ፈልግ

በፈረንሳይ ፅንስ የማቋረጥ መብትን በሕገ መንግሥቱ ለማካተት ውይይት እየተካሄደ ነው በፈረንሳይ ፅንስ የማቋረጥ መብትን በሕገ መንግሥቱ ለማካተት ውይይት እየተካሄደ ነው  (ANSA) ርዕሰ አንቀጽ

ፈረንሳይ ሕይወትን የሚጻረር ሕገ-መንግሥት ወደማርቀቅ እያመራች ነው

በፈረንሳይ ፅንስ የማቋረጥ መብትን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ለማካተት ውይይት እየተካሄደ ነው። የሕገ መንግሥት ማሻሻያው በ30 ተቃውሞ በ493 ድምፅ በብሔራዊ ምክር ቤት ፀድቆ በአሁኑ ወቅት በሴኔቱ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል።

የርዕሠ አንቀጽ ትርጉም፥ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"አዲስ የእምነት ተነሳሽነቶች፥ በጎ አድራጎት እና ተስፋ" የሚለውን መርህ በመከተል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአምስት ወራት በፊት በፈረንሳይ-ማርሴይ ቬሎድሮም ከተማ ባደረጉት 44ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ማጠናቀቂያ ከ50,000 ለሚበልጡ ምእመናን ባደረጉት ንግግር፥ ሕይወትን፣ በእንግድነት መቀበልን እና ወንድማማችነትን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች እንዲረቀቁ በፈረንሳይ እና በመላው አውሮፓ የምትገኘውን ቤተ ክርስቲያንን ተማጽነዋል።

ቅዱስነታቸው በወቅቱ ጥርጣሬ እና ስልጣንን መልቀቅ የሚሉ ሁለት ጠንከር ያሉ ቃላትን በመጠቀም፥ “ማኅበረሰባችንን ብዙ ጊዜ የሚያሰቃዩ ቁስሎች ዓይናችን ወደ ሰማይ እንድመልስ ያደረገን፣ በታሪክ መካከል ድንቅ ነገሮችን የሚሠራ እግዚአብሔር አምልካችን በዓለማዊነት እና በተወሰነ ደረጃ ሃይማኖታዊ ግዴለሽነት ባለው ማኅበረሰባችን ውስጥም እየሠራ ነው” ብለዋል።

ከስደተኞች እስከ ገና ያልተወለዱ ሕጻናት ወይም የተዘነጉ አዛውንቶች ድረስ በተለያየ መልኩ በሕይወት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመመልከት ችላ ሳንል፥ እርስ በርስ እንድንዋደድ፣ ሌላውን ሰው እንደ ራስ አድርገን መመልከት እንደሚገባ አሳስበው፥ በባሕር ላይ በሚገኝ ጀልባ ተሳፍረው ለአደጋ የተጋለጡ ስደተኞችን ወይም በእናት ማህፀን ውስጥ የሚገኝ ለውርጃ አደጋ የተጋለጠ ፅንስ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ አሰላስለዋል።

ይህ ቅዱስነታቸው ወደ ፈረንሳይ ያመጡት ጠንካራ የተስፋ፣ የብርሃን እና የቁርጠኝነት መልዕክት ቢሆንም ነገር ግን በያዝነው ጥር ወር መጨረሻ ላይ በፓሪስ የሚገኘው ብሔራዊ ምክር ቤት ፅንስን የማቋረጥ መብትን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት አፅድቋል።

በፈረንሳይ መንግሥት የቀረበው ማሻሻያ አሁን በሴኔት እየተመረመረ ሲሆን፥ በጦርነት የተመሰቃቀለች፣ ለሉዓላዊነት፣ ለሕዝባዊነት እና ለሸማችነት ዝንባሌ የተጋረጠች አውሮፓ ከመሥራቾቿ አባቶች፥ ከአልሲዴ ደ ጋስፒሪ፣ ከሮበርት ሹማን፣ ከኮንራድ አድናወር ራዕይ ራሳቸውን የሚያርቁ የኢኮኖሚ ስልቶችን የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለሰው ልጆች ግልጽ አድርገዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመስከረም 2021 ዓ. ም. በስሎቫኪያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ሲመለሱ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ “ፅንስ ማስወረድ ግድያ ነው” ሲሉ በግልፅ ተናግረዋል። እንግዲህ ሰውን ከአደጋ እንጠብቅ እየተባለ እንዴት ነው የአንድን ሰው ሞት በመሠረታዊ የመንግሥት ቻርተር ውስጥ እንዲካተት የሚፈቀደው?

የምንኖረው በቴክኖሎጂ የላቀ እና በዲጂታል የተገናኘ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ለብዙ አሥርተ ዓመታት የሰው ልጅ ዕድገት ምስጢር አይደለም። እንደ ቅድመ-ፅንስ፣ ፅንስ፣ አራስ፣ ልጅ፣ ጎረምሳ፣ ጎልማሳ፣ አዛውንት የመሳሰሉ ቃላትን እንጠቀማለን። የዕድገት ደረጃዎችን ለማመልከት የሴሎች ቁጥር ቢጨምርም፣ የእውቀት ገጽታ ቢቀየርም፣ የዕርዳታ ፍላጎት ቢለያይም ነገር ግን የሰው ልጅ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ነው።

"ችግርን ለመፍታት የሰውን ሕይወት መግደል ተገቢ ነው? የሰውን ሕይወት ለመግደል ገዳይ መቅጠር ተገቢ ነው?" በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከብራቲስላቫ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወደ ሮም ሲመለሱ ጋዜጠኞችን በድጋሚ ጠይቀዋል።

አንድ ማኅበረሰብ የሚለካው እንዳያደርግ በሚከለከው ሳይሆን በማፍቀር ችሎታው ነው። "ነጻነት በፍቅር ያድጋል" ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 20/2021 ዓ. ም. በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ዕለት ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ አስረድተው፥ “በኢየሱስ የምናየው የፍቅር ቸርነት እውነተኛ እና ነጻ የሚያወጣ ፍቅር ነው” ብለዋል።

የፈረንሳይ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በፓርላማው ሂደት መጀመሪያ ላይ ስለ ሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ያላቸውን ሥጋት ገልጸው፥ እያንዳንዱ ሕይወት ከመነሻው እስከ ተፈጥሯዊ ፍጻሜው ድረስ በምስጋና የሚቀበሉት እና የሚያገለግሉት አቅመ ደካማ እና ውድ ስጦታ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሰው ልጅ፥ ዳርዊን “ኢዩጀኒክ” ብሎ በሚጠራው “ፅንስ ቁስ እንጂ ሰው አይደለም” የሚለውን ንድፈ ሃሳብ ዘወትር በማውገዝ፥ በዚህ ዐውድ ውስጥ ፅንስ ማስወረድ ቅድመ ሁኔታ እና መዘዝ እንደሆነም ይገልጻል። የ “ኢዩጀኒክ” ንድፈ ሃሳብ በሚገርም መልኩም እኛ ሰዎች ማየት፣ ነፃ መሆን፣ ለሌላቸው መስጠት ወይም መርዳት እንደማንችል አድርጎ ያቀርባል።

ጥሩ የአቀባበል እና የድጋፍ ስትራቴጂ በመገንባት፥ አስቸጋሪ የሆነ እርግዝና ላጋጠማቸው ሴቶች እና በማህፀናቸው ለተሸከሙት ሕፃናት የድጋፍ ገንዘብ መመደብ፣ ትኩረት ማድረግ እና ፍቅርን መስጠት በብዙ ዓመጽ በቆሰለ ዓለማችን ውስጥ ከባድ ይመስላል።

ይሁን እንጂ ኑሮን የሚደግፉ ማዕከላት እንደሚያረጋግጡት፥ ፅንስ ማስወረድ ብቸኛው መፍትሔ በሚመስልበት ወቅት ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ሕጋዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ ድጋፍ ቢደረግላቸው የብዙዎች ሕይወት ከሞት ይተርፋል።

ብዙ ጊዜ ራሳችንን ውጤት በሌላቸው የፖለቲካ ወይም የርዕዮተ ዓለም ተቃዋሚዎች ተወጥረን እንገኛለን። ነገር ግን ተግዳሮቱ ሕጎችን ማውጣት እና ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሃሳቦችን ለሕይወት ሳይሆን ለሞት  ማቅረባችን ነው። ችግሩ ስቃይን፣ ፍርሃትን፣ ጽንፈኛ እና አስገራሚ ሁኔታዎችን መንከባከብ የሚችሉ መዋቅሮችን እና እውነታዎችን ለማጠናከር መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሳችን ነው።

ሰውን መርዳት ማፍቀርን ይገልጻል። ለመምረጥ ነፃ መሆንን ያመለክታል። ይህ ወንድማማችነት ሌላውን ሰው የመንከባከብ ሃላፊነት የሚወስድ፥ ራሳቸውን ሳያገልሉ ነገር ግን ወደ ትክክለኛው እርስ በርስ የመቀባበል፣ የመጋራት እና የሰላም ባሕልን የሚጓዙ ማኅበረሰቦችን ይገነባል።

 

08 February 2024, 12:35