ፈልግ

2019.07.13 Papa Emerito Benedetto XVI

የቀድሞው ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ የእምነት መምህር እና ምስክር እንደ ነበሩ ተነገረ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ያረፉበትን አንደኛ ዓመት በማስታወስ፥ ቃል አቀባያቸው የነበሩት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ፥ አበርክተው ያለፏቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎቶች በማስታወስ፥ “የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ‘የእምነት መምህር እና ምስክር’ ነበሩ” በማለት ተናገረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ካረፉ ከአንድ ዓመት በኋላ ትሩፋታቸውን ማጤን ተገቢ ነው ያሉት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ያለፈውን ጊዜ በሐዋርያነት የመሩን አባት ብቻ ወይስ አሁን የምንገኝበት የአሳዛኝ ወቅት ፈተናንም የሚፈቱ አባት ናቸው?” በማለት ጠይቀዋል።

“የእምነት ሊቅ እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም ያሉት” አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ፥ “የክርስትና እምነት መግቢያ” እና “የናዝሬቱ ኢየሱስ” በሚሉት ርዕሦች የጻፏቸውን መጽሐፍት ደግመን ማንበብ አይታክተንም ብለዋል። የነገረ መለኮት ሊቃውንትም ለረጅም ዓመታት ወደ ቅዱስነታቸው የጽሑፍ ሥራዎች ዘልቀው መግባት እንደሚችሉ እና ለአስተያየታቸውም ሆነ ለምርምር ሥራዎቻቸው ጥቆማዎችን እና መመሪያዎችን ሊያገኙ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በዘላለም ሕይወት ውስጥ ለሚገኝ የክርስቲያን እምነት ታላቅ ምስክር እንደነበሩ፥ ቃለ ምዕዳናቸውን እና ሐዋርያዊ አስተምህሮአቸወን ተከታትለው መረዳት ለቻሉት እና በቅርብ ለሚያውቋቸው፣ ጥልቅ የሆነውን መንፈሳዊ ጉዟቸውን በመከታተል ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ለበቁት ሰዎች በሙሉ የእምነት ሕይወት ምስክር እንደነበሩ አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ ተናግረዋል።

“አሁንም መመልከት የምፈልገው ነገር አለ” ያሉት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በምድራችን ውስጥ በሕይወት እና በሰው ልጅ ታሪክ ላይ በመሳተፍ ዛሬም አስደናቂ ጥያቄዎቻቸውን ለሚያቀርቡት ሰዎች በሙሉ ወዳጃቸው ሆነው መቀጠላቸውን አስረድተዋል።

“የዓለማችን መንገድ ብዙ ገፅታዎች እንዳሉት እና ከቁጥጥር ውጪ መሆኑን መደበቅ አንችልም” ያሉት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ፥ ሥነ-ምህዳራዊ ቀውስ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በማኅበራዊ ግንኙነት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት በኩል ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎች፣ በመጨረሻም እርስ በራሱ የሚቃረኑ የመብት ጥያቄዎች፣ ብጥብጥ እና ረብሻ የሚታይበት ዓለም አቀፋዊነት እና በቀጣይነት በማደግ ላይ የሚገኘው የጦርነቶች መስፋፋት ስጋት መኖሩን አስረድተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳዊው በኅዳር 30/2023 ዓ. ም. የራትዚንገር ሽልማትን ሲቀበሉ ፕሮፌሰር ፍራንችስኮ ቶራልባ እንዳብራሩት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ የዘመናችን ቀውሶች መንስኤን በጥልቀት በመመልከት፥ የዘመናችን ባሕል አድማሱን በማስፋት ለሥነ ምግባር እና ለእምነት ምክንያታዊነት ሰፊ ቦታን መስጠት እንደሚገባ ሃሳብ አቅርበዋል።

በዚህም የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፥ የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ውድቀቶችን መካድ ወይም መገደብ ሳይሆን፣ ዓለም እንዴት እንደሚጓዝ ማወቅ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ በሥነ ፍጥረት ውስጥ ያለውን ቦታ እና ጀብድ ትርጉም ለመረዳት በስፋት እንዲሠራ መጋበዛቸው እንደ ነበር፥ ፕሮፌሰር ፍራንችስኮ ቶራልባ ገልጸዋል። “ይህ በተወሰነ መልኩ ከወቅታዊ ባሕል ጋር ለመወያየት የቀረበው ሃሳብ ብዙውን ጊዜ በግዴለሽነት ውድቅ የተደረገ መሆኑን መካድ አይቻልም” በማለት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ ተናግረዋል።

“ስለ እግዚአብሔር ግድ የለኝም” የሚለው፥ ነገር ግን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ጋር ለመነጋገር የሞከረው የሒሳብ ትምህርት ሊቅ ኦዲፍሬዲ፥ ከክህደቱ በኋላ በነበሩት ዓመታት ውስጥ ያልተለመደ እና አክብሮት የተሞላበት ትኩረት በመስጠት ባደረገው ውይይቱ፥ ቅዱስነታቸው ለባሕል ያላቸው አስተያየት እና ግልጽነት አሳዛኝ እንደ ነበር፥ በሌላ በኩልም ከባሕል ሰዎች በኩል ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግሯል።

“የሒሳብ ሊቃውንቱን የኦዲፍሬዲ አስተያየት አልቀበልም” ያሉት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ፈጣን ምላሽ የማይሰጡ፥ ነገር ግን በአርቆ አሳቢነታቸው ትክክለኛነታቸውን ጠብቀው በማቆየት በሳይንስ እና በእምነት መካከል፥ በአጠቃላይ በዘመናዊ ባህል እና በእምነት መካከል ለሚደረጉ ውይይቶች ምቹ መንገዶችን ይፈልጉ እንደ ነበር፥ በችግሮቹ መንስኤዎች ላይ ከማሰላሰል እና በእውነት ላይ የተመሠረተ ስምምነትን ከመፈለግ ወደ ኋላ ያሉ አልነበሩም በማለት አስረድተዋል።

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ክርስቲያናዊ ራዕይ ውስጥ፥ የምክንያት መስፋፋት በፍቅር አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ውስጥ የሚገለጽ እና ወደ ወንድማማችነት፣ ወደ አብሮነት እና ወደ እርቅ የሚተረጎመውን የፍቅር አመክንዮ እንደሚያካትት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ ገልጸው፥ እውነት እና ፍቅር በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በሙላት ይገለጣሉ ብለዋል።

“እግዚአብሔር ፍቅር ነው”፣ “ፍቅር በእውነት”፣ “ውዳሴ ለእግዚአብሔር ይሁን” እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖች የመጨረሻዎቹ ሁለት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት በተከታታይ እና በቀጣይነት የሚከተሏቸው ዋና ዋና ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናት እንደሆኑ አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ አብራርተዋል። የቤተ ክርስቲያን እና የክርስቲያኖች ቁርጠኝነት፥ የሰው ልጆች በአንድነት ወደ እምነት ብርሃን በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ባላቸው ሃላፊነት፥ ምክንያትን እና ፍቅርን እንዲያውቁ ዓለም የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለማቋረጥ ዘወትር የሚናገሩት የበጎነት ተግባር እንቅስቃሴዎች በጊዜአችን ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት የሚያስችል ብሩህ ራዕይ እና ወጥነት ያለው ማዕቀፍ እንዲኖረን መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ከማረፋቸው ከሦስት ወራት በፊት የስቴውበንቪል ፍራንችስካዊ ዩኒቨርሲቲ ላዘጋጀው የራትዚንገር ፋውንዴሽን ሲምፖዚየም በጻፉት ጠቃሚ እና አስገራሚ መልዕክታቸው፥ ስለ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሲናገሩ፥ ጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ የሃይማኖቶች ሥነ-መለኮት ጥያቄን በአክራሪነት ማቅረቡን፥ በእምነት እና በምክንያት መካከል ስላለው ግንኙነት እና ሁለቱም ርዕሠ ጉዳዮች ከዚህ በፊት ባልተነገሩ መንገዶች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

ጉባኤው መጀመሪያ ላይ ቤተ ክርስቲያንን ብቻ የተመለከተ ቢመስልም፥ የቤተ ክርስቲያን አመሠራረት እና ተልዕኮ የመገንባት አስፈላጊነት ቀስ በቀስ እየታየ መምጣቱ እና ቤተ ክርስቲያን በዓለም ውስጥ የሚለው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሊመልስ የሞከረው እውነተኛ እና ማዕከላዊ ጥያቄ እንደ ነበር አስረድተዋል።

ጠቅላላውን ጉባኤ የተሳተፉት እና ከውስጥ ሆነው በተግባር የኖሩት የመጨረሻው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፥ ለዘለቄታው ትተውልን በሄዱት ጠቃሚ ምስክርነት፥ መዘዙን ሳንፈራ ፍሬውን ማሳደግ እንደሚገባ፥ በዓለም ላይ ያለችውን የቤተ ክርስትያን ተልዕኮ በማስተካከል፣ ምክንያት እና እምነት ለሰው ልጅ እና ለዓለም ድነት መመተባበር እንደሚገባ ያበረታቱናል” በማለት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ ተናግረዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክት 16ኛ አገልግሎት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እና በተተኪዎቹ መሪነት፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጥልቅ እንቅስቃሴ እና ዕይታቸውም በተስፋ ወደ ወደፊቱ እንደሚጓዝ አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ ተናግረዋል።

 

02 January 2024, 16:10