ፈልግ

በቫቲካን ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙ የድምጽ መቅረጫ ክፍሎች አንዱ  በቫቲካን ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙ የድምጽ መቅረጫ ክፍሎች አንዱ  

የቫቲካን ሬዲዮ የምሥረታውን 93ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓሉን አከበረ

“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሬዲዮ” በመባል የሚታወቀው የቫቲካን ሬዲዮ የተመሠረተበትን 93ኛ ዓመት የካቲት 4/2016 ዓ. ም. አከበረ። የዓለም የሬዲዮ ቀንም የካቲት 5/2016 ዓ. ም. የተከበረ ሲሆን፥ ከመነሻው ጀምሮ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉ ሕዝቦችን የመድረስ ተልዕኮአቸውን ጠብቀው ቆይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሁለቱ የመታሰቢያ ቀናቱ እጅግ አስደናቂ የቴክኖሎጂ ለውጥ በታየበት የብዙኃን መገናኛ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ምዕራፎችን ለማየት ዕድል የሰጡ፣ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተለያዩ ዓመታት በካቲት ወር ውስጥ የሚከበሩ ሲሆን፥ በዓለም ዙሪያ እጅግ ተስፋፍቶ ከነበረው የመገናኛ ዘዴ ታሪክ ጋር የተቆራኘውን የቫቲካን ሬዲዮን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ የካቲት 5/1923 ዓ. ም. መርቀው ማስጀመራቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዕለቱ ባስተላለፉት የመጀመሪያቸው የሬዲዮ መልዕክት ፥ “ደሴቶች ሆይ ስሙ! እናንተ በምድር ዳርቻ የምትገኙ ሕዝቦች ሆይ ስሙ!” በማለት “Qui Arcano Dei” ወይም “የእግዚአብሔር ምስጢር” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መልዕክት አስተላልፈዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሬዲዮ

ታሪካዊውን ክስተት ይፋ ያደረገው የሬዲዮው ፈጣሪው ጣሊያናዊው ጉሊዬልሞ ማርኮኒ በወቅቱ ባደረገው ንግግር፡- “የሮማው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለሁለት ሺህ ዓመታት ያህል መለኮታዊ አስተምህሮአቸውን በዓለም ላይ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ነገር ግን ሕያው ድምጻቸው በጠቅላላው የምድር ዳርቻ በተመሳሳይ ጊዜ ሲሰማ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1931 ዓ. ም. የተመሠረተው የቫቲካን ሬዲዮ በመገናኛ ብዙኃን ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው እንደ ሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። የሚፈጥረው ተፅዕኖው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ድምጽ በማሰራጨት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ አውድ ውስጥም ተንጸባርቋል።

በዩኔስኮ የተቋቋመው የዓለም የሬዲዮ ቀን ከቫቲካን ሬዲዮ ዓመታዊ ክብረ በዓል ጋር በመተባበር የብዙሃን መገናኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ጠቀሜታ እና ተፅእኖ አጉልቶ ያሳያል።

ከሞገድ ወደ ድረገጽ

ሬዲዮ ከባህላዊው የሬዲዮ ሞገዶች ወደ ዲጂታል ዘመን እና ወደ ድረገጽ በመሸጋገር በተለያዩ የለውጥ ደረጃዎች ውስጥ አልፏል፤ ወደ ዌብ ሬዲዮ እና ፖድካስትነት ተቀይሯል።

በተለይም የሬዲዮ ዲሞክራሲያዊ ገጽታ እንደ መሠረታዊ እሴቶች አጽንኦት ተሰጥቶታል። ብዙውን ጊዜ በዋና ሚዲያዎች ችላ የተባሉትን እና የተረሱትን ጨምሮ በማኅበረሰቡ ውስጥ ላሉ ድምፆች በሙሉ ቦታን ይሰጣል። በተጨማሪም ሬዲዮ በድንገተኛ ጊዜ ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ መረጃ እና ድጋፍ በመስጠት በሕዝብ ደህንነት ውስጥ ወሳኝ ሚና መጫወቱን ቀጥሏል።

በማጠቃለያም፥ የቫቲካን ሬዲዮ ታሪክ እና የዓለም የሬዲዮ ቀን ኅብረተሰቡን በመቅረጽ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነትን በማመቻቸት ረገድ የሃይል እና የአግባብነት ማሳያ ሆኖ ያገለግላል።

 

15 February 2024, 17:13