግዛል (46)።

ፅንስ ማስወረድ እና ቀዶ ጥገና

ጠንከር ያለው የፅንስ ማቋረጥ ውግዘቱ፥ በሕይወት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል በተለይ ከባድ እና አሳፋሪ ባህሪያት ያሉት ፅንስ ማስወረድ፥ በማሕጸን ውስጥ ለሚገኝ ገና ላልተወለደ ሕጻን ሊደረግ ከሚገባው ጥበቃ እና ከእያንዳንዱ እና ከሁሉም ሰብዓዊ መብቶች ጋር በቅርበት የተሳሰረ ነው” (47) የሚል እውነታም ተጠቅሷል ።

“ከፍተኛ ክብር የሚጠው እና በማሕጸን ውስጥ የሚገኝ ሕጻን እንደ ተራ ነገር ተቆጥሯል” ያለው ሠነዱ፥ ይህ “የሴቷን እና የልጁን ክብር የሚጋፋ ከባድ ጥሰት እንደሆነ ገልጾ፥ አንድ ሕጻን ዘወትር የእግዚአብሔር ስጦታ እና በፍጹም ለንግድ ስምምነት ሊቀርብ የማይችል መሆኑን አስረድቷል (48)።

አንዳንድ ሕጎች ግራ በሚያጋባ መልኩ፥ “በክብር መሞት” በሚለው አተረጓጎማቸው፥ በሕክምና እገዛ ራስን ማጥፋት “ኢውታናሲያ” ን ከዝርዝሮቹ መካከል የጠቀሰው ሠነዱ፥ “ስቃይ ሕሙማን ክብራቸውን እንዲያጡ እንደማያደርግ እና ክብራቸው ውስጣዊ እና የማይነጣጠል እንደሆነ” ገልጿል (51)።

ሠነዱ በመቀጠልም የፈውስ መድኃኒት ለሌላቸው ሕመሞች የሚደረግ የማስታገሻ እንክብካቤ አስፈላጊነትን አስታውሶ፥ ተመጣጣኝ ያልሆኑ የሕክምና ሂደቶችን ስለማስወግ ተናግሯል። በሕይወት መኖር እንጂ መሞት መብት ባለመሆኑ ሞት በሕክምና መታገዝ እንደሌለበት ያረጋግጣል (52)። ሌላው ከባድ የሰው ልጅ ክብር ጥሰት፥ አቅም ደካማ የሆኑ ሰዎችን ማግለል እንደሆነ ገልጿል (53)።

የሥርዓተ-ፆታ ጽንሰ-ሐሳብ

ሠነዱ በግብረ ሰዶማውያን ላይ የሚፈጸመው ኢ-ፍትሃዊ የአድሎ ምልክት በሙሉ፥ “በተለይም ማንኛውም ዓይነት ጠብ እና ጥቃት በጥንቃቄ መወገድ አለበት” በማለት ይህን ርዕሥ እስመልክቶ ይገልጻል። በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በፆታዊ ዝንባሌያቸው ብቻ የሚታሰሩት፣ የሚሰቃዩት አልፎ ተርፎም ጥቅማ ጥቅሞችን የሚነፈጉ መኖራቸው “ከሰው ልጅ ክብር ጋር የሚጋጭ ነው” ሲል ሠነዱ ይገልጻል (55)። የሥርዓተ-ፆታ ፅንሰ-ሃሳብ “እጅግ አደገኛ የሚሆነው ሁሉንም ሰው እኩል የሚያደርገውን የይገባኛል ጥያቄ ስለሚሰርዝ ነው” (56)።

ቤተ ክርስቲያን “የሰው ሕይወት በሁሉም ዘርፍ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ረገድ የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ፥ ይህን ስጦታ ከምስጋና ጋር መቀበል እና ለበጎ አገልግሎት ማዋል እንደሚገባ ታስታውሳለች። የሥርዓተ-ፆታ ፅንሰ-ሃሳብ እንደሚገልጸው ራስን ፈጣሪ ማድረግ ከቆየ ዘመን ፈተና ጋር መስማማት ማለት ነው” (57)። የሥርዓተ-ፆታ ፅንሰ-ሃሳብ “በሕያዋን ፍጥረታት መካከል ሊኖር የሚችለውን ታላቅ የፆታ ልዩነት ለመካድ ያለመ ነው” (58)። ስለዚህ “በወንድና በሴት መካከል ያለውን የማይሻር የፆታ ልዩነት ለማድበስበስ የሚደረጉ ሙከራዎች ሁሉ ተቀባይነት የላቸውም” (59)።

ጾታን መለወጥ

“የሰው ልጅ ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ያገኘውን ልዩ ክብር አደጋ ላይ የሚጥል” ስለሆነ በአሉታዊ መልኩ ይገመገማል። ይህ ማለት ግን ያለውን ዕድል አያካትትም ማለት ሳይሆን ነገር ግን “በወሊድ ጊዜ በግልጽ የሚታዩ ወይም ከጊዜ በኋላ የሚከሰት የብልት መዛባት እና ያልተለመዱ ችግሮችን ለመፍታት የጤና ባለሙያዎችን ዕርዳታ መጠይቅ ይቻላል” (60)።

የዲጂታል ጥቃት

ሠነዱ በዝርዝሩ ላይ ያስቀመጠው የመጨረሻው ርዕሥ፥ “ዲጂታል ጥቃት” ሲሆን፥ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት እየተሰራጩ የሚገኙ አዳዲስ የጥቃት ዓይነቶች እንደ ሳይበር ጥቃት ያሉ እና “በድረ ገጽ በኩል የሚሰራጩ የብልግና ምስሎች እና ሰዎችን ለወሲብ ወይም ለቁማር ዓላማ በማዋል የሚበዘብዙበት ናቸው” (61)።

ሠነዱ በመጨረሻም “ለሰው ልጅ የሚሰጥ ክብር ከሁሉም በላይ ለጋራ ጥቅም ለሚደረግ ቁርጠኝነት እና የእያንዳንዱ የሕግ ሥርዓት ማዕከል ሊሆን ይገባል” (64) በማለት ያጠቃልላል።

 

09 April 2024, 17:31