ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ሚካኤል ቸርኒ በደቡብ ሱዳን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ሚካኤል ቸርኒ በደቡብ ሱዳን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት   (© X - VaticanIHD)

ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ሚካኤል ቸርኒ ደቡብ ሱዳን ሁከትን እንድታስቀር ጥሪ አቀረቡ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ በደቡብ ሱዳን ያደረጉትን የአንድ ሳምንት ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ተመልሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ሚካኤል ቸርኒ በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ማጠቃለያ ላይ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ባልደረባ በሆነች በቅድስት ጆሴፊን ባኪታ የተሰየመችውን ጀልባንም መርቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕነታቸው በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ “ጀልባነቷ ብቻ ሳይሆን ጥላቻ፣ ግፍ እና በቀል ቀርቶ በሰላማዊ ውሃ ላይ የሚመሠረት የአዲስ ሕይወት ምልክት ናት” በማለት በደቡብ ሱዳን ባደረጉት የአንድ ሳምንት ሐዋርያዊ ጉብኝት ፍጻሜ ላይ ተናግረዋል። ጀልባዋ ከዚህ በፊት የአባይን ወንዝ ለመሻገር የተገደዱ ስደተኞችን ስታጓጉዝ የቆየች እንደ ነበር ተነግሯል።

ጀልባዋ ስሙን ያገኘችው በአንድ ወቅት በደቡብ ሱዳን ዳርፉር ግዛት በባርነት ሕይወት የኖረች እና በኋላም ቅድስናዋ የታወጀላትን፣ ያለፈው እና የአዲሱ ባርነት ሰለባዎች ሁሉ ጠባቂ በመባል የምትታወቅ ቅድስት ጆሴፊን ባኪታን ለማስታወስ ሲሆን፥ የቅድስት ጆሰፊን ባኪታ ዓመታዊ በዓል በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በብዙ በሚቆጠሩ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች እና መንፈሳዊ ማኅበራት ዘንድ በየዓመቱ ጥር 30 እንደሚከበር ይታወቃል።

በአካባቢው የሚገኝ “ካሪታስ” የተሰኘ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጊ ድርጅት ከእንጨት እና ከብረት የተሠራችውን ይህች ጀልባ ከጎረቤት አገር ሱዳን የሚመጡ ስደተኞችን ለማጓጓዝ እንደሚጠቀማት ተገልጿል። የተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት፥ ለአስሥር ወራት በዘለቀው የእርስ በርስ ግጭት በወደመች ሱዳን 25 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እና ጥበቃ እንደሚያስፈቸዋል አስታውቋል።

ሰላም የሰፈነበት ውሃ

ጀልባው ከሱዳን የሚሰደዱ ሰዎች አደጋ እና መሰናክል የበዛበትን ሰፊውን የናይል ወንዝ ለማቋረጥ እንደሚረዳ ታውቋል። ከሱዳን የሚፈናቀሉ ሰዎች ጉዞ ከሬንክ ድንበር ጀምሮ እስከ ማላካል ሀገረ ስብከት የሚደርስ መሆኑ ተገልጿል። በጁባ ወደብ ላይ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ባሰሙት ንግግር፥ ጀልባው የግጭት ፣ የአመጽ ፣ የጥላቻ እና የበቀል ማዕበል ወደ ኋላ በመተው የበለጠ ሰላማዊ በሆነ ውሃ ላይ ሰዎች እንደ ወንድም እና እህት ወደሚኖሩበት አካባቢ የሚያደርስ ጀልባ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአንድ ዓመት በፊት በእንግሊዝ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጀስቲን ዌልቢ እና የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጉባኤ መሪ አባ ግሪንሺልድስ ጋር በመሆን በደቡብ ሱዳን ባካሄዱት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ሚካኤል ቸርኒ ደግመዋል።

በሬንክ እና ማላካል ሀገረ ስብከቶች ያደረጓቸው ጉብኝቶች

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ በደቡብ ሱዳን የተለያዩ አካባቢዎችን የጎበኟቸው ሲሆን፥ በማላካል ባካሄዱት የመጨረሻ ጉብኝታቸው ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ. ም. ለአሥረኛ ጊዜ በተከበረው ዓለም አቀፍ የጸሎት እና የጸረ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን በማስመልከት የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መርተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ሚካኤል ቸርኒ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ሐሰተኛ አማልክትን ወይም ጣዖታትን አውግዘው፥ “የገንዘብ እና የሥልጣን ጥማት፥ ሁሉን በቁጥጥር ሥር የማድረግ እና የበላይነት ረሃብ፣ ከብሔርተኘት ስሜት የሚመነጭ አግላይነት እና ጎሰኝነት፥ እነዚህ በሙሉ እስካሁን የሰዎችን ሕይወት የሚያጠፉ እና ደቡብ ሱዳንን እራሷን እያወደሙ የሚገኙ ክፋቶች ናቸው” ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ሚካኤል ቸርኒ በማላካል ሀገረ ስብከት ባደረጉት ጉብኝት የሀገረ ስብከቱ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ባላቸው ውስን አቅም ያደረጉላቸውን የክብር አቀባበል አድንቀው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። እንደዚሁም በሬንክ ሀገረ ስብከት ከስደት ለሚመለሱት ለደቡብ ሱዳን ሕዝቦች እና ለሱዳን ስደተኞች የተሠራውን የእንግዳ መቀበያ ማዕከልን ጎብኝተዋል። በዋና ከተማዋ ጁባ እሁድ ጥር 26/2016 ዓ. ም. በቅድስት ቴሬሳ ካቴድራል በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ በደቡብ ሱዳን ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ፈለግ የተከተለ እንዲሆን ለማድረግ የፈለጉት እንደ ሆነ ገልጸው፥ ቤተ ክርስቲያን ስደት የሚያስከትለውን ድንገተኛ አደጋ እና አሳዛኝ ሁኔታን በታላቅ ትኩረት እንደምትከታተለው የሚያሳይ ምልክት ነው ብለዋል።

ተልዕኮውን ማስቀጥል

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ሚካኤል ቸርኒ ከሉቃ. 8:22-25 ተወስዶ በተነበበው እና ኢየሱስ ሐይቁን በጀልባ ሲያቋርጥ አውሎ ነፋሱ ያስከተለውን ማዕበል በሚያስታውስ የዕለቱ ምንባብ ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ “ምንባቡ የጀልባውን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ የሚረዳን እና በባሕር ላይ ሊነሳ የሚችለውን ማዕበል ልናስብ የሚያስችለን እንዲሁም ደቡብ ሱዳን የደረሰባትን አስከፊ ግጭቶችና መከራዎች የሚወክል ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በጀልባው ላይ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ዳርቻ እንዲደርሱ ማዕበሉን እንዳረጋጋው ተናግረው፥ ይህም በተልዕኳችን፣ በጉዟችን እና በተግባራችን መካከል ማድረግ የምንችለው እና የሚገባን መልዕክት ነው” ብለዋል።

የእግዚአብሔር የፈዋሽነት ምልክት

“በጆሴፊን ባሂታ የተሰየመው ጀልባ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ያበረክታል” ሲሉ ያከሉት ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ሚካኤል ቸርኒ፥ ለሚያበረክተው መልካም ነገሮች ሁሉ አመስጋኞች እንደሆኑ እና እግዚአብሔርን ለበረከቱ አመስግነው፥ ጀልባው ለተሠራለት ዓላማ በመዋል በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር የሚገለጥበት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛም መካከል እና በሁሉም ሥፍራ የፈውስ ለሚረብሹን የችግር ማዕበሎችን የማረጋጋት ምልክት ይሁን” በማለት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ በደቡብ ሱዳን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ማጠቃለያ ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ተናግረዋል። 

 

10 February 2024, 16:36