ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በካናዳ ከሚገኙ ነባር ተወላጆች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በካናዳ ከሚገኙ ነባር ተወላጆች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት 

ቅድስት መንበር የነባር ህዝቦች ተወላጅ የሆኑ ወጣቶችን እንደ ባህል ጠባቂ አድርጋ እንደምታይ ገለጸች

ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በኒውዮርክ በተካሄደው በነባር ህዝቦች ጉዳዮች ላይ በሚመክረው የተባበሩት መንግስታት 23ኛው ቋሚ ስብሰባ ላይ የተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹእ አቡነ ገብርኤሌ ካቺያ በሰጡት መግለጫ፣ ተወላጆችን በተለይም ወጣቶችን መደገፍ እና የውይይት ልምድን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብጹእ አቡነ ካቺያ ማክሰኞ ዕለት በኒውዮርክ በተካሄደው 23ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የተወላጆች ቋሚ ፎረም ላይ ንግግር አድርገዋል።

ስብሰባው “በተባበሩት መንግስታት የነባር ህዝቦች መብት ድንጋጌ ላይ በመንተራስ የአገሬው ተወላጆች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ማሳደግ፡ የአገሬው ተወላጆችን ድምፅ ማጉላት” በሚል መሪ ሃሳብ ነበር የተደረገው።

ሊቀ ጳጳሱ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ ቅድስት መንበር ለቋሚ ፎረሙ በነባር ህዝቦች ጉዳዮች ላይ ላከናወነው ተግባር እውቅና እንደሰጠች በመግለጽ፥ በዚህ ዓመት ቅድሚያ በተሰጠው መሪ ሃሳብ ላይ አንዳንድ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የነባር ተወላጆች መብቶች ድንጋጌ (UNDRIP) በመጥቀስ፥ “የአገሬው ተወላጅ ወጣቶች የአሁኑ እና የወደፊት ባህላቸው ጠባቂ በመሆን የሚጫወቱትን ሚና” የመገንዘብ አስፈላጊነትን ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ፍትሃዊ እና ሰብአዊነት የሰፈነበት ዓለም ለመገንባት የአገሬው ተወላጅ ወጣቶች መገለልን፣ ብክነትን እና ድህነትን በመዋጋት ባህላቸውንና ወጎቻቸውን እንዲጠብቁ ማበረታታታቸውን አስረድተዋል።

ወጣቶች ባህል ጠባቂ እና ድልድይ ናቸው

የቫቲካኑ ዲፕሎማት የነባር ህዝቦች ተወላጅ የሆኑ ወጣቶች በባህል መስክ ሊያበረክቱት ስለሚችሉት አስተዋፅኦ በማንሳት፥ “ባህላዊ እሴቶቻቸውን በመጠበቅ እና በማደስ ላይ በንቃት መሳተፍ እንዲሁም የራሳቸውን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸው ላይ ወሳኝ የሆኑትን የማህበረሰባቸውን ልዩ ልዩ የአኗኗር ዘይቤዎች ለመጠበቅ አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላሉ” ብለዋል።

የአገሬው ተወላጆች ፣ በትውልድ መካከል ያለውን ውይይት፣ መግባባት እና ትብብርን በማዳበር በማህበረሰባቸው መካከል ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ” ሲሉም ሊቀ ጳጳሱ አክለዋል።

በተጨማሪም “የነባር ተወላጆች የማንነት ቁልፍ አካል የሆኑትን የአባቶቻቸውን ምድር፣ የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ጥበቃ ሥርዓት” በመደገፍ ወጣቶቹ ግንባር ቀደም ናቸውም ብለዋል።

የውይይት አስፈላጊነት

ሊቀ ጳጳሱ ከአገሬው ተወላጆች ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልግ በማበረታታት፥ ውይይት እና ማንነት “የጋራ እና የማይነጣጠሉ” እንደሆኑም አብራርተዋል። “ሙሉ በሙሉ የተዘጋ፣ ታሪካዊ፣ የማይለዋወጥ ከማንኛውም ዓይነት ውህደትን የማይቀበል ‘ተወላጅነትን’ ሳይሆን ከሌሎች ጋር “የመገናኘት ባህል” እንዲያራምዱም አሳስቧል።

የቫቲካንኑ ዲፕሎማት በመጨረሻም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ንግግርን በማስታወስ “የሰው ልጆች እና በምድር ላይ ያሉ ሁሉ ፈጣሪ እና አባት፣ እግዚአብሔር ዛሬ ጠርቶናል፥ ለዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ውይይት፣ በሰጥቶ መቀበል፣ በፍቅር እና ሰላም በሰብዓዊ ጥሪያችንን እንድንኖር እና እንድንመሰክር ይጠራናል” ካሉ በኋላ “እርስ በርስ ግጭትን፣ ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ መለያየትን፣ ሁከትንና ጦርነትን ከማቀጣጠል መቆጠብ አለብን” ብለዋል።
 

18 April 2024, 16:32