ፈልግ

እ.አ.አ. በ2021 የተከበረው የዘረኝነት ቀን ላይ የተደረገ እ.አ.አ. በ2021 የተከበረው የዘረኝነት ቀን ላይ የተደረገ  (Copyright 2011 Brett Jorgensen Photography)

ቅድስት መንበር በስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን ዘረኝነት እና የሃይማኖት አድልኦን አወገዘች

በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጋብሪኤሌ ካቺያ በስደተኞች እና በፍልሰተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር መድልዎ እና ሃይማኖታዊ አለመቻቻል እየጨመረ በመምጣቱ የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ቅድስት መንበር በሁሉም ዘርፍ ያሉትን ‘አስፈሪ እና አስጸያፊ የዘረኝነት ተግባራትን’ በቆራጥነት ለመቅረፍ እና ተዛማጅ የሃይማኖት አለመቻቻልን፣ አድልዎን እና ስደትን ለማስወገድ ጥሪዋን በተደጋጋሚ አቅርባለች።

በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቺያ “በሕግ ላይ የሚታዩ መሻሻሎች እና በሕጉ ላይ ጉልህ ለውጦች ቢደረጉም የዘረኝነት እውነታ አሁንም ድረስ አለ” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።

የእያንዳንዱን ሰው ተፈጥሮአዊ ክብር ማዋረድ

የቫቲካኑ ጳጳስ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ለሦስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በሰጡት መግለጫ “የሰው ልጅ ተራ ወደሆነ ባሕርይ ተቀይሮ ‘አንዱ ከሌላው ይበልጣል’ የሚለው አመለካከት ዘረኝነትን መሠረት ያደረገ ‘የተሳሳተ እምነት’ እንደሆነ አስታውሰዋል። አክለውም “የእያንዳንዱን ሰው የተፈጥሮ ክብር መናቅ ነው” ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል።

“ሁሉም የሰው ልጅ አባላት አምላክ የሰጠን አንድ አይነት ክብር ስላላቸው፥ አንድ ዓይነት መብትና ግዴታ ሊኖራቸው ይገባል”

ስደተኞች የፖለቲካው ችግር አይደሉም ነገር ግን የሰው ልጆች ችግር ናቸው

በተለይም በስደተኞች፣ በፍልሰተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የሚፈጸሙትን ‘መወቀስ የሚገባው የዘረኝነት፣ የውጭ ዜጋ ጥላቻ እና መድልዎ ‘የዘረኝነት አስተሳሰብ ግልፅ መገለጫዎች’ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። “ስደተኞች እንደማንኛውም ሰው ተፈጥሮአዊ ክብር ተሰጥቷቸው ስለማይታዩ በግልጽ ማግለል ይደርስባቸዋል” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ካቺያ ዘረኝነትን አውግዘዋል።

“ስደት ፍርሃትንና ስጋትን ሊፈጥር ይችላል፥ በመሆኑም ብዙውን ጊዜ ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ ሲውል ይታያል፥ ስለዚህ ይህንን ልዩ ጉዳይ ‘በቆራጥነት’ መፍታት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

“ስደተኞች በቀላሉ የሚወገዱ ፖለቲካዊ ችግሮች ሳይሆን መታየት ያለባቸው እንደ ማንኛውም ሰው ተመሳሳይ የሆነ ውስጣዊ ክብር እና ዋጋ ያላቸው ሰዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል”

አሳሳቢ የሆነው የሃይማኖት መድልዎ መጨመር

የቫቲካን ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጋብሪኤሌ ካቺያ በተጨማሪም የሃይማኖታዊ አለመቻቻል፣ መድልዎ እና የስደት ጉዳዮች በቀጣይነት እየጨመሩ በመምጣታቸው ቅድስት መንበር ጥልቅ ስጋት እንዳደረባት ገልፀዋል። የሃይማኖት ነፃነት በጣም የተገደበባቸውን በርካታ ቦታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት “በክብር ለመኖር ከሚያስፈልጉት ዝቅተኛ መስፈርቶች ውስጥ አንዱ በመሆኑ መንግስታት የዜጎቻቸውን መብት የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው” ሲሉ አስታውሰዋል።

ሊቀ ጳጳስ ካቺያ በመቀጠል ሁሉንም ልዩነቶችን እና ባህሎችን የሚያስወግደውን እና ወደ ወጥ የሆነ አንድ አይነትነት ፍለጋ የሚመራውን የ ‘ሌላነት’ አስተሳሰብ ፍራቻን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አስጠንቅቀዋል።

'ሌላነት'ን የመፍራት አባዜን የሚቀርፈው የውይይት ባህል ነው

አቡነ ገብርኤል ካችያ የዚህ ‘የውሸት ዓለም አቀፋዊነት’ ማርከሻው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጳጳሳዊ ደብዳቤያቸው በሆነው ‘ፍራቴሊ ቱቲ’ ውስጥ የጠቀሱትን ቃላቶችን በማስተጋባት “የእያንዳንዱን ሰው እና የእያንዳንዱን ህዝብ የበለጸጉ ስጦታዎች እና ልዩ የመሆን መብት ለማረጋገጥ የውይይት ባህል ውስጥ መገኘት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ሊቀ ጳጳስ ካቺያ በማጠቃለያቸው ለሁሉም የሰው ልጆች እኩል ክብር የሚሰጠውን እ.አ.አ. በ1948 በወጣው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ ላይ የሰፈረውን “ለዘረኝነት ወይም ማግለል ፈጽሞ ዓይናችንን መጨፈን እንደማይገባን፡ ነገር ግን እያንዳንዱን ሰው በግልፅ፣ በአብሮነት እና በፍቅር እንድንቀርብ” የሚደነግገውን ተግባራዊ እንድናደርግ ጠይቀዋል።

“ዘረኝነት የሰውን ልጅ ክብር የሚነፍግ እና የሰውን ልጅን የሚከፋፍል አጥፊ እና አስጸያፊ ተግባር ነው። ማንም ሰው በዘሩ፣ በቀለሙ፣ በጾታ፣ በቋንቋው፣ በሃይማኖቱ፣ በፖለቲካ አስተሳሰቡ ወይም በሌሎች አመለካከቱ፣ በብሔር ወይም በማህበራዊ አመጣጡ፣ በንብረቱ፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት በህግ ወይም በተጨባጭ ሁኔታም መገለል ዬለበትም” 
 

02 November 2023, 14:34