ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር በቪዬትናም ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር በቪዬትናም ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት  

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር በቪዬትናም ያሚደርጉትን ጉብኝት ፈጽመው ተመልሰዋል

ቫቲካን ከአገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያላትን ግንኙነት በበላይነት የሚከታተል የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በቪዬትናም ያደረጉትን ጉብኝት ፈጽመዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በደቡብ ምሥራቅ የእስያ አገር ቪዬትናም ጉብኝት ማድረግ የጀመሩት ሚያዝያ 1/2016 ዓ. ም. ነበር። ሊቀ ጳጳሱ በጉብኝታቸው ወቅት ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር ከተገናኙ በኋላ ሦስቱን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አውራጃዎች ጎብኝተዋል። ከቬትናም ብጹዓን ጳጳሳት ጋርም በአገሪቱ ስለሚሰየም ቋሚ ተወካይ ጳጳስ መተዳደሪያ ደንብ እና ስለ ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ተወያይተዋል።

ቅድስት መንበር ከቪዬትናም ጋር ያላትን ግንኙነት በተግባር ለመግለጽ በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር ቪዬትናም ያደረጉትን ጉብኝት ያገባደዱት እሑድ ሚያዝያ 6/2016 ዓ. ም. ነበር። የቅድስት መንበር የአገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በጉብኝታቸው ወቅት ከአካባቢው የፖለቲካ እና የቤተ ክህነት ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቪዬትናም ካቶሊክ ማኅበረሰብ ያላቸውን ቅርበት በፑ ካም ካቴድራል ውስጥ በገለጹበት መልዕክታቸው የአካባቢው ካቶሊክ ምዕመናን አደራን ለላ ቫንግ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰጥተዋል።

ከሲቪል ባለስልጣናት እና ከጳጳሳት ጋር ያደረጉት ግንኙነት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በአገሪቱ በነበራቸው ቆይታ ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ሦስቱን ማለትም የሀኖይ፣ ሁዌ እና ሆ ቺ ሚን ከተሞች የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አውራጃዎችን ጎብኝተዋል። በመቀጠልም በአገሪቱ ስለሚሰየም ቋሚ ተወካይ ጳጳስ መተዳደሪያ ደንብ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ 2023 ዓ. ም. በቪዬትናም እና በቅድስት መንበር መካከል ስለተፈረመው ታሪካዊ ስምምነት እና ከአገሪቱ ሕዝብ 27% ወይም 27 ሚሊዮን አማኞች መካከል በማደግ ላይ የሚገኝ ከ 7.2 ሚሊዮን በላይ ካቶሊክ ምዕመናን ሁኔታ ከብጹዓን ጳጳሳት ጋር ተወያይተዋል።

ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገ ውይይት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በቀደሙት ቀናት ውስጥ ከአንዳንድ የቪዬትናም መንግሥት ተወካዮችን ጋር በሃኖይ ከተማ ውስጥ ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡይ ታን ሣን እና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ፋም ታህ ትራ ይገኙበታል። በቪዬትናም እና በቅድስት መንበር መካከል አወንታዊ እና መልካም የሁለትዮ ሽግንኙነት መኖሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ተደጋግሞ የተገለጸ ሲሆን፥ ቀጣዩ የቪዬትናም እና የቅድስት መንበር የጋራ ቡድን አሥራ አንደኛው ስብሰባ በቅርቡ ሊካሄድ እንደሚችል እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በቪዬትናም ሐዋርያዊ ጉብኝት ሊያደርጉ እንደሚችሉም በውይይቶቹ መካከል ተጠቅሷል።

 

16 April 2024, 17:34