ፈልግ

የክህነት ምስጢር አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት የክህነት ምስጢር አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት  (ANSA)

ቫቲካን ክኅነታዊ አገልግሎትን የተመለከተ ዓለም አቀፍ ጉባኤን እንደምታስተናግድ ተገለጸ

ቫቲካን ካህናት ለወንጌል አገልግሎት የሚዘጋጁበትን መንገድ ለማጥናት ያለመ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለማስተናገድ መዘጋጀቷ ታውቋል። ክኅነታዊ አገልግሎትን አስመልክቶ የሚካሄደውን ይህን ጉባኤ ለመካፈል ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች በቫቲካን እንደሚሰበሰቡ ይጠበቃል። ከጥር 28 እስከ የካቲት 2/2016 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደው ጉባኤ መሪ ርዕሥ "በውስጣችሁ ያለውን የእግዚአብሔር ስጦታ አንቁ" የሚል ሲሆን፥ ዓላማውም ካኅናት ለወንጌል አገልግሎት የሚዘጋጁበትን መንገድ ለማጥናት ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብራዚል ወደዚህ ጉባኤ ብዛት ያላቸውን ተሳታፊዎች የምትልክ ሲሆን፥ ከብራዚል ቀጥሎ ሜክሲኮ፣ ጣሊያን፣ ፖላንድ እና ፊሊፒንስም በርካታ ተሳታፊዎችን እንደሚልኩ ታውቋል። በዓለም አቀፉ ጉባኤ ላይ ከአይስላንድ፣ ቡሩንዲ፣ ኤልሳልቫዶር፣ ቻይና፣ ጓቲማላ፣ ሞልዳቪያ፣ ሩሲያ፣ ዩክሬን እና ከ60 በላይ ሌሎች አገሮች ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምዕመናን እንደሚገኙ ይጠበቃል።

ጉባኤው እንዲዘጋጅ ድጋፍ ያደረጉት በቅድስት መንበር የቤተ ክኅነት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ናቸው።

በአገራት ከሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ጋር ያለው ትብብር

ዓለም አቀፍ ጉባኤው ትኩረት ያደረገው በሀገረ ስብከቶች፣ በክልላዊ እና ብሔራዊ የዘርዓ ክኅነት ማሰልጠኛዎች የሚገኙ አስተባባሪዎች ላይ እንዲሁም በዘርፉ ፍላጎት ያላቸውን አካላት ሲሆን፥ ዓላማው በዓለም ዙሪያ በየአገራቱ ከሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ጋር የትብብር ሂደት ለመፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።ጉባኤው በቅርቡ የዳሰሳ ጥናት ይሆነው ዘንድ ለሁሉም ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች የተላከውን ጽሑፍ እና ተሳታፊዎች ከጉባኤው በፊት እና በጉባኤው ወቅት ያበረከቱትን አስተዋጾ እንደ መነሻ የሚወስድ ሲሆን፥ ዋና መሠረት ያደረገው “Ratio Fundamentalis Institutionis Sacerdotalis” ወይም የክኅነት መሠረታዊ ተቋም በሚል ርዕሥ በታተመው ጽሑፍ እና “የክህነት ጥሪ ስጦታ” በሚል ርዕሥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2016 ዓ. ም. ጀምሮ ተግባር ላይ በዋለው ሠነድ ላይ እንደሆነ ታውቋል።

የሲኖዶሳዊነት ዘዴን የተከተለ

በጉባኤው ወቅት የሚካሄድ የእያንዳንዱ ውይይት ጭብጥ በሁለት ወይም በሦስት አጫጭር ገለጻዎች የሚቀርብ ሲሆን፥ በመቀጠልም በቋንቋዎቻች ከተመደቡ ትናንሽ ቡድኖች በሚቀርቡ ገንቢ ልምዶች ላይ ውይይት ይደረግባቸዋል። በዚህ አካሄድ ጉባኤው ከጊዜ ወደ ጊዜ በአሳታፊነት እና በሲኖዶሳዊ ዘይቤ እየተካሄደ ያለውን የክኅነት ምስረታ ምሳሌያዊ ተሞክሮ ለማቅረብ ተስፋ አድርጓል።

በቫቲካን ዜና አገልግሎት ዋና መሥሪያ ቤት ሥር ከሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ ከጥር 28 እስከ የካቲት 2/2016 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ለአምስት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።

 

01 February 2024, 16:19