ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ እና እህት አሌሳንድራ ሰሜሪሊ ለጉባኤው ንግግር ሲያደርግሁ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ እና እህት አሌሳንድራ ሰሜሪሊ ለጉባኤው ንግግር ሲያደርግሁ  

ለሰብዓዊ መብቶች፣ ለሰው ልጆች እና ለፍጥረት የሚደረጉ እንክብካቤዎች የተገናኙ መሆናቸው ተገለጸ

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የተደነገገበት 75ኛ ዓመት መታሰቢያ እና “ውዳሴ ለእግዚአብሔር” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አስመልክቶ በጄኔቭ በቀረበው ከፍተኛ ዝግጅት ላይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ እና እህት አሌሳንድራ ሰሜሪሊ ንግግር አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጄኔቭ የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ተልዕኮ፥ “የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊነት እና የመንከባከብ ሁለንተናዊ ኃላፊነት” በሚል ርዕሥ ዓርብ ኅዳር 28/2016 ዓ. ም. ከፍተኛ ዝግጅት ማቅረቡ ታውቋል። ዝግጅቱ፥ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የወጣበት 75ኛ ዓመት ለማክበር እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ውዳሴ ለእግዚአብሔር” በሚለው ቃለ ምዕዳናቸው በአየር ንብረት ቀውስ ላይ የሰጡትን ሐዋርያዊ ማሳሰቢያን ይፋ ለማድረግ የተካሄደ እንደ ነበር ታውቋል። ለዝግጅቱ በጋራ ድጋፍ ያደረጉት፥ የማልታ ሉዓላዊነት ቋሚ ተልዕኮ ሠራዊት፣ "ቸርነትን በእውነት” የተሰኘ ፋውንዴሽን፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የስደተኞች ኮሚሽን እና በጄኔቭ የሚገኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ካቶሊክ ድርጅት መሆናቸው ታውቋል።

ሕይወትን ከጉዳት መከላከል

ጄኔቭ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶር ባሌስትሬሮ ስብሰባውን በመምራት የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ሕይወትን ከጉዳት ለመከላከል የሚያግዝ የማዕዘን ድንጋይ ነው” በማለት የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ፥ ድርጅቱ “የሰው ልጅ ክብርን እና ከእርሱ የሚመጡትን ሰብዓዊ መብቶች በመደበኛነት የሚጠብቅ እና የሚያስተዋውቅ ነው” በማለት አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳሱ ከዚህም ጋር በማያያዝ፥ የእነዚህ ሰብዓዊ መብቶች መነሻዎች “በእግዚአብሔር በተፈጠረው እያንዳንዱ ሰው ክብር ውስጥ የሚገኙ ናቸው" ብለው፥ በዚህች ምድር ላይ ያለውን የግንኙነት ትስስር የሚያጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶር ባሌስትሬሮ በመቀጠልም፥ በዓለም አቀፉ ድንጋጌ አንቀጽ 3 ላይ የተገለጸው ድንጋጌ በሁሉም ደረጃዎች በሕይወት የመቆየት መብትን፥ ማለትም ከጽንስ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ በተለይም በሕመም ምክንያት ሕይወት ለአደጋ በሚጋለጥበት ወቅት፣ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች ሰዎች ከግጭት፣ ከአደጋ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች በሚሸሹበት ወቅት እና እንዲሁም በሥራ ቦታም መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ የሚያሳስብ መሆኑን አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ በተጨማሪም፥ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፥ 'በሰው ልጅ ሕይወት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ ለሚሰነዘረው ጥቃት ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ የሚያቀርብ መሆኑን ገልጸዋል። የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአየር ንብረት ቀውስን በማስመልከት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰጡትን ማስጠንቀቂያን በመጥቀስ፥ “የምንኖርበት ዓለም ሊፈርስ እና ሊሰባበር የሚችልበት ጊዜ በተቃረበበት ወቅት የምንሰጠው እንክብካቤ በቂ አይደለም” ሲሉ የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ደግመዋል።

ሥነ-ምህዳራዊ ሃላፊነት እና ማህበራዊ ፍትህ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ “ውዳሴ ለእግዚአብሔር” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ለሁባኤው ተካፋዮች ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፥ ሰብዓዊ መብቶች እና ፍጥረትን ከአደጋ መጠበቅ “የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው” ብለዋል። አክለውም፥ “ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በመንከባከብ እና ለምድራችን በምናደርገው እንክብካቤ መካከል ጥልቅ እና ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለ ገልጸው፥ ሁለቱም የተመሠረቱት ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ በመገንዘብ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

እህት አሌሳንድራ በመቀጠም፥ ያልተገደበ ዕድገት አፈ ታሪክ እና የሐሰት አመክንዮ፥ ትርጉም የለሽ ኢኮኖሚያዊ የዕድገት ዘዴ እና ለተፈጥሮ ሃብቶች ምዝበራን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሠረት እንዳላቸው አፅንዖት ሰጥተዋል። እህት አሌሳንድራ፥ ሥነ-ምህዳራዊ ኃላፊነት ከማኅበራዊ ፍትህ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ሰብዓዊ መብቶችን ከማክበር እና ከማስከበር ጋር የተቆራኘ መሆኑን አስረድተዋል።

እህት አሌሳንድራ በማጠቃለያቸው፥ ለወደፊቱ ትውልዶች ለምናወርሰው ዓለም ያለንን ሥነ-ምግባራዊ ሃላፊነት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲቀበል በማሳሰብ ንግግራቸውን አጠናቅቀዋል።

 

11 December 2023, 16:45