ፈልግ

ካርዲናል ዩ ሄንግ-ሲክ በ2014 ዓ.ም. ካርዲናል ከመሆናቸው በፊት ካርዲናል ዩ ሄንግ-ሲክ በ2014 ዓ.ም. ካርዲናል ከመሆናቸው በፊት  (Vatican Media)

ብፁዕ ካርዲናል ዩ ሄንግ-ሲክ በየቀኑ ለካህናት ባልደረቦቼ እጸልያለሁ አሉ

ብፁዕ ካርዲናል አልዓዛር ዩ ሄንግ-ሲክ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በቅርቡ በሮም ስለሚካሄደው የካህናት ምሥረታ የጋራ ኮንፈረንስ ሃሳባቸውን ያካፈሉ ሲሆን፥ ካህናት በአገልግሎት ዘመናቸው ሁሉ ያለማቋረጥ አብረው መጓዝ መቻላቸው ወሳኝ ነገር ነው ብለዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“የተከበራችሁ ወንድሞቼ ካህናት፥ በየዕለቱ በጸሎቴ አስታውሳችኋለሁ” ብለው ነበር ብፁዕ ካርዲናል አልዓዛር ዩ ሄንግ-ሲክ በቅርቡ ከቫቲካን ዜና ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ የጀመሩት።

የኮሪያ ተወላጅ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ፥ ከጥር 28 እስከ የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በሚካሄደው እና በቫቲካን የካህናት ጽ/ቤት ከተዘጋጀው እና እርሳቸው በሚመሩት ትልቁ ጉባኤ ቀደም ብለው ነበር ይህን ቃለ ምልልስ ያደረጉት።

በዚህ ጉባኤ ከ60 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ወደ 1,000 የሚጠጉ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉም ካርዲናሉ ያስታወቁ ሲሆን፥ ስለጉባኤው አስፈላጊነት ላይም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ብጹእ ካርዲናሉ እንደተናገሩት ካህናቱ በአገልግሎታቸው ወቅት “ብቻቸውን” እንዳልሆኑ፥ ነገር ግን ብዙ ሰዎች በአቅራቢያቸው እንዳሉ ማወቅ መቻላቸው በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ዛሬ ላይ አብዛኛው ካህናት ብቸኝነት እና የመገለል ስሜት እንደሚሰማቸው ብፁዕ ካርዲናሉ ገልጸው፥ ኮንፈረንሱ “ስለ ሕይወታቸው ከሌሎች ጋር ለመካፈል” እና “በጋራ ወደፊት ለመራመድ” ዕድል እንደሚፈጥረላቸው ተናግረዋል።

የሰበካ ካህናት ዓለም አቀፍ ስብሰባ

ብፁዕ ካርዲናል ዩ ሄንግ-ሲክ ለመጪው ጉባኤ እየተዘጋጁ ባለበት ጎን ለጎን “የሰበካ ካህናት ለሲኖዶስ” በሚል ርዕስ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለማድረግ ሲሠሩ እንደቆዩም ተናግረዋል።

በካህናት ጽ/ቤት እና በሲኖዶስ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት በጋራ ስፖንሰር የተደረገው ዝግጅቱ፥ 300 የሚሆኑ ከተለያየ የዓለም ክፍል የተውጣጡ ካህናትን በሮም ለአምስት ቀናት ‘በማዳመጥ፣ በጸሎትና በማስተዋል’ መንፈስ ጉባኤውን ይታደማሉ ተብሏል።

ስብሰባው የሚካሄደው ከሚያዝያ 20 እስከ 24 2016 ዓ.ም. ሮም አቅራቢያ በሚገኘው ‘ፍራቴርና ዶሞስ ሳክሮፋኖ’ ውብ መንደር ውስጥ እንደሆነ እና በመዝጊያው ዕለትም ተሰብሳቢዎቹ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር እንደሚገናኙ ተገልጿል።

ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳመላከተው፥ ይህ ስብሰባ ባለፈው ዓመት ላይ በተካሄደው የጳጳሳት ሲኖዶስ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ፥ አንደኛው ምዕራፍ ላይ ተሳታፊዎች ላነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል። ይህም ‘በሚመጣው ዓመት በሚደረገው የሲኖዶስ ጉባኤ ዲያቆናት፣ ካህናት እና ጳጳሳት በሲኖዶሱ ሂደት ውስጥ የበለጠ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን መንገድ ለማዘጋጀት’ እንደሆነም ጠቁመዋል።

 የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች ያኔ “ሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን ያለ ካህናቱ ድምጽ፣ ልምድ እና ካላቸው አስተዋጽዖ ውጪ ምንም ማድረግ አትችልም” በማለት አቋማቸውን በጽሁፍ ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

ከስብሰባው የሚገኙት ውጤቶችም በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ለሚካሄደው የሲኖዶስ ሁለተኛው ምዕራፍ ጉባኤ የሥራ ሰነድ ሲዘጋጅ ግብዓት እንደሚሆንም ተገልጿል።
 

06 February 2024, 14:38