ፈልግ

የአባ ክሪስቶፍ ዛክያ ኤል-ካሲስ ስመተ ጵጵስና፥ የአባ ክሪስቶፍ ዛክያ ኤል-ካሲስ ስመተ ጵጵስና፥   (� Vatican Media)

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ ሃይማኖት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችል ተገለጸ

በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዱባይ ከተማ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) እየተካሄደ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፥ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክሪስቶፍ ዛክያ ኤል-ካሲስ፥ የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቅረፍ ሃይማኖት እና የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይቶች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክሪስቶፍ በዱባይ ከተማ በመካሄድ ላይ ከሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ጎን ለጎን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሃይማኖት ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችል ገልጸው፥ “ሃይማኖት ሰዎችን በመምራት እና አስተሳሰባቸውን እንዲለውጡ በማገዝ ትልቅ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት የጉባኤው አዘጋጆች የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት መሪዎችን ለማሳተፍ ጥረት አድርገዋል ብለው፥ የሃይማኖት መሪዎች ምዕመናኖቻቸውን ስለ ሰው ልጅ፣ እንዲሁም ሕይወት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን እንዲያስቡ መርዳት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

“ፍጥረት የእግዚአብሔር ስጦታ ስለሆነ መንከባከብ አለብን" ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክሪስቶፍ፥ “እኛም የተፈጠርነው በእግዚአብሔር ስለሆነ የእርሱ ስጦታዎች በመሆናችን ስለ ስጦታው እግዚአብሔርን በማመስገን የእርሱ ስጦታ የሆነውን የጋራ መኖሪያ ምድራችንን መንከባከብ አለብን” ብለዋል።

የአየር ንብረትን ለመከላከል የሚደረግ ቁርጠኝነት

“እንደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ላለች አገር የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP28) ማስተናገድ ለምን አስፈላጊ?” ተብለው የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክርስቶፍ፥ አገሪቱ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፥ በዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሷንም ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከፍተኛ መጠን ያለውን የነዳጅ ዘይት ብታመርትም፥ ከቅሪተ አካል ነዳጅ ወደ ንፁህ የኃይል ፍጆታ ለማሸጋገር ቃል መግባቷን ጠቁመው፥ ያሳየችው አስደናቂ ቁርጠኝነት ለሌሎች አገራት ምሳሌ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለጉባኤው የላኩት መልዕክት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክርስቶፍ በመጨረሻም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጉባኤው ላይ ባለመገኘታቸው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፣ ቅዱስነታቸው በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ለመገኘት የነበራቸው ዕቅድ በጤና ምክንያት መሠረዙን ተናግረዋል።

“ቅዱስነታቸው በጉባኤው ላይ እንደማይገኙ ባወቅን ጊዜ አዝነን ነበር” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክርስቶፍ፥ ሁሉም ሰው ቅዱስነታቸውን ለማግኘት ደስተኛ እንደ ነበር ተናግረው፥ “ቅዱስነታቸው በመንፈስ ከእኛ ጋር ነበሩ” ብለው፥ እርሳቸውን በመወከል መልዕክታቸውን ለጉባኤው በንባብ ያቀረቡት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን እንደነበሩ አስታውሰው፥ “በቅዱስነታቸው መልዕክት ጉባኤው በእውነት መነካቱን አስተውያለሁ” ብለዋል።

 

07 December 2023, 16:44