ፈልግ

ከአባ ኢብራሂም ጋር ወደ ጣሊያን መጥተው "ባምቢኖ ጄሱ" ሆስፒታል ከገቡት ሕጻናት መካከል ከአባ ኢብራሂም ጋር ወደ ጣሊያን መጥተው "ባምቢኖ ጄሱ" ሆስፒታል ከገቡት ሕጻናት መካከል  

ከስቃይ ውስጥ የወጡ የጋዛ ሕጻናት ወደ ሮም መድረሳቸው ተገለጸ

በእስራኤል እና በሐማስ ታጣቂዎች በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ከሚገኙ ሕጻናት መካከል የተወሰኑት ወደ ሮም መድረሳቸው ታውቋል። ከእነዚህ መካከል አራቱ ሕጻናት አሁን ሮም ውስጥ በሚገኝ “ባምቢኖ ጄሱ” ካቶሊካዊ የሕጻናት ሆስፒታል ገብተው አስፈላጊው የሕክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ታውቋል። “በሕጻናት ፊት አሁን ገና የደስታ ስሜት ይታይባቸዋል” በማለት የቅድስት አገር መጋቢ አባ ኢብራሂም ፋልታስ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሕጻናቱ ጋዛ ውስጥ ከነበሩበት ስቃይ በመውጣታቸው የደስታ ስሜት እንደሚታይባቸው አባ ኢብራሂም ፋልታስ ተናግረው፥ ወደ ጣሊያን መምጣት ህልማቸው እንደ ነበር፥ የቅድስት አገር መጋቢ አባ ኢብራሂም ፋልታስ ማክሰኞ ጥር 21/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል። ከጋዛ የመጡ እነዚህን ሕጻናት በቅድስት መንበር የፍልስጤም አምባሳደር አቶ ኢሳ ካሲሲዬ ጎብኝተዋቸዋል። 

በመከራ ባሕር ውስጥ ያለ ተስፋ

“ለሕጻናቱ የተደረገላቸው አቀባበል መልካም ነበር” ያሉት አባ ፋልታስ አክለው፥ ሆስፒታሉ ያለ ምንም ልዩነት ሁሉን ሰው እንደሚቀበል ገልጸው፥ ከጋዛ ሰርጥ የመጡ ሕጻናት ሁሉም ሙስሊሞች እንደሆኑ እና እያንዳንዳቸው ከኋላቸው የተለየ ታሪክ ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

“ባምቢኖ ጄሱ” የሕጻናት ሆስፒታል ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ ቲሲያኖ ኦኔስቲ፥ “ሕጻናቱ ከዚህ ቀደም በበሽታ አምጪ ተህዋስያን የተጠቁ በመሆናቸው እና ጋዛ ውስጥ መታከም የማይቻል በመሆናቸው ወደ ሮም ልናመጣቸው ወስነናል” ብለዋል። አለመታደል ሆኖ በሆስፒታላቸው የሕክምና ዕርዳታን ማግኘት የቻሉት በአሁኑ ጊዜ ጥቂት እንደሆኑ፥ ነገር ግን ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሌሎች ብዙ እንዳሉ ተናግረዋል። አቶ ቲሲያኖ ኦኔስቲ በማከልም፥ ሌሎችን ሕጻናትን ከጋዛ ለማምጣት ተስፋ እንዳለ ገጸው፥ ሆስፒታላቸው የሚያደርገው ዕርዳታ “በእርግጥ ጋዛ ውስጥ ካለው ከፍተኛ ችግር ጋር ሲወዳደር ጠብታ ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የእንግዳ መቀበያ ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሉቺያ ቼሌስቲ፥ በሆስፒታላቸው የሕክምና ዕርዳታ ከሚደረግላቸው ሕጻናት መካከል ሁለቱ የነርቭ ሕመምን በሚያስከትሉ ተህዋስያን የተጠቁ መሆናቸው፣ አንዷ ሕጻን የደም ሕክምና የሚያስፈልጋት በመሆኑ እስክታገግም ድረስ እንክብካቤ እየተደረገላት እንደምትቆይ አስረድተዋል።

በጋዛ የሚደርስ የሞት አደጋ ሊቆም ይገባል!

ሕጻናቱን ከጋዛ ማውጣት ቀላል አልነበረም ያሉት የቅድስት አገር መጋቢ አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ ጉዳዩን ለማሳካት ከፍልስጤም፣ ከግብፃውያን እና ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር መነጋገር እንደነበረባቸው አስረድተዋል። ወደ ሮም ለማምጣት የተመዘገቡት ሕጻናት ቁጥር 100 ቢሆንም ነገር ግን ከ13 ረዳቶቻቸው ጋር ወደ ሮም የደረሱት 11 ሕጻናት ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አባ ኢብራሂም ፋልታስ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባቀረቡት አዲስ ጥሪ፥ “በንጹሃን ሰዎች ላይ የሚደርስ ሞት ይብቃ! ለማለት ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል። በጋዛ ውስጥ ሕይወታቸውን ያጡ ከ26,000 በላይ ሰዎች እንደሆኑ እና ሌሎች 65,000 የቆሰሉ ወይም የተጎዱ ሰዎች ሆስፒታሎች በመውደማቸው ምክንያት የሕክምና ዕርዳታን ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸው፥  ይህን ጦርነት ለማስቆም የዓለም ማኅበረሰብ ጣልቃ መግባት እንዳለበት አሳስበዋል።

አባ ኢብራሂም ፋልታስ በማከልም፥ “ከነዚህ ሁሉ ጉዳት በኋላ ተስፋቸው የችግሩ መፍትሄ ይገኛል፥ ሰላምም ይሰፍናል የሚል ነው” ብለዋል። መፍትሄው አሁን ካልተገኘ መቼ ነው? ብለው፥ ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን በሰላም እንዲኖሩ ዋስትናን ሊሰጥ የሚችለው፥ የሁለት መንግሥታት የሚለው ሃሳብ ተግባራዊ ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል። “እውነታው በአሁኑ ጊዜ ለአይሁዶችም፣ ለክርስቲያኖችም፣ ለእስላሞችም፣ ለፍልስጤማውያን እና ለእስራኤላውያንም ሰላም የለም” ሲሉ አባ ኢብራሂም ፋልታስ ተናግረዋል።

በቅድስት መንበር የፍልስጤም አምባሳደር አቶ ኢሳ ካሲሲዬ፥ በፍልስጤም አመራር እና በፍልስጤም ሕዝብ ስም፥ እንዲሁም ልጆቻችንን ከስቃይ ለማውጣት ድጋፍ ላደረጉት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ የእነርሱን እና የቤተሰቦቻቸውን ታሪክ መስማት በጣም ያሳምማል።" ብለዋል።

አምባሳደር ኢሳ ካሲሲዬ በመጨረሻም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለፍልስጤም ሕዝብ እና ለቅድስት አገር ሰላም ብዙ እንደሚጸልዩ፥ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ድንበር እንዲከፈት እና “ሁለት መንግሥታት” የሚል የመፍትሄ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆን መማጸናቸውን አስታውሰው፥ “ከዚህ አስከፊ ጦርነት በመውጣት ወደ ነፃነት እንደምንሻገር ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

31 January 2024, 17:13