ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቫቲካን የምጣኔ ሃብት ጽ/ቤት ሠራተኞች ጋር   ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቫቲካን የምጣኔ ሃብት ጽ/ቤት ሠራተኞች ጋር   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቫቲካን የምጣኔ ሃብት ጽ/ቤት ሠራተኞች ጋር ተገናኙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቫቲካን የኤኮኖሚ ጽ/ቤት ሠራተኞች ጋር በመገናኘት በቅድስት መንበር በሚገኙ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ የተደረጉ ማሻሻያዎች ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ከጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ ከሆኑት ከአቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ሌዶ የቀረበላቸውን ሪፖርት አድምጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው የቫቲካን የምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችን እና ተባባሪዎቻቸውን ሰኞ ኅዳር 3/2016 ዓ. ም. በግል ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል። ጽሕፈት ቤቱ በቫቲካን የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ፣ የአስተዳደር፣ የኮምፒዩተር እና የሰው ሃብት ቁጥጥር እና መስክ ዙሪያ እንደሚሠራ ታውቋል።

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ሌዶ ለቀዱስነታቸው ባደረጉት አጭር የመግቢያ ሰላምታ፥ ተቋማቸው አጭር ዕድሜ ያለው እና በቫቲካን የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ጅምር ላይ የተቋቋመ መሆኑን ገልጸው፥ ከልዩ ልዩ የሥራ መዋቅሮች ጋር በመተባበር፥ በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን ለማሻሻል የተወሰደውን የተሃድሶ ሂደት እንዲከታተል በአደራ የተሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ ያለ ተቋም መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ሌዶ በንግግራቸው፥ የምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤታቸው ሃላፊነት የተሃድሶ ሂደትን ለመደገፍ በየጊዜው በሚያደረገው የቁጥጥር እና የአስተዳደር ሂደቶች መካከል ሚዛናዊነት እንዲኖር ለማድረግ፥ ከግልጽነት እና ከሃብቶች ጥበቃ አስፈላጊነት አንፃር ውጤታማነትን መሠረት በማድረግ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተልዕኮን እውን ለማድረግ የሚረዱ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች የአስተዳደር ቅልጥፍናን ማረጋገጥ እንደሆነ አጽንዖትን ሰጥተዋል።

አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ አክለውም፥ የምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ያተኮረባቸውን ዋና ዋና ማሻሻያዎች በማሳየት፥ እስካሁን የተገኘው ዕድገት በሁሉም የምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች እና ተባባሪዎች አስተዋፅዖ መሆኑን ገልጸዋል።

ዕለት ተዕለት በአገልግሎት ላይ መሻሻልን ለማሳየት የእያንዳንዱ ሰው አስተዋፅዖ ወሳኝ በመሆኑ ተጨባጭ እና ለጋስ ጥረቶችን ማድረግ ለሥራው አስፈላጊ ነው ብለዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በተለያዩ ዘርፎች የተዘረጋውን አዲስ የአሠራር ሂደትን ለማሻሻል እና የቅድስት መንበርን ሃብት ዘላቂነትን እና ጥበቃን ከማረጋገጥ አንጻር አሁንም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ጨምረው ገልፀዋል።

አቶ ማክሲሚኖ በማጠቃለያቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤት ጋር ላደረጉት ቅርበት አመስግነው፣ የቅዱስነታቸው ድጋፍ ገና ባልተጠናቀቀ መንገድ ላይ ለመራመድ ወሳኝ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች የስንብት ሰላምታቸውን ከማቅረባቸው በፊት፥ ግልጽነት እና ቁጥጥርን በተመለከተ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተስተካከሉ እና ውጤታማ የሆኑ አሠራሮችን በመለየት በተካሄደው መንገድ እንዲቀጥሉ ጋብዘዋቸዋል።

 

16 November 2023, 14:17