ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ችዘርኒ - የፋይል ፎቶ ብጹዕ ካርዲናል ችዘርኒ - የፋይል ፎቶ  

ብፁዕ ካርዲናል ችዘርኒ በቤኒን ሃዋሪያዊ ጉብኝት እያደረጉ እንደሆነ ተገለጸ

ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ችዘርኒ ከጥር 8 እስከ 11/ 2016 ዓ.ም. ለሃዋሪያዊ ጉብኝት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቤኒን ይገኛሉ። ጉብኝቱ ለድሆች እና በገጠራማ የሃገሪቱ መንደሮች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን በኮቶኑ ከተማ የሚገኘውን የቅዱስ ዣን ዲ ዲዩ ሆስፒታልን መጎብኘት እንደሚያካትት ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ችዘርኒ ከጥር 8 እስከ 11 ድረስ ቤኒንን እየጎበኙ እንደሆነ ተነግሯል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የኮንጎን 140ኛ ዓመት የወንጌል ስርጭት ምክንያት በማድረግ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ተወካይ በመሆን ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፥ ብራዛቪል ተጉዘው እንደ ነበር ይታወሳል።

ቅዱስ ዣን ሆስፒታል፡- ጥራት ያለው እንክብካቤ በተመጣጣኝ ዋጋ

አፍሪካ የብፁዕ ካርዲናሉ የመጪው ጊዜ የትኩረታቸው ማዕከል እንደምትሆን የተገለጸ ሲሆን፥ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በኮቶኑ ከተማ ለትርፍ ያልተቋቋመውን ሴንት ዣን ዲ ዲዩ ሆስፒታል በመገኘት ህዝቡን በተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች የሚረዳውን የጤና እንክብካቤ ተቋም ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሆስፒታሉ እ.አ.አ. በ1963 በሊዮን የቅዱስ ዮሴፍ ገዳማዊያት እህቶች የተመሰረተ ሲሆን፥ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1986 ገዳማዊያቱ ሃገሩን ለቀው ሲወጡ ከምዕመናን ለተውጣጡ አስተዳዳሪዎች እንደተሰጠ ተጠቁሟል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ተቋሙ የሚተዳደረው በኮቶኑ ሊቀ ጳጳስ በተሾሙ ካህናት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ ተቋም ዛሬ ላይ በአከባቢው ከፍተኛ እውቅና ያለው ሆስፒታል ሲሆን፥ በሴሆ ከተማ ውስጥ 43 ሄክታር መሬት ለመግዛትም እንደቻለ ተገልጿል።

ተቋሙ ለድሃው ማህበረሰብ እና ከከተማው ርቀው ለሚኖሩ ሰዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያመቻች ሲሆን፥ አዲስ የተገነባውን የእናቶች ማዋለጃ ብሎክን ጨምሮ ሆስፒታሉ ሁለት የቀዶ ጥገና ማድረጊያ ክፍሎች፣ ሁለት የማቆያ ክፍሎችን እና በርካታ ዎርዶች እንዳሉት ተብራርቷል።

ከጳጳሳት እና ከምዕመናን ጋር በመገናኘት በሥነ-ምህዳር ዙሪያ በክብ ጠረጴዛ መወያየት

የብፁዕ ካርዲናሉ ሃዋሪያዊ ጉብኝት የቶጎ ጳጳሳት ጉባኤ እና የቤኒን ጳጳሳት እያጋጠሟቸው ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ሁለት የስራ ስብሰባዎች ማድረግን እንደሚያካትት ተነግሯል።

በተጨማሪም ካርዲናሉ ከጳጳሳዊ ማሕበራዊ ኮሚሽኖች እና በማህበራዊ መስክ ውስጥ በአካባቢው የሚሰሩ የሃይማኖት ጉባኤዎች ጋር በሚደረግ ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።

ብፁዕ ካርዲናል ችዘርኒ ጥር 10 በኮቶኑ በሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በመገኘት ከ5,000 በላይ ምእመናን ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀውን ሥርዓተ ቅዳሴን እንደሚመሩ ተገልጿል።

ቤኒን ለደን መጨፍጨፍ እና ለድርቅ በጣም ከተጋለጡ አገሮች መካከል ቀዳሚ መሆኗን፥ በዚህም ሰበብ በእረኞች እና በአርሶአደሮች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በሥነ-ምህዳር ዙሪያ በሚደረገው ውይይት ላይ በመሳተፍ ካርዲናሉ በሀገሪቱ የሚያደርጉት ጉብኝት ማጠቃለያ እንደሚሆን ተገልጿል።

የአውሮፓ ዕርዳታ ለሰብአዊ ልማት እና ደህንነት

ከውስጥ ደህንነት አንፃር ቤኒን በምዕራብ አፍሪካ የሚንቀሳቀሱትን የጂሃዲስት ሚሊሻዎችን እንቅቃሴ ለማቆም እየሞከረች እንደሆነ ተነግሯል።

አፍሪካ ኤክስፕረስ የተባለው የሚዲያ ተቋም እንደዘገበው በአውሮጳ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር መሐንዲሶች አክራሪ ጽንፈኛ ድርጅቶች በሚንቀሳቀሱበት እና በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ገጠራማ አከባቢዎች የተጠናከረ የጀልባ ማምረቻ ጣቢያ እና አንዳንድ የሰብአዊ እርዳታ ፕሮጀክቶችን በተለይም ትምህርት ቤቶችን እና የጤና ጣቢያዎችን እድሳት የማድረግ ኃላፊነቱን ወስዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ የአውሮፓ ህብረት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ለኮቶኑ ከተማ 255 ሚሊዮን ዩሮ ለ“ማክሮ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት” የኢኮኖሚ ዕርዳታ በመመደብ፥ በተለይም በሶስት ስትራቴጂካዊ ዘንጎች ማለትም የሰው ልጅ ልማት፣ የአረንጓዴ ዲጂታል እድገት እንዲሁም የበለጸገ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመገናባት አልሞ እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል።
 

18 January 2024, 13:37