ፈልግ

ካርዲናል ፓሮሊን፥ ቅድስት መንበር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ቁርጠኛ አቋም እንዳላት አስታወቁ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ በተባበሩት መንግሥታት አስተባባርነት በአቡ ዳቢ ከሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ቀደም ብለው በሰጡት አስተያየት፥ ቅድስት መንበር እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአየር ንብረት ቀውስን ለመቅረፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓለማችን ዋና ዋና የሃይማኖት ማኅበረሰቦችን እና ባሕሎችን የሚወክሉ ሰላሳ የሚደርሱ የእምነት መሪዎች ምዕመናኖቻቸውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ቁርጠኝነታቸውን እንደሚያሳዩ እና በሚቀጥለው ወር በአቡ ዳቢ ከተማ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት “COP28” የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስዱ የሚጠይቅ የሃይማኖት ድርጅቶች መግለጫን በጋራ ፈርመዋል።

በአቡ ዳቢ ከተማ ሰኞ ጥቅምት 26/2016 ዓ. ም. ማምሻውን በተካሄደው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ተሳትፈዋል። የፊርማው ሥነ-ሥርዓት የተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመቋቋም የሃይማኖት መሪዎች እና አማኞች ድምጻቸውን ለማሰማት በተገኙበት የዓለም የሃይማኖት መሪዎች እና ተወካዮች ባካሄዱት ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ማጠቃለያ ላይ እንደነበር ታውቋል።

ከሥነ-ሥርዓቱ ቀጥለው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቆይታን ያደረጉት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የእምነት መሪዎች እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ዓለም አቀፍ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ሊጫወቱ ስለሚችሉት ሚና እና ቅድስት መንበር በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ ያላትን ልዩ ሚና በማስመልከት ገለጻ አድርገዋል።

ጥያቄ፡- የአየር ንብረት ለውጥ በተመለከተ የእምነት መሪዎች ሊጫወቱ የሚችሉት ሚና ምን እንደሆነ እና ጉዳዩ በብዙዎች ዘንድ እንደ ዓለማዊ ጉዳይ የሚመለከተው ለምንድነው?

መልስ፥ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በእርግጥም ዓለማዊ ርዕሥ በመሆኑ ፖለቲከኞች እና በፖለቲካው ዓለም ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እና የሳይንስ ጠበብት የሚወያዩበት ርዕሠ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረው፥ ነገር ግን በዚህ አንድምታ ውስጥ የአገራት እና የሃይማኖት መሪዎች በእጅጉ የሚያሰምሩበት፣ ጉዳዩ ሥነ-ምግባራዊ እና ሞራላዊ ይዘት ያለው በመሆኑ እንደሆነ ገልጸው፥ በመሆኑም የሃይማኖት መሪዎች ሃሳባቸውን በማጋራት መላው ዓለም ችግሩን ለመፍታት ባለው ቁርጠኝነት ላይ ተነሳሽነት ለመጨመር የሚያግዙ ድምጾች እንዳሏቸው ተናግረዋል።

ጥያቄ፡- በመላው ዓለም ውስጥ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ውክልና ያላት በሃይማኖቶች መካከል ልዩ ሚናን የምትጫወት በመሆኑ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ባሉ ጉዳዮች ላይ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና የቅድስት መንበር ልዩ ሚናን እንዴት ያዩታል? ተብለው የተጠየቁት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣

መልስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረው፥ ለዚህም ማስረጃው “ውዳሴ ላንት ይሁን” ከተባሉ ሁለቱ ሠነዶች መካከል የመጀመሪያው ሠነዳቸው የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት በተፈረመበት የፓሪሱ ጉባኤ ወቅት ለብዙ የዓለም መሪዎች እና ለበርካታ መንግሥታት ማጣቀሻ ነጥብ ሆኖ እንዳገለገለ አስታውሰው፥ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ያዘጋጁት ሁለተኛው የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሠነዳቸውም የመጀመሪያውን ሠነድ ለማጠናከር የተዘጋጀ እንደሆነ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አክለውም ቅድስት መንበር በሁሉም የችግሩ ገጽታዎች ላይ መፍትሄዎችን ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፥ የጋዝ ልቀት፣ የባሕር ከፍታ መጨመር እና ለሌሎች ችግሮችም የመፍትሄ ሃሳቦችን እንደምታቀርብ ገልጸዋል። ትኩረታቸው በተለይ በሁለት ነገሮች ላይ እንደሆነ የተነገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የመጀመሪያው የአኗኗር ዘይቤን መለወጥ እንደሆነ ተናግረው፥ ችግርን ለመቅረፍ ብዙ ገንዘብ ማውጣት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፥ ሌሎች ተጨማሪ መንገዶችን መጥቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት ፍጥረትን ለጉዳት አሳልፎ ከመስጠት እና ተፈጥሮን ከማውደም ይልቅ በመንከባከብ የአኗኗር ዘይቤን መለወጥ እንደሚገባ እና ይህም እግዚአብሔር የሰው ልጅን ሲፈጥር የሰጠው አደራ ነው ብለዋል።

ትምህርት ሌላው እጅግ አስፈላጊ ነጥብ እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ አዲሱ ትውልድ የዚህን ዓለም ሃብት እንዴት እና በምን ዓይነት መንገድ መጠቀም እንዳለበት ማስተማር የመላው ዓለም እና የዓለም አቀፋዊት ቅድስት መንበር ቁርጠኝነት መሆኑን በፓሪሱ ስምምነት ወቅት ቅድስት መንበር በፊርማ ማረጋገጧን አስታውሰዋል።

ቫቲካን ቃል ኪዳን የገባችባቸው ነጥቦች መኖራቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በዚህ ደረጃ አንዳንድ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችሉ ተናግረው፥ የቫቲካን ግዛት ትንሽ እንደሆነች እና በክስተቱ ላይ ጉልህ ተጽእኖ ማድረግ ባትችልም ነገር ግን አዲሱ ትውልድ የዚህን ዓለም ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀም ለማስቻል ከትምህርት ጎን ለጎን ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደምትችል ተናግረዋል።

 

07 November 2023, 17:33