ፈልግ

የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት ለማስቆም ፈረንሳይ ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት ለማስቆም ፈረንሳይ ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት  (AFP or licensors)

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ለሰላም ውይይት አስፈላጊነት ትኩረት መስጠታቸው ተገለጸ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የወቅቱን የጦርነት ሁኔታ በማስመልከት አስተያየት ሰጥተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባላፈው ረቡዕ ሳምንታዊ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት፥ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በቅድስት አገር ሕዝቦች ላይ እየደረሰ ባለው ስቃይ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ “ይህ ጦርነት ሳይሆን ሽብርተኝነት ነው” በማለት የገለጹትን እና የተጠቀሙባቸውን ሌሎች ቃላትንም በማስመልከት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ሐሙስ ኅዳር 13/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በሮም ካሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ቀደም ብሎ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስራኤል እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል ያለውን ጦርነት አስመልክተው በረቡዕ ሳምንታዊ አስተምህሮአቸው ወቅት ያሰሙትን ንግግር ተከትሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቅድስት መንበር በሁሉም መንገድ ፍትሃዊ ለመሆን እና የሁሉንም ሰው ስቃይ ከግምት ውስጥ ለማስገባት የምትጥር ይመስለኛል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በቅርቡ የሐማስ ታጣቂዎች በእስራኤላውያን ላይ የፈጸሙትን ጥቃት እና እንደዚሁም በፍልስጤም በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና ለመከራ መዳረጋቸውን በመቃወም ቫቲካን ግልጽ አቋም እንዳላት ተናግረዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዚህ ቃለ ምልልሳቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ግጭት ለሚሰቃዩት በሙሉ ያላቸውን ቅርበት አመልክተዋል። የውይይት መድረኮችን ለመክፈት የሚደረገው ጥረት በማስመልከት ተጠይቀው ሲመልሱ፥ ጥረቱ የታገቱትን ለማስለቀቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኩል የተደረገው እንቅስቃሴ ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት እንድመኢረዳ አምናለሁ ብለዋል።

ወደ ሩሲያ የተወሰዱ የዩክሬን ልጆች ጉዳይ

በግዳጅ ወደ ሩሲያ ስለተወሰዱት የዩክሬን ሕጻናትን በማስመልከት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን እንደተናገሩት፥ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ወደ ሞስኮ እና ወደ ኪየቭ ተጉዘው ያደረጓቸው የዲፕሎማሲ ጥረቶች የተወሰኑ ውጤቶችን እያስገኙ መሆናቸውን እና በሂደት ላይ የሚገኙ ጥረቶችም መሻሻሎችን ማሳየታቸውን ገልጸዋል። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን እንዲያቆሙ የሚቀርብላቸው ጥሪ ተቀባይነት እንደሚኖረው ያላቸውን ተስፋ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል።

የፀረ-ሴማዊነት ስጋት

በሐማስ ታጣቂዎች እና በእስራኤል ጦር መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ መታየት የጀመረው የፀረ ሴማዊነት ማዕበል አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች ቅድስት መንበርን በእጅጉ እንደሚያሳስባት ተናግረዋል።

“በእኛ ዘመን” የሚለው ሐዋርያዊ ሠነድ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ዓመታት ውስጥ የታዩት ስኬቶች በእርግጠኝነት ጥያቄ ውስጥ አይገቡም" ብለዋል። በሐማስ ታጣቂዎች እና በእስራኤል ጦር መካከል የተደረሰው ስምምነት አፈፃፀም አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ ስምምነቱም ተግባራዊነቱን እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ በማረጋገጥ የታጋቾችን ጉዳይ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቅድስት መንበር አሠራር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቅድስት ሀገር ውስጥ ስላለው ጦርነት ሲናገሩ፥ “ሽብርተኝነት” የሚለውን ቃል በመምረጣቸው ምክንያት ለተሰነዘሩባቸው ትችቶች ምላሽ ሲሰጡ፥ የቀረቡባቸው ትችቶች በሙሉ ፍትሃዊ አይደሉም በማለት ካርዲናል ፓሮሊን አጣጥለዋቸዋል። "ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማለት የሚፈልጉትን በግልጽ እንደሚናገሩ እና ተፋላሚ ወገኖች በሚፈልጉት መንገድ አይናገሩም” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመጨረሻም አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ስለ ሰላም በተወያዩበት አውድ ላይ፣ የገለልተኝነት አቋምን በመጠበቅ እና ሁለቱንም ወገኖች ለማነጋገር የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ገልጸው፣ ቅድስት መንበር ግጭቶችን በሚመለከት ሁልጊዜም ትችት እንደሚደርስባት አምነዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መባል ያለበትን ከመናገር ወደ ኋላ እንደማይሉ፣ ነገር ግን የቅድስት መንበርን አሠራር እና ዘይቤ በመከተል እንደሆነ አስረድተዋል።

25 November 2023, 16:53