ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥  

ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ታጋቾችን ለማስለቀቅ የተደረገው ስምምነት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው እርምጃ ነው” አሉ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በሐማስ የታገቱት እስራኤላውያንን ለማስለቀቅ የተደረሰውን ስምምነት መልካም እንደሆነ ተመልክተው፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ደም አፋሳሽ ለሆነው ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ እንደሚገኝ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከታጋቾቹ ቤተሰቦች እና ከፍልስጤማውያን ቡድን አባላት ጋር ያደረጉትን ግንኙነት አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፥ ቀጥለውም በወጣት ጁሊያ ቼኬቲኒ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ወንጀል በማስመልከት በሰጡት አስተያየትም ሴት በመሆናቸው ምክንያት የሚፈጸም ጥቃት እንዲቆም በመመኘት መልካም ዓላማዎችን ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በእስራኤል እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል ኅዳር 12/2016 ዓ. ም. የተፈረመው የተኩስ አቁም እና ወደ 50 የሚጠጉ ታጋቾችን ለማስፈታት የተፈረመው ስምምነት እጅግ ጠቃሚ እርምጃ ነው ብለው፥ በሮም በተካሄደው የቅድስት መንበር ታሪካዊ እና የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ጥበቃ ቋሚ ኮሚሽን ጉባኤ ላይ ተገኝተው በሰጡት አስተያየት፥ የታጋቾች መለቀቅ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት ከማቆም ጋር ተዳምሮ ለሰላም ጥረቱ ቁልፍ እንደሆነ፥ ችግሩ በዚህ መንገድ መፍታት ከተጀመረ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ደም አፋሳሽ ግጭት ለማስወገድ ድርድር በመጀመር ወደ ሰላማዊ መፍትሄ ላይ መድረስ እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ከታጋቾች ቤተሰቦች እና ከፍልስጤማውያን ቡድን ጋር የተደረገው ግንኝነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍልስጤማዊ ታዳሚዎችን ኅዳር 12/2016 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ “ዘር ማጥፋት" የሚል ቃል ተናግረው እንደ ሆነ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የተጠየቁ ሲሆን፥ በዚህ ጊዜ የቫቲካን መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ በሰጡት ምላሽ፥ ቅዱስነታቸው ይህን ቃል ስለመጠየቃቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌላቸው ገልጸው፥ በሳምንታዊው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት የተናገሯቸውን ቃላት በመድገም ጋዛ ውስጥ የተፈጠሩ አስከፊ ሁኔታዎችን የሚገልጹ ቃላትን ከመናገር በቀር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ዘር ማጥፋት” የሚል ቃል ተጠቅመዋል ብሎ ማሰብ ከእውነታው የራቀ ነው” ሲሉ የመግለጫ ክፍሉ ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ተናግረዋል። የዘር ማጥፋት ወንጀል በተወሰኑ ሁኔታዎች ላይ የሚተገበር ቴክኒካል ቃል እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በበኩላቸው፥ ጋዛ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ ስለ ዘር ማጥፋት መነጋገር የሚቻል እንደሆነ አላውቅም ብለው፥ ነገር ግን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ቃል ተጠቅመዋል ብሎ ማሰብ ለእውነታው የራቀ ነው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ቫቲካን ውስጥ በእንግድነት ከተቀበሏቸው የእስራኤል ታጋቾች ቤተሰቦች መካከል አንዱ የሐማስ ታጣቂዎችን ሳይጠቅሱ “ሽብርተኝነት” በማለታቸው ምክንያት የተሰማውን ቅሬታ ገልጾ ሊሆን ይችላል ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ሁሉንም ሰው ማስደሰት ዘወትር አስቸጋሪ ነው” ብለው፥ አክለውም ቅዱስነታቸው በተለምዶ ሰዎችን በስማቸው ሳይሆን በጥቅሉ እንደሚጠሩ ገልጸው፥ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ መሄድ የቅድስት መንበር ጠቅላላ ዘይቤ ነው ብለው እንደማያምኑ ብጹዕነታቸው አስረድተዋል።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ስጋት

በመጨረሻም በጣሊያን ውስጥ በሴቶች ላይ በሚደርስ ጥቃት ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በቅርቡ ጁሊያ ቼኬቲኒ በተባለች የ22 ዓመት ወጣት ላይ በቀድሞ ፍቅረኛዋ የተፈጸመው አስከፊ የግድያ ተግባር በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረው፥ ከሕዝቡ የቀረቡትን በርካታ ሰላማዊ ምላሾች እና መልካም አስተያየቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በሕግ አውጭዎች ደረጃ የሕዝብ አስተያየቶችን በማሰባሰብ ክስተቱን ወሳኝ እና ቆራጥ በሆነ መንገድ ለማወቅ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አሳስበዋል። 

 

23 November 2023, 18:12